መጽሐፈ ባሮክ 2

2
1ስለዚህ ጌታ በእኛ ላይና እስራኤልን ያስተደድሩ በነበሩት ዳኞች ላይ፥ በንጉሦቻችን ላይ፥ በገዢዎቻችን ላይ፥ በእስራኤልና በይሁዳ ሰዎች ላይ ተናግሮት የነበረውን ፍርድ ፈጸመ። 2በሙሴ ሕግ ላይ በተጻፈው መሠረት በኢየሩሳሌም እንዳደረገው ከሰማይ በታች በየትም አልተደረገም። 3አንዳንዱ ሰው የወንድ ልጁን ሥጋ ሌላው ሰው የሴት ልጁን ሥጋ በላ፤ 4ጌታ እነርሱን በበተነበት በዙሪያቸው በሚገኙት ሕዝቦች ሁሉ መካከል ለውርደትና ለመከራ እንዲሆኑ በዙሪያችን ባሉ መንግሥታት ሁሉ እንዲገዙ አሳልፎ ሰጣቸው። 5ድምጹን ባለመስማት ጌታ አምላካችንን ስለበደለን ዝቅ ተደረጉ፥ ክፍም አላሉም። 6ጽድቅ የጌታ የአምላካችን ነው፤ በእኛና በአባቶቻችን ግን እንደ ዛሬው ቀን የፊት ኀፍረት ነው። 7እነዚያ ጌታ በእኛ ላይ እንደሚደርሱ የነገረን መከራዎች ሁሉ ደረሱብን። 8ሆኖም እያንዳንዳችንን ከመጥፎ ልባችን ሐሳብ ለመመለስ የጌታን ፊት አልለመንንም። 9ጌታ መከራዎቹን ጠብቆ አቆያቸው፥ ጌታም በእኛ ላይ አመጣቸው፥ እንድናደርገው ባዘዘን ነገር ሁሉ ጌታ እውነተኛ ነውና፤ 10ነገር ግን በፊታችን ባስቀመጣቸው በጌታ ትእዛዞች መሠረት እንድንሄድ የተናገረንን ድምጹን አልሰማንም። 11አሁንም ሕዝብህን ከግብጽ ምድር በብርቱ እጅ፥ በተአምራትና በድንቅ ነገሮች፥ በታላቅ ኃይልና በተዘረጋ ክንድ ያወጣህ፥ እስከ ዛሬም ድረስ ያለ ስምን ያደረግህ የእስራኤል አምላክ ጌታ ሆይ፤ 12ኃጢአትን ሠርተናል፥ ክፉ ሰዎች ሆነናል፥ ስህተት ሰርተናል፥ ጌታ አምላካችን ሆይ ትእዛዞችህን ሁሉ አፍርሰናል። 13እኛን በበታተንህበት አገሮች መካከል በቍጥር ጥቂት ሆነን ተጥለናልና መዓትህ ከእኛ ወዲያ ይራቅ። 14ጌታ ሆይ ጸሎታችንንና ልመናችንን ስማ፤ ስለ ራስህ ስትል አድነን፥ በማረኩን ሰዎች ፊት ሞገስን ስጠን፤ 15በዚህ ዓይነት ምድር ሁሉ አንተ ጌታ አምላካችን መሆንህን ትወቅ፤ እስራኤልና ዘሩ በአንተ ስም ተጠርቶአልና። 16ጌታ ሆይ ከቅዱስ ማደሪያህ ላይ ሆነህ ተመልከት፥ እኛንም አስበን፤ ጌታ ሆይ ጆሮህን አዘንብል፥ ስማ። 17ጌታ ሆይ ዐይኖችህን ክፈትና እይ፥ በሲኦል የሚገኙ ሙታን፥ መንፈሳቸው ከሥጋቸው የተወሰደባቸው፥ ክብርን ወይም ተገቢውን ነገር ለጌታ አይሰጡም፤ 18ነገር ግን በጣም ያዘነች ነፍስ፥ አጎንብሳ የምትሄድና አቅም ያነሳት፥ የፈዘዙ ዐይኖችና የተራበች ነፍስ፥ ክብርን ወይም ተገቢውን ነገር ለጌታ ይሰጣሉ። 