1ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 12
12
ዳዊትን በምድረ በዳ የተከተሉት ሰዎች
1በጺቅላግም ከቂስ ልጅ ከሳኦል በተሸሸገ ጊዜ ወደ ዳዊት የመጡ እነዚህ ናቸው፤ በጦርነትም ካገዙት ኃያላን መካከል ነበሩ። 2ቀስተኞችም ነበሩ፥ በቀኝና በግራም እጃቸው ድንጋይ ሊወነጭፉ ፍላጻም ሊወረውሩ ይችሉ ነበር፤ ከብንያም ወገን የሳኦል ወንድሞች ነበሩ። 3አለቃቸው አሒዔዝር ነበረ፥ ከእርሱም በኋላ ኢዮአስ፥ ሁለቱም የጊብዓዊው የሸማዓ ልጆች ነበሩ፤ እንዲሁም ይዝኤል፥ ፋሌጥ፥ የዓዝሞት ልጆች ነበሩ፤ በራኪያ፥ ዓናቶታዊው ኢዩ፥ 4ገባዖናዊው ሰማያስ፥ እርሱ በሠላሳው መካከልና በሠላሳው ላይ ኃያል ሰው ነበረ፤ ኤርምያስ፥ የሕዚኤል፥ ዮሐናን፥ ገድሮታዊው ዮዛባት፥ 5ኤሉዛይ፥ ኢያሪሙት፥ በዓልያ፥ ሰማራያ፥ ሐሩፋዊው ሰፋጥያስ፥ 6ቆሬያውያን ሕልቃና፥ ይሺያ፥ ዓዘርኤል፥ ዮዛር፥ ያሾብዓም ነበሩ፤ 7የጌዶር ሰው የይሮሐም ልጆች ዮዔላ፥ ዝባድያ ነበሩ።
8ዳዊትም በምድረ በዳ ውስጥ ባለችው በአምባይቱ ሳለ ከጋድ ወገን የሆኑ እነዚህ በጋሻና በጦር ስልታቸው የተካኑ፥ ጽኑዓን ኃያላን፥ ተዋጊዎች፥ ወደ እርሱ መጡ፤ ፊታቸውም እንደ አንበሳ ፊት ነበረ፥ በተራራም ላይ እንደሚዘልል ሚዳቋ ፈጣኖች ነበሩ። 9አለቃው ዔጼር፥ ሁለተኛው አብድዩ፥ ሦስተኛው ኤልያብ፥ 10አራተኛው መስመና፥ አምስተኛው ኤርምያስ፥ 11ስድስተኛው ዓታይ፥ ሰባተኛው ኤሊኤል፥ 12ስምንተኛው ዮሐናን፥ ዘጠኝኛው ኤልዛባድ፥ 13አሥረኛው ኤርምያስ፥ ዐሥራ አንደኛው መክበናይ ነበሩ። 14እነዚህ የጋድ ልጆች የሠራዊቱ አለቆች ነበሩ፤ ከእነርሱም ታናሹ የመቶ አለቃ፥ ታላቁ የሺህ ማዕርግ ያላቸው ነበሩ። 15በመጀመሪያው ወር ዮርዳኖስ ከዳር እስከ ዳር ሞልቶ በነበረ ጊዜ የተሻገሩት እነዚህ ናቸው፤ በሸለቆውም ውስጥ በምሥራቅና በምዕራብ በኩል የተቀመጡትን ሁሉ አባረሩ።
16ዳዊትም ወደ ነበረባት ወደ አምባይቱ ከብንያምና ከይሁዳ ወገን ሰዎች መጡ። 17ዳዊትም ሊገናኛቸው ወጣ እነርሱንም እንዲህ አላቸው፦ “እኔን ለመርዳት በሰላም ወደ እኔ መጥታችሁ እንደሆነ ልቤ ከእንናተ ጋር አንድ ይሆናል፤ ለጠላቶቼ አሳልፋችሁ ልትሰጡኝ መጥታችሁ እንደሆነ ግን፥ በእጄ ዓመጽ የለብኝምና የአባቶቻችን አምላክ ይመልከት፤ ፍርድም ይስጥ።” 18መንፈስም በሠላሳው አለቃ በዓማሣይ ላይ ወረደ፥ እርሱም እንዲህ አለ፦ “ዳዊት ሆይ! እኛ የአንተ ነን፤ የእሴይ ልጅ ሆይ! እኛ ከአንተ ጋር ነን፤ አምላክህ ይረዳሃልና ሰላም ሰላም ለአንተ ይሁን፥ ለሚረዱህም ሰላም ይሁን።” ዳዊትም ተቀበላቸው፥ የጭፍራም አለቆች አደረጋቸው።
19ዳዊትም ከፍልስጥኤማውያን ጋር ሳኦልን ሊወጋ በመጣ ጊዜ ከምናሴ ወገን ሰዎች ወደ ዳዊት ከዱ፤ የፍልስጥኤማውያን አለቆች ግን፦ “በራሳችን ላይ ጉዳት አምጥቶ ወደ ጌታው ወደ ሳኦል ይመለሳል” ሲሉ ተማክረው እንዲመለስ አድርገውታልና እርሱ አልረዱአቸውም። 20ወደ ጺቅላግም ሲሄድ ከምናሴ ወገን የምናሴ ሻለቆች የነበሩ ዓድና፥ ዮዛባት፥ ይዲኤል፥ ሚካኤል፥ ዮዛባት፥ ኤሊሁ፥ ጺልታይ ወደ እርሱ ከዱ። 21ሁሉም ጽኑዓን ኃያላንና በሠራዊቱ ላይ አለቆች ነበሩና በአደጋ ጣዮቹ ጭፍሮች ላይ ዳዊትን አገዙት። 22እንደ እግዚአብሔርም ሠራዊት ታላቅ ሠራዊት እስኪሆን ድረስ ዳዊትን ለመርዳት ዕለት ዕለት ይመጡ ነበር።
