የእስራኤል ሕዝብ ርዳታቸውን ፈልጎ ወደ መሪዎቹ ይመጣል፤ እነርሱ ግን በጽዮን ተዝናንተው ስለሚቀመጡና በሰማርያ ተራራ ላይ ያለ ሥጋት ስለሚኖሩ ለእነዚህ ታዋቂ መሪዎች ወዮላቸው! እስቲ ወደ ካልኔ ከተማ ሄዳችሁ ተመልከቱ፤ ከዚያም አልፋችሁ “ሐማት” ተብላ ወደምትጠራው ታላቂቱ ከተማና የፍልስጥኤማውያን ከተማ ወደሆነችው ወደ ጋት ውረዱ፤ እናንተ ከእነርሱ ትበልጣላችሁን? ግዛታችሁስ ከእነርሱ ግዛት ይበልጣልን? እናንተ “ክፉ ቀን ፈጥኖ አይመጣም” ብላችሁ በማሰብ በአስተዳደራችሁ የግፍን ሥራ ታፋጥናላችሁ። ከዝሆን ጥርስ በተሠሩ አልጋዎች ላይ ትተኛላችሁ፤ ከበግ መንጋ የጠቦት ሥጋ፥ ከከብት መንጋ የጥጃ ሥጋ እየበላችሁ በድንክ አልጋ ላይ ታርፋላችሁ! የሙዚቃ ቃና በመቃኘት በበገና የማይረባ ዘፈን ትዘፍናላችሁ፤ እንደ ዳዊትም ቅኔዎችን በማዘጋጀት በሙዚቃ መሣሪያ ታዜማላችሁ። የወይን ጠጁን በብርሌ ሳይሆን በገምቦ ትጠጣላችሁ፤ ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ ሽቶ ትቀባላችሁ፤ በእስራኤል ሕዝብ ላይ ስለ ደረሰው ጥፋት ግን ፈጽሞ አታዝኑም፤ ይህን ሁሉ ስለምታደርጉ ወዮላችሁ! ስለዚህ ተማርካችሁ በመሄድ እናንተ የመጀመሪያዎቹ ትሆናላችሁ፤ በዚያን ጊዜ የዚያ የቅጥ ያጣ ፈንጠዝያ ኑሮአችሁ ፍጻሜ ይሆናል። የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር “የእስራኤልን ሕዝብ ትዕቢት ጠልቼአለሁ፤ የተዋቡ ቤተ መንግሥቶቻቸውን ተጸይፌአለሁ፤ ከዚህም የተነሣ ከተማይቱንና በእርስዋ የሚኖሩትን ሁሉ ለጠላት አሳልፌ እሰጣለሁ” ሲል በራሱ ምሎአል። ከአንድ ቤተሰብ ዐሥር ሰዎች ቢቀሩ እነርሱም እንኳ ይሞታሉ፤ ከሟቾቹ የአንዱ የቅርብ ዘመድ የሆነና ሥርዓተ ቀብሩን የሚፈጽም ሬሳውን ከቤት አውጥቶ ይወስዳል፤ በዚያን ጊዜ በቤት ውስጥ ያለውን አንድ ሰው ጠርቶ “ከአንተ ጋር የቀረ ሌላ ሰው አለን?” ብሎ ይጠይቀዋል፤ ሰውየውም “ማንም የቀረ የለም!” ብሎ ይመልስለታል፤ ጠያቂውም “የእግዚአብሔርን ስም መጥራት ስለማይገባን ዝም በል!” ይለዋል። በእግዚአብሔር ትእዛዝ ታላላቅ ቤቶች ይፈርሳሉ፤ ታናናሽ ቤቶችም የፍርስራሽ ክምር ይሆናሉ። ፈረሰኛ በቋጥኝ ላይ ሊጋልብ ይችላልን? ገበሬስ በባሕር ላይ በሬ ጠምዶ ማረስ ይችላልን? እናንተ ግን ፍርድን ወደ መርዝ ለወጣችሁ፤ እውነትንም እንደ ሬት መራራ አደረጋችሁ። ሎደባር የምትባለውን ከተማ በማሸነፋችሁ ተደስታችኋል፤ “ቃርናይም የምትባለውንም ከተማ በጒልበታችን ይዘናል” ብላችሁ ትፎክራላችሁ። የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! በእናንተ ላይ የሌላ ሕዝብ ኀይል አስነሣባችኋለሁ፤ እርሱም በሰሜን ከሐማት መግቢያ በር ጀምሮ በደቡብ እስከ አረባ ሸለቆ ድረስ ዘልቆ ያስጨንቃችኋል።”
ትንቢተ አሞጽ 6 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ አሞጽ 6:1-14
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች