በጽዮን ላሉ ዓለመኞች፥ በሰማርያም ተራራ ላይ ተማምነው ለተቀመጡ፥ የእስራኤልም ቤት ወደ እነርሱ ለመጡባቸው ለአሕዛብ አለቆች ወዮላቸው! ወደ ካልኔ እለፉና ተመልከቱ፤ ከዚያም ወደ ታላቂቱ ሐማት ሂዱ፤ ከዚያም ወደ ፍልስጥኤም ጌት ውረዱ፤ እነርሱ ከእነዚህ መንግሥታት ይሻላሉን? ወይስ ድንበራቸው ከድንበራችሁ ይሰፋልን? ክፉውን ቀን ከእናንተ ታርቃላችሁን? የግፍንስ ወንበር ታቀርባላችሁን? ከዝሆን ጥርስ በተሠራ አልጋ ላይ ለምትተኙ፥ በምንጣፋችሁም ላይ ተደላድላችሁ ለምትቀመጡ፥ ከበጎችም መንጋ ጠቦትን ከጋጥም ውስጥ ጥጃን ለምትበሉ፥ በበገናም ድምፅ ለምትንጫጩ፥ እንደ ዳዊትም ለራሳችሁ የዜማን ዕቃ ለምታዘጋጁ፥ በፋጋ የወይን ጠጅ ለምትጠጡ፥ እጅግ ባማረ ቅባትም ለምትቀቡ፥ ስለ ዮሴፍ መከራ ግን ለማታዝኑ ለእናንተ ወዮላችሁ! ስለዚህ በመጀመሪያ ተማርከው ከሚፈልሱት ይሆናሉ፥ እንደ ፈቃዳቸው ከሚሆኑ መካከል ፈንጠዝያ ይርቃል። ጌታ እግዚአብሔር፦ “የያዕቆብን ትዕቢት ተጸይፌአለሁ፥ የንጉሥ ቅጥሮቹንም ጠልቻለሁ፤ ስለዚህ ከተማይቱንና በውስጧ ያለውን ሁሉ አሳልፌ እሰጣለሁ” ብሎ በራሱ ምሎአል፥ ይላል ጌታ የሠራዊት አምላክ። እንዲህም ይሆናል፤ ዐሥር ሰዎች በአንድ ቤት ውስጥ ቢቀሩ እነርሱ ይሞታሉ። የሞተውን ሰው የሚያቃጥለው ዘመዱ አጥንቱን ከቤቱ አንስቶት ባወጣው ጊዜ፥ በቤቱም በውስጠኛው ክፍል ያለውን፦ “በእዚያ እስከ አሁን ድረስ ከአንተ ጋር ሰው አለን?” ይለዋል፥ እርሱም፦ “ማንም የለም” ይላል፤ ያንጊዜ፦ “የጌታን ስም ልንጠራ አይገባንምና ዝም በል” ይለዋል። እነሆም፥ ጌታ ያዝዛል፤ ታላቁንም ቤት በማፍረስ፥ ታናሹንም ቤት በመሰባበር ይመታል። በውኑ ፈረሶች በዓለታም መሬት ላይ ይጋልባሉን? ወይስ ሰው በበሬዎች በዚያ ላይ ሊያርስ ይችላልን? ነገር ግን እናንተ ፍርድን ወደ ሐሞት፥ የጽድቅንም ፍሬ ወደ እሬት ለወጣችሁ፤ በሎዴባር ደስ የሚላችሁ፥ እናንተም፦ “በብርታታችን ቃርናይምን ለራሳችን አልወሰድንምን?” የምትሉ ናችሁ። “የእስራኤል ቤት ሆይ! እነሆ፥ እኔ አሕዛብን አስነሣባችኋለሁ፥” ይላል ጌታ የሠራዊት አምላክ፤ “እነርሱም ከሐማት መግቢያ ጀምረው እስከ ዓረባ ወንዝ ድረስ ያስጨንቋችኋል።”
ትንቢተ አሞጽ 6 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ አሞጽ 6:1-14
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች