አሞጽ 6:1-14
አሞጽ 6:1-14 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ጽዮንን ለሚንቁ፥ በሰማርያም ተራራ ለሚታመኑ ሰዎች ወዮላቸው፤ የአሕዛብን አለቆች ለቀሙአቸው። የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ወደ ካልኔ ተሻግራችሁ ተመልከቱ፤ ከዚያም ወደ ኤማትራባ እለፉ፤ ከዚያም ወደ ፍልስጥኤም ጌት ውረዱ፤ እነርሱ ከእነዚህ መንግሥታት ይበረታሉ፤ ድንበራቸውም ከድንበራቸው ይሰፋልና። ክፉ ቀንን ለሚፈልጓት፥ የሐሰት ሰንበታትን ለሚያቀራርቡና አንድ ለሚያደርጉ፥ ከዝሆን ጥርስ በተሠራ አልጋ ላይ ለሚተኙ፥ በምንጣፋቸው ደስ ለሚሰኙ፥ ከበጎችም መንጋ ጠቦትን፥ ከጋጥም ውስጥ ጥጃን ለሚመገቡ፥ ከበገናው ድምፅ ጋር አስተባብረው ለሚያጨበጭቡ ሰዎች፤ ይኸውም የማያልፍ ለሚመስላቸውና እንደሚያመልጣቸው ለማያውቁ፤ በጽዋ የቀላ ወይን ለሚጠጡ፥ እጅግ በአማረ ሽቱም ለሚቀቡ፥ በዮሴፍ ስብራት ለማያስቡ ወዮላቸው። ስለዚህ ከአለቆቻቸው አስቀድመው ይማረካሉ፤ ሯጮች የሚሆኑ የኤፍሬም ፈረሶችም ያልቃሉ። ጌታ እግዚአብሔር፥ “የያዕቆብን ትዕቢት አረክሳለሁ፤ ሀገሮቹንም ጠላሁ፤ ከተሞቹንም ከሚኖሩባቸው ሰዎች ጋር አጠፋለሁ” ብሎ በራሱ ምሎአልና። እንዲህም ይሆናል፤ ዐሥር ሰዎች በአንድ ቤት ውስጥ ቢቀሩ እነርሱ ይሞታሉ፤ የቀሩት ግን ይተርፋሉ። አጥንቶቻቸውንም ከቤት ያወጡ ዘንድ ቤተሰቦቻቸው በወሰዱአቸው ጊዜ፥ ቤት ጠባቂውን በአንተ ዘንድ የቀረ አለን? በአለው ጊዜ እርሱ የለም ይላል። ያም የእግዚአብሔርንም ስም እንዳትጠራ ዝም በል ይለዋል። እነሆም እግዚአብሔር ያዝዛል፤ ታላቁንም ቤት በማፍረስ፥ ታናሹንም ቤት በመሰባበር ይመታል። ፍርድን ወደ ቍጣ፥ የእውነትንም ፍሬ ወደ እሬት ለውጣችኋልና፥ በውኑ ፈረሶች በጭንጫ ላይ ይሮጣሉን? ወይስ በሬዎች በዚያ ላይ ያርሳሉን? በከንቱ ነገር ደስ የሚላችሁ በኀይላችን ቀንዶችን አበቀልን የምትሉ አይደለምን? “የእስራኤል ቤት ሆይ እነሆ እኔ የሚያስጨንቋችሁን ሕዝብ አስነሣባችኋለሁ፥” ይላል የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር፤ እነርሱም ከሐማት መግቢያ ጀምረው እስከ ዐረባ ወንዝ ድረስ ትገቡ ዘንድ አይፈቅዱላችሁም።
አሞጽ 6:1-14 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በጽዮን ተዘልላችሁ የምትቀመጡ፣ በሰማርያ ተራራ ያለ ሥጋት የምትኖሩ፣ የእስራኤልም ሕዝብ ለርዳታ ወደ እናንተ የሚመጡባችሁ፣ እናንተ የአሕዛብ አለቆች ሆይ፤ ወዮላችሁ! ወደ ካልኔ ሂዱ፤ እርሱንም ተመልከቱ፤ ከዚያም ወደ ታላቂቱ ሐማት ሂዱ፤ ወደ ፍልስጥኤም ከተማ ወደ ጋትም ውረዱ፤ እነዚህ ከሁለቱ መንግሥታታችሁ ይሻላሉን? የምድራቸውስ ስፋት ከእናንተ ይበልጣልን? ክፉውን ቀን ለምታርቁ፣ የግፍንም ወንበር ለምታቀርቡ ወዮላችሁ! በዝኆን ጥርስ ባጌጠ ዐልጋ ላይ ለምትተኙ፤ በድንክ ዐልጋችሁ ላይ ለምትዝናኑ፣ ከበጎች መንጋ ጠቦትን፣ ከሠቡትም ጥጃን ለምትበሉ፤ ባልተቃኘ በገና እንደ ዳዊት ለምትዘፍኑ፣ በሙዚቃ መሣሪያ ለመጫወት ለምትሹ፣ በፋጋ የወይን ጠጅ ለምትጠጡ፣ ምርጥ ሽቱም ለምትቀቡ፣ ስለ ዮሴፍ መከራ ግን ለማታዝኑ ወዮላችሁ! ስለዚህ እናንተ በመጀመሪያ በምርኮ ከሚወሰዱት መካከል ናችሁ፤ መፈንጠዛችሁና መዝናናታችሁም ያበቃል። ጌታ እግዚአብሔር “የያዕቆብን ትዕቢት ተጸይፌአለሁ፤ ምሽጎቹንም ጠልቻለሁ፤ ከተማዪቱንና በውስጧ ያለውን ሁሉ፣ አሳልፌ እሰጣለሁ” ሲል በራሱ ምሏል፤ ይላል የሰራዊት አምላክ እግዚአብሔር። በአንድ ቤት ውስጥ ዐሥር ሰዎች ቢቀሩ እነርሱም ይሞታሉ። በድኖቹንም ከቤት አውጥቶ ማቃጠል ያለበት አንድ ዘመድ መጥቶ ተደብቆ ያለውን ሰው፣ “ከአንተ ጋራ የቀረ ሌላ ሰው አለን?” ሲለው፣ እርሱም “የለም” ይለዋል፤ ከዚያም በኋላ፣ “ዝም በል፤ የእግዚአብሔርን ስም መጥራት አይገባንም” ይለዋል። እነሆ፤ እግዚአብሔር ትእዛዝ ሰጥቷልና፤ ታላላቅ ቤቶችን ያወድማቸዋል፤ ትንንሾቹንም ያደቅቃቸዋል። ፈረሶች በጭንጫ ላይ ይሮጣሉን? ሰውስ እዚያ ላይ በበሬ ያርሳልን? እናንተ ግን ፍትሕን ወደ መርዝነት፣ የጽድቅንም ፍሬ ወደ መራራነት ለወጣችሁ። እናንተ ሎዶባርን በማሸነፋችሁ ደስ ያላችሁ፣ “ቃርናይምን በራሳችን ብርታት ይዘናል” የምትሉ። የሰራዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፣ “የእስራኤል ሕዝብ ሆይ፤ እነሆ፤ እኔ ከሐማት መግቢያ እስከ ዓረባ ሸለቆ ድረስ፣ የሚያስጨንቃችሁን ሕዝብ፣ በእናንተ ላይ አስነሣለሁ።”
አሞጽ 6:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በጽዮን ላሉ ዓለመኞች፥ በሰማርያም ተራራ ላይ ተዘልለው ለተቀመጡ፥ የእስራኤልም ቤት ወደ እነርሱ ለመጡባቸው ለአሕዛብ አለቆች ወዮላቸው! ወደ ካልኔ አልፋችሁ ተመልከቱ፥ ከዚያም ወደ ታላቂቱ ሐማት ሂዱ፥ ከዚያም ወደ ፍልስጥኤም ጌት ውረዱ፥ እነርሱ ከእነዚህ መንግሥታት ይሻላሉን? ወይስ ድንበራቸው ከድንበራችሁ ይሰፋልን? ክፉውን ቀን ከእናንተ ለምታርቁ፥ የግፍንም ወንበር ለምታቀርቡ፥ ከዝሆን ጥርስ በተሠራ አልጋ ላይ ለምትተኙ፥ በምንጣፋችሁም ላይ ተደላድላችሁ ለምትቀመጡ፥ ከበጎችም መንጋ ጠቦትን ከጋጥም ውስጥ ጥጃን ለምትበሉ፥ በመሰንቆም ድምፅ ለምትንጫጩ፥ እንደ ዳዊትም የዜማን ዕቃ ለምታዘጋጁ፥ በፋጋ የወይን ጠጅ ለምትጠጡ፥ እጅግ ባማረ ሽቱም ለምትቀቡ፥ ስለ ዮሴፍ መከራ ግን ለማታዝኑ ለእናንተ ወዮላችሁ! ስለዚህ በምርኮ መጀመሪያ ይማረካሉ፥ ተደላድለው ከተቀመጡትም ዘንድ ዘፈን ይርቃል። ጌታ እግዚአብሔር፦ የያዕቆብን ትዕቢት ተጸይፌአለሁ፥ አዳራሾቹንም ጠልቻለሁ፥ ስለዚህ ከተማይቱንና የሚኖርባትን ሁሉ አሳልፌ እሰጣለሁ ብሎ በራሱ ምሎአል፥ ይላል የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር። እንዲህም ይሆናል፥ አሥር ሰዎች በአንድ ቤት ውስጥ ቢቀሩ እነርሱ ይሞታሉ። አጥንቱንም ከቤቱ ያወጡ ዘንድ የሰው ዘመድና አቃጣዩ ባነሡት ጊዜ፥ በቤቱም ውስጥ ያለውን፦ እስከ አሁን ድረስ ገና ሰው በአንተ ዘንድ አለን? ባለው ጊዜ፥ እርሱም፦ ማንም የለም ባለ ጊዜ፥ ያን ጊዜ፦ የእግዚአብሔርን ስም እንጠራ ዘንድ አይገባንምና ዝም በል ይለዋል። እነሆም፥ እግዚአብሔር ያዝዛል፥ ታላቁንም ቤት በማፍረስ፥ ታናሹንም ቤት በመሰባበር ይመታል። ፍርድን ወደ ሐሞት፥ የጽድቅንም ፍሬ ወደ እሬት የለወጣችሁ፥ በከንቱም ነገር ደስ የሚላችሁ፦ በኃይላችን ቀንድ የወሰድን አይደለምን? የምትሉ፥ እናንተ ሆይ፥ በውኑ ፈረሶች በጭንጫ ላይ ይጋልባሉን? ወይስ በሬዎች በዚያ ላይ ያርሳሉን? የእስራኤል ቤት ሆይ፥ እነሆ፥ እኔ ሕዝብን አስነሣባችኋለሁ፥ ይላል የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር፥ እነርሱም ከሐማት መግቢያ ጀምረው እስከ ዓረባ ወንዝ ድረስ ያስጨንቋችኋል።
አሞጽ 6:1-14 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የእስራኤል ሕዝብ ርዳታቸውን ፈልጎ ወደ መሪዎቹ ይመጣል፤ እነርሱ ግን በጽዮን ተዝናንተው ስለሚቀመጡና በሰማርያ ተራራ ላይ ያለ ሥጋት ስለሚኖሩ ለእነዚህ ታዋቂ መሪዎች ወዮላቸው! እስቲ ወደ ካልኔ ከተማ ሄዳችሁ ተመልከቱ፤ ከዚያም አልፋችሁ “ሐማት” ተብላ ወደምትጠራው ታላቂቱ ከተማና የፍልስጥኤማውያን ከተማ ወደሆነችው ወደ ጋት ውረዱ፤ እናንተ ከእነርሱ ትበልጣላችሁን? ግዛታችሁስ ከእነርሱ ግዛት ይበልጣልን? እናንተ “ክፉ ቀን ፈጥኖ አይመጣም” ብላችሁ በማሰብ በአስተዳደራችሁ የግፍን ሥራ ታፋጥናላችሁ። ከዝሆን ጥርስ በተሠሩ አልጋዎች ላይ ትተኛላችሁ፤ ከበግ መንጋ የጠቦት ሥጋ፥ ከከብት መንጋ የጥጃ ሥጋ እየበላችሁ በድንክ አልጋ ላይ ታርፋላችሁ! የሙዚቃ ቃና በመቃኘት በበገና የማይረባ ዘፈን ትዘፍናላችሁ፤ እንደ ዳዊትም ቅኔዎችን በማዘጋጀት በሙዚቃ መሣሪያ ታዜማላችሁ። የወይን ጠጁን በብርሌ ሳይሆን በገምቦ ትጠጣላችሁ፤ ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ ሽቶ ትቀባላችሁ፤ በእስራኤል ሕዝብ ላይ ስለ ደረሰው ጥፋት ግን ፈጽሞ አታዝኑም፤ ይህን ሁሉ ስለምታደርጉ ወዮላችሁ! ስለዚህ ተማርካችሁ በመሄድ እናንተ የመጀመሪያዎቹ ትሆናላችሁ፤ በዚያን ጊዜ የዚያ የቅጥ ያጣ ፈንጠዝያ ኑሮአችሁ ፍጻሜ ይሆናል። የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር “የእስራኤልን ሕዝብ ትዕቢት ጠልቼአለሁ፤ የተዋቡ ቤተ መንግሥቶቻቸውን ተጸይፌአለሁ፤ ከዚህም የተነሣ ከተማይቱንና በእርስዋ የሚኖሩትን ሁሉ ለጠላት አሳልፌ እሰጣለሁ” ሲል በራሱ ምሎአል። ከአንድ ቤተሰብ ዐሥር ሰዎች ቢቀሩ እነርሱም እንኳ ይሞታሉ፤ ከሟቾቹ የአንዱ የቅርብ ዘመድ የሆነና ሥርዓተ ቀብሩን የሚፈጽም ሬሳውን ከቤት አውጥቶ ይወስዳል፤ በዚያን ጊዜ በቤት ውስጥ ያለውን አንድ ሰው ጠርቶ “ከአንተ ጋር የቀረ ሌላ ሰው አለን?” ብሎ ይጠይቀዋል፤ ሰውየውም “ማንም የቀረ የለም!” ብሎ ይመልስለታል፤ ጠያቂውም “የእግዚአብሔርን ስም መጥራት ስለማይገባን ዝም በል!” ይለዋል። በእግዚአብሔር ትእዛዝ ታላላቅ ቤቶች ይፈርሳሉ፤ ታናናሽ ቤቶችም የፍርስራሽ ክምር ይሆናሉ። ፈረሰኛ በቋጥኝ ላይ ሊጋልብ ይችላልን? ገበሬስ በባሕር ላይ በሬ ጠምዶ ማረስ ይችላልን? እናንተ ግን ፍርድን ወደ መርዝ ለወጣችሁ፤ እውነትንም እንደ ሬት መራራ አደረጋችሁ። ሎደባር የምትባለውን ከተማ በማሸነፋችሁ ተደስታችኋል፤ “ቃርናይም የምትባለውንም ከተማ በጒልበታችን ይዘናል” ብላችሁ ትፎክራላችሁ። የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! በእናንተ ላይ የሌላ ሕዝብ ኀይል አስነሣባችኋለሁ፤ እርሱም በሰሜን ከሐማት መግቢያ በር ጀምሮ በደቡብ እስከ አረባ ሸለቆ ድረስ ዘልቆ ያስጨንቃችኋል።”
አሞጽ 6:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በጽዮን ላሉ ዓለመኞች፥ በሰማርያም ተራራ ላይ ተማምነው ለተቀመጡ፥ የእስራኤልም ቤት ወደ እነርሱ ለመጡባቸው ለአሕዛብ አለቆች ወዮላቸው! ወደ ካልኔ እለፉና ተመልከቱ፤ ከዚያም ወደ ታላቂቱ ሐማት ሂዱ፤ ከዚያም ወደ ፍልስጥኤም ጌት ውረዱ፤ እነርሱ ከእነዚህ መንግሥታት ይሻላሉን? ወይስ ድንበራቸው ከድንበራችሁ ይሰፋልን? ክፉውን ቀን ከእናንተ ታርቃላችሁን? የግፍንስ ወንበር ታቀርባላችሁን? ከዝሆን ጥርስ በተሠራ አልጋ ላይ ለምትተኙ፥ በምንጣፋችሁም ላይ ተደላድላችሁ ለምትቀመጡ፥ ከበጎችም መንጋ ጠቦትን ከጋጥም ውስጥ ጥጃን ለምትበሉ፥ በበገናም ድምፅ ለምትንጫጩ፥ እንደ ዳዊትም ለራሳችሁ የዜማን ዕቃ ለምታዘጋጁ፥ በፋጋ የወይን ጠጅ ለምትጠጡ፥ እጅግ ባማረ ቅባትም ለምትቀቡ፥ ስለ ዮሴፍ መከራ ግን ለማታዝኑ ለእናንተ ወዮላችሁ! ስለዚህ በመጀመሪያ ተማርከው ከሚፈልሱት ይሆናሉ፥ እንደ ፈቃዳቸው ከሚሆኑ መካከል ፈንጠዝያ ይርቃል። ጌታ እግዚአብሔር፦ “የያዕቆብን ትዕቢት ተጸይፌአለሁ፥ የንጉሥ ቅጥሮቹንም ጠልቻለሁ፤ ስለዚህ ከተማይቱንና በውስጧ ያለውን ሁሉ አሳልፌ እሰጣለሁ” ብሎ በራሱ ምሎአል፥ ይላል ጌታ የሠራዊት አምላክ። እንዲህም ይሆናል፤ ዐሥር ሰዎች በአንድ ቤት ውስጥ ቢቀሩ እነርሱ ይሞታሉ። የሞተውን ሰው የሚያቃጥለው ዘመዱ አጥንቱን ከቤቱ አንስቶት ባወጣው ጊዜ፥ በቤቱም በውስጠኛው ክፍል ያለውን፦ “በእዚያ እስከ አሁን ድረስ ከአንተ ጋር ሰው አለን?” ይለዋል፥ እርሱም፦ “ማንም የለም” ይላል፤ ያንጊዜ፦ “የጌታን ስም ልንጠራ አይገባንምና ዝም በል” ይለዋል። እነሆም፥ ጌታ ያዝዛል፤ ታላቁንም ቤት በማፍረስ፥ ታናሹንም ቤት በመሰባበር ይመታል። በውኑ ፈረሶች በዓለታም መሬት ላይ ይጋልባሉን? ወይስ ሰው በበሬዎች በዚያ ላይ ሊያርስ ይችላልን? ነገር ግን እናንተ ፍርድን ወደ ሐሞት፥ የጽድቅንም ፍሬ ወደ እሬት ለወጣችሁ፤ በሎዴባር ደስ የሚላችሁ፥ እናንተም፦ “በብርታታችን ቃርናይምን ለራሳችን አልወሰድንምን?” የምትሉ ናችሁ። “የእስራኤል ቤት ሆይ! እነሆ፥ እኔ አሕዛብን አስነሣባችኋለሁ፥” ይላል ጌታ የሠራዊት አምላክ፤ “እነርሱም ከሐማት መግቢያ ጀምረው እስከ ዓረባ ወንዝ ድረስ ያስጨንቋችኋል።”