1ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 11
11
በእስራኤል ላይ ዳዊት መንገሡ
1እስራኤልም ሁሉ በኬብሮን ወደ ዳዊት ተሰብስበው እንዲህ አሉት፦ “እነሆ፥ እኛ የአጥንትህ ፍላጭ የሥጋህ ቁራጭ ነን፤ 2አስቀድሞ ሳኦል ንጉሥ ሆኖ ሳለ እስራኤልን የምታወጣና የምታገባ አንተ ነበርህ፤ ጌታ አምላክህም፦ ‘ሕዝቤን እስራኤልን አንተ ትጠብቃለህ፤ በሕዝቤም በእስራኤል ላይ አለቃ ትሆናለህ’ ብሎህ ነበር።” 3የእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ ወደ ንጉሡ ወደ ኬብሮን መጡ፤ ዳዊትም በኬብሮን በጌታ ፊት ቃል ኪዳን ከእነርሱ ጋር አደረገ፤ በሳሙኤልም አንደበት እንደ ተናገረው እንደ ጌታ ቃል በእስራኤል ላይ ንጉሥ እንዲሆን ዳዊትን ቀቡት።
ኢየሩሳሌም መያዝዋ
4 #
ኢያ. 15፥63፤ መሳ. 1፥21። ዳዊትም እስራኤልም ሁሉ ኢያቡስ ወደምትባል ወደ ኢየሩሳሌም ሄዱ፤ በአገሩም የተቀመጡ ኢያቡሳውያን በዚያ ነበሩ። 5በኢያቡስም የተቀመጡ ዳዊትን፦ “ወደዚህ አትገባም” አሉት፤ ዳዊት ግን አምባይቱን ጽዮንን ያዘ፤ እርሷም የዳዊት ከተማ ናት። 6ዳዊትም፦ “ኢያቡሳውያንን አስቀድሞ የሚመታ ሰው አለቃና መኮንን ይሆናል” አለ። የጽሩያም ልጅ ኢዮአብ አስቀድሞ ወጣ አለቃም ሆነ። 7ዳዊትም በአምባይቱ ውስጥ ተቀመጠ፤ ስለዚህም የዳዊት ከተማ ብለው ጠሩአት።
8ከሚሎም ጀምሮ በዙሪያው ከተማ ሠራ፤ ኢዮአብም የቀረውን ከተማ አደሰ። 9ዳዊትም የሠራዊት ጌታ ከእርሱ ጋር ነበረና እየበረታ ሄደ።
የንጉሥ ዳዊት ኃያላን ሰዎችና ተገዢዎቻቸው
10ለዳዊትም የነበሩት የኃያላን አለቆች እነዚህ ናቸው፤ ስለ እስራኤል እንደ ተናገረው እንደ ጌታ ቃል ሊያነግሡት ከእስራኤል ሁሉ ጋር በመንግሥቱ ላይ አጸኑት። 11የዳዊትም ኃያላን ቍጥር ይህ ነበረ፤ የሦስቱ ኃያላን አለቃ የሐክሞናዊው ልጅ ያሾብዓም ነበረ፤ እርሱ ጦሩን አንሥቶ ሦስት መቶ ሰው በአንድ ጊዜ ገደለ። 12ከእርሱም በኋላ በሦስቱ ኃያላን መካከል የነበረ የአሆሃዊው የዱዲ ልጅ አልዓዛር ነበረ። 13እርሱ ከዳዊት ጋር በፈስደሚም ነበረ፥ በዚያም ገብስ በሞላበት እርሻ ውስጥ ፍልስጥኤማውያን ለውጊያ ተሰብስበው ነበር፤ ሕዝቡም ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ። 14እርሱና ዳዊት በእርሻውም መካከል ጸንተው ቆሙ፤ ስፍራውንም አላስደፈሩም፥ ፍልስጥኤማውያንንም ገደሉ፤ ጌታም በታላቅ ድል አድራጊነት አዳናቸው።
15ከሠላሳውም አለቆች ሦስቱ ወርደው ዳዊት ወዳለበት ወደ ዓለቱ ወደ ዓዶላም ዋሻ መጡ፤ የፍልስጥኤማውያንም ሠራዊት በራፋይም ሸለቆ ሰፍሮ ነበር። 16በዚያም ጊዜ ዳዊት በምሽጉ ውስጥ ነበረ፤ የፍልስጥኤማውያንም ጭፍራ በቤተልሔም ነበረ። 17ዳዊትም፦ “በበሩ አጠገብ ካለችው ከቤተልሔም ምንጭ ውኃ ማን ይሰጠኛል?” ብሎ ተመኘ። 18እነዚህም ሦስቱ የፍልስጥኤማውያንን ሠራዊት በመካከላቸው ጥሰው አለፉ፥ በበሩም አጠገብ ካለችው ከቤተልሔም ምንጭ ውኃ ቀዱ፤ ይዘውም ለዳዊት አመጡለት። እርሱ ግን ሊጠጣ አልፈለገም፥ ነገር ግን ለጌታ እንደ መባ አፈሰሰው፤ 19እርሱም እንዲህ አለ፦ “ይህን እንዳደርግ አምላኬ አይፈቅድልኝም፤ በነፍሳቸው የደፈሩትን የእነዚህን ሰዎች ደም እጠጣለሁን? ነፍሳቸውን አደጋ ላይ ጥለው አምጥተውታል።” ስለዚህም ሊጠጣው አልፈለገም። ሦስቱም ኃያላን ያደረጉት ይህ ነው።
20የኢዮአብም ወንድም አቢሳ የሦስቱ አለቃ ነበረ፤ ጦሩንም በሦስት መቶ ላይ አንሥቶ ገደላቸው፥ በሦስቱም መካከል ስሙ የተጠራ ነበረ። 21በሁለተኛውም ተራ በሆኑት በሦስቱ መካከል የከበረ ነበረ፥ አለቃቸውም ሆነ፤ ነገር ግን ወደ ፊተኞቹ ወደ ሦስቱ ደረጃ አልደረሰም ነበር።
22በቀብስኤልም የነበረው፥ ታላቅ ሥራ ያደረገው የጽኑዕ ሰው የዮዳሄ ልጅ በናያስ የሞዓባዊን የአሪኤልን ሁለቱን ልጆች ገደለ፤ በአመዳይም ወራት ወርዶ በጉድጓድ ውስጥ አንበሳ ገደለ። 23ቁመቱም አምስት ክንድ የነበረውን ረጅሙን ግብጻዊውን ሰው ገደለ፤ በግብጻዊውም እጅ የሸማኔ መጠቅለያ የመሰለ ጦር ነበረ፤ እርሱ ግን በትር ይዞ ወደ እርሱ ወረደ፥ ከግብፃዊው እጅ ጦሩን ነጠቀው፥ በገዛ ጦሩም ገደለው። 24የዮዳሄ ልጅ በናያስ ያደረገው ይህ ነው፤ ስሙም በሦስቱ ኃያላን መካከል የተጠራ ነበረ። 25እነሆ፥ ከሠላሳው ይልቅ የከበረ ነበረ፥ ነገር ግን ወደ ፊተኞቹ ወደ ሦስቱ አልደረሰም። ዳዊትም በዘበኞቹ ላይ ሾመው።
26ደግሞም በሠራዊቱ ዘንድ የነበሩት ኃያላን እነዚህ ናቸው፤ የኢዮአብ ወንድም አሣሄል፥ የቤተልሔሙ ሰው የዱዲ ልጅ ኤልያናን፥ 27ሃሮራዊው ሳሞት፥ ፈሎናዊው ሴሌስ፥ 28የቴቁሔ ሰው የዒስካ ልጅ ዒራስ፥ ዓናቶታዊው አቢዔዜር፥ 29ኩሳታዊው ሴቤካይ፥ አሆሃዊው ዔላይ፥ 30ነጦፋዊው ኖኤሬ፥ የነጦፋዊው የበዓና ልጅ ሔሌድ፥ 31ከብንያም ወገን ከጊብዓ የሪባይ ልጅ ኤታይ፥ ጲርዓቶናዊው በናያስ፥ 32የገዓስ ወንዝ ሰው ኡሪ፥ ዓረባዊው አቢኤል፥ 33ባሕሩማዊው ዓዝሞት፥ ሰዓልቦናዊው ኤሊያሕባ፥ 34የጊዞናዊው የአሳን ልጆች፥ የሃራራዊው የሻጌ ልጅ ዮናታን፥ 35የአሮዳዊው የአራር ልጅ አምናን፥ የኡር ልጅ ኤሊፋል፥ 36ምኬራታዊው ኦፌር፥ ፍሎናዊው አኪያ፥ 37ቀርሜሎሳዊው ሐጽሮ፥ የኤዝባይ ልጅ ነዕራይ፥ 38የናታንም ወንድም ኢዮኤል፥ የሃግሪ ልጅ ሚብሐር፥ 39አሞናዊው ጼሌቅ፥ የጽሩያ ልጅ የኢዮአብ ጋሻ ጃግሬ ቤሮታዊው ነሃራይ፥ 40ይትራዊው ዒራስ፥ ይትራዊው ጋሬብ፥ 41ኬጢያዊው ኦርዮ፥ የአሕላይ ልጅ ዛባድ፥ 42የሮቤላዊው የሺዛ ልጅ ዓዲና፥ እርሱ የሮቤላውያን አለቃ ነበረ፥ ከእርሱም ጋር ሠላሳ ሰዎች ነበሩ፥ 43የማዕካ ልጅ ሐናን፥ ሚትናዊው ኢዮሣፍጥ፥ 44አስታሮታዊው ዖዝያ፥ የአሮዔራዊው የኮታም ልጆች ሻማና ይዒኤል፥ 45የሺምሪ ልጅ ይዲኤል፥ ወንድሙም ቲዳዊው ዮሐ፥ 46መሐዋዊው ኤሊኤል፥ ይሪባይ፥ ዮሻውያ፥ የኤልነዓም ልጆች፥ ሞዓባዊው ይትማ፥ 47ኤሊኤል፥ ዖቤድ፥ ምጾባዊው የዕሢኤል ነበሩ።
Currently Selected:
1ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 11: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