የሐዋርያት ሥራ 24:1-16

የሐዋርያት ሥራ 24:1-16 አማ05

ከአምስት ቀን በኋላ የካህናት አለቃው ሐናንያ ከአንዳንድ ሽማግሌዎችና ጠርጠሉስ ከሚባል ጠበቃ ጋር ወደ ቂሳርያ ሄደ፤ እነርሱም ወደ አገረ ገዥው ወደ ፊልክስ ቀርበው ጳውሎስን ከሰሱ፤ ጳውሎስ ተጠርቶ በመጣ ጊዜ፥ ጠርጠሉስ እንዲህ ሲል ክሱን ጀመረ፤ “ክቡር ፊልክስ ሆይ! በአንተ አማካይነት ብዙ ሰላም አግኝተናል፤ በመልካም አስተዳደርህም ለሕዝባችን መሻሻል ተገኝቶአል፤ እጅግ የተከበርክ ፊልክስ ይህን መልካም አድራጎትህን በየቦታውና በየጊዜው የምንቀበለው ከፍ ባለ ምስጋና ነው። አሁን ግን ጊዜህን ሳላባክን ባጭሩ የምነግርህን በቸርነትህ እንድትሰማን እለምንሃለሁ፤ ይህ ሰው መጥፎ በሽታ ሆኖብናል፤ በዓለም ባሉት አይሁድ ሁሉ ላይ ሁከት ያስነሣል፤ ናዝራውያን ለሚባሉት መሪያቸው ነው። ቤተ መቅደስንም ሊያረክስ ሲሞክር ይዘነዋል፤ [በሕጋችንም መሠረት ልንፈርድበት አስበን ነበር፤ ነገር ግን የጦር አዛዡ ሉስዮስ መጥቶ በታላቅ ኀይል ከእጃችን ነጥቆ ወሰደው። ከሳሾቹም ወደ አንተ እንዲመጡ አዘዘ፤] ይህን በእርሱ ላይ ያቀረብነውን ክስ ሁሉ እውነት መሆኑን አንተ ራስህ እርሱን መርምረህ ልታረጋግጥ ትችላለህ።” አይሁድ “ይህ ሁሉ ነገር እውነት ነው” እያሉ በክሱ ተስማሙ። አገረ ገዥው ፊልክስ በእጁ ጠቅሶ ጳውሎስ እንዲናገር ፈቀደለት፤ ጳውሎስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ለብዙ ዓመቶች የዚህ አገር ገዢ መሆንክን ስለማውቅ ለቀረበብኝ ክስ መከላከያዬን በአንተ ፊት ሳቀርብ በጣም ደስ እያለኝ ነው፤ ለመስገድ ወደ ኢየሩሳሌም ከሄድኩ ከዐሥራ ሁለት ቀን እንደማይበልጥ አንተ ራስህ ማረጋገጥ ትችላለህ፤ በቤተ መቅደስም ሆነ በምኲራብ ወይም በከተማ ውስጥ ከማንም ጋር ስከራከር ወይም ሕዝቡን ለሁከት ሳነሣሣ አላገኙኝም፤ አሁን ላቀረቡብኝ ክስ ሁሉ ምንም ማስረጃ ሊያቀርቡልህ አይችሉም። ነገር ግን ይህን ልገልጥልህ እወዳለሁ፤ እነርሱ አዲስ መንገድ በሚሉት የሃይማኖት ክፍል እምነት የአባቶቻችንን አምላክ አመልካለሁ፤ በሕግና በነቢያት መጻሕፍት የተጻፈውንም ሁሉ አምናለሁ። እነርሱም ተስፋ እንደሚያደርጉት እኔም ጻድቃንና ኃጥአን ከሞት እንደሚነሡ በእግዚአብሔር ተስፋ አደርጋለሁ። ስለዚህ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ንጹሕ ኅሊና እንዲኖረኝ ዘወትር እተጋለሁ።