19ጌታ አምላካችን ሆይ በፊትህ የምሕረት ጸሎት የምናቀርበው በአባቶቻችንና በንጉሦቻችን በሰሩት የጽድቅ ሥራ አይደለም፤ 20በአገልጋዮችህ በነቢያት አማካይነት እንደተናገርህ፥ መዓትህንና ቁጣህን በእኛ ላይ ላክህ፤ እንዲህም አልህ፦ 21#ኤር. 7፥34፤ 27፥10-12።ጌታ እንዲህ ይላል፥ ትከሻችሁን ዝቅ አድርጉ፥ የባቢሎንን ንጉሥንም አገልግሉ፤ ለአባቶቻችሁ በሰጠኋት ምድርም ትቀመጣችሁ፤ 22ነገር ግን ለጌታ ድምጽ የማትታዘዙ ከሆነ፥ የባቢሎንንም ንጉሥ የማታገለግሉ ከሆነ፤ 23የሣቅና የደስታ ድምጽ፥ የሙሽራና የሙሽሪት ድምጽ ከይሁዳ ከተሞችና ከኢየሩሳሌም እንዲቋረጥ አደርጋለሁ፥ ምድሪቱ በሙሉ ነዋሪዎች የሌሉበት በረሀ ትሆናለች። 24#ኤር. 8፥1፤2።ነገር ግን የባቢሎን ንጉሥ ለማገልገል ድምጽህን አልሰማም፤ የንጉሦቻችን ዐፅሞችና የአባቶቻችን ዐፅሞች ከቦታቸው እንደሚወጡ በአገልጋዮችህ በነቢያት እጅ የተናገርኸው ቃል ፈጸምከው። 25እነሆ በቀን ሐሩርና በሌሊት ውርጭ ላይ ተጥለዋል፤ እነሱም በረሀብ፥ በሰይፍና በቸነፈር ክፉ ሞትን ሞቱ። 26በእስራኤል ቤትና በይሁዳ ቤት ክፋት ምክንያት ስምህ የተጠራበትን ቤት ዛሬ በሚታይበት ሁኔታ ላይ ጣልኸው። 27ሆኖም ጌታ አምላካችን ሆይ እንደ ደግነትህ ሁሉና እንደ ታላቁ ርህራሄህ ሁሉ አደረግህልን፥ 28#ዘዳ. 28፥58፤62።በእስራኤል ልጆች ፊት ሕግህን እንዲጽፍ ባዘዝኸው ቀን፥ በአገልጋይህ በሙሴ እንዲህ ስትል እንደ ተናገርኸው ነው፥ 29“ድምጼን የማትሰሙ ከሆነ፥ ይህ በጣም ብዙ ሕዝብ በምበትናቸው አገሮች መካከል ወደ ጥቂት ቍጥር ይመለሳል። 30አንገተ ደንዳና ሕዝብ ሰለሆኑ እንደማይሰሙኝ ኣውቃለሁና፤ ነገር ግን በተሰደዱበትም ምድር ወደ ልባቸው ይመለሳሉ፥ 31እኔም ጌታ አምላካቸው እንደሆንሁ ያውቃሉ፤ የሚታዘዝ ልብና የሚሰሙ ጆሮዎችን እሰጣቸዋለሁ፤ 32በተሰደዱበት ምድር ያመሰግኑኛል፥ ስሜንም ያስታውሳሉ፤ 33ከእልኸኝነታቸውና ከክፉ ሥራቸው ይመለሳሉ፤ በጌታ ፊት የበደሉ የአባቶቻቸውን መንገድ ያስባሉ። 34ለአባቶቻቸውም ለአብርሃም፥ ለይስሐቅና ለያዕቆብ እሰጣችኋለሁ ብዬ ወደ ማልሁላቸው ምድር አመጣቸዋለሁ፥ ይገዙአታልም፤ አበዛቸዋለሁ፤ በቍጥር ም አይቀንሱም። 35#ኤር. 32፥38-40።አምላካቸው ለመሆን የዘለዓለም ቃል ኪዳን ከእነርሱ ጋር እገባለሁ፥ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ፤ ሕዝቤ እስራኤልን ከስጠኋቸው ምድር ዳግም አላወጣቸውም።”

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