የዳዊት ሠራዊት በኬብሮን
23እንደ ጌታም ቃል የሳኦልን መንግሥት ወደ እርሱ ለመመለስ በኬብሮን ሳለ ወደ ዳዊት የመጡት የሠራዊቱ አለቆች ቍጥር ይህ ነው። 24ጋሻና ጦር ተሸክመው ለውግያ የተዘጋጁ የይሁዳ ልጆች ስድስት ሺህ ስምንት መቶ ነበሩ። 25ለውግያ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች የነበሩ የስምዖን ልጆች ሰባት ሺህ አንድ መቶ ነበሩ። 26የሌዊ ልጆች አራት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ። 27የአሮንም ቤት አለቃ ዮዳሄ ነበረ፥ ከእርሱም ጋር ሦስት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ፤ 28ከእርሱም ጋር ጽኑዕ ኃያል ጎልማሳ ሳዶቅ ነበረ፥ ከአባቱም ቤት ሀያ ሁለት የጦር አዛዦች ነበሩ። 29የሳኦልም ወንድሞች ከሆኑ ከብንያም ልጆች የሚበልጠው ክፍል እስከዚያ ዘመን ድረስ የሳኦልን ቤት ይከተል ነበርና ከእነርሱ ዘንድ የመጡ ሦስት ሺህ ነበሩ። 30ጽኑዓን ኃያልን የሆኑ በአባቶቻቸውም ቤት የታወቁ የኤፍሬም ልጆች ሀያ ሺህ ስምንት መቶ ነበሩ። 31በየስማቸውም የተጻፉ ዳዊትን ለማንገሥ የመጡ የምናሴ ነገድ እኩሌታ ዐሥራ ስምንት ሺህ ነበሩ። 32እስራኤልም የሚገባውን እንዲፈጽም የዘመኑን ሁኔታ የሚያውቁ ጥበበኞች ሰዎች የይሳኮር ልጆች አለቆች ሁለት መቶ ነበሩ፤ ወንድሞቻቸውም ሁሉ ይታዘዙአቸው ነበር። 33በጽኑ የሠለጠኑ ተዋጊዎች ለውግያም የተዘጋጁ፥ የማያመነቱ፥ ሁሉንም ዓይነት የጦር መሣሪያ የታጠቁ የዛብሎን ሰዎች ኀምሳ ሺህ ነበሩ። 34የንፍታሌምም አለቆች አንድ ሺህ ነበሩ፥ ከእነርሱም ጋር ጋሻና ጦር የታጠቁ ሠላሳ ሰባት ሺህ ነበሩ። 35ለውጊያም የተዘጋጁ የዳን ሰዎች ሀያ ስምንት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ። 36በጽኑ የሠለጠኑ ተዋጊዎች፥ ለውጊያም የተዘጋጁ የአሴር ሰዎች አርባ ሺህ ነበሩ። 37በዮርዳኖስም ማዶ ካሉ ከሮቤልና ከጋድ ሰዎች ከምናሴም ነገድ እኩሌታ ሁሉንም ዓይነት የጦር መሣሪያ ታጥቀው የመጡ መቶ ሀያ ሺህ ነበሩ።
38እነዚህ ሁሉ ተዋጊዎች በሰልፍ ዳዊትን በእስራኤል ሁሉ ላይ ለማንገሥ በፍጹም ልባቸው ወደ ኬብሮን መጡ፤ ደግሞም ከእስራኤል የቀሩት ሁሉ ዳዊትን ለማንገሥ በአንድ ልብ ነበሩ። 39ወንድሞቻቸውም አዘጋጅተውላቸው ነበርና እየበሉና እየጠጡ በዚያ ከዳዊት ጋር ሦስት ቀን ተቀመጡ። 40ደግሞም በእስራኤል ዘንድ ደስታ ሆኖአልና ከይሳኮርና ከዛብሎን ከንፍታሌምም ድረስ በእርሱ አቅራቢያ የነበሩ በአህያና በግመል በበቅሎና በበሬ ላይ እንጀራ ዱቄት የበለስ ጥፍጥፍና የዘቢብ ዘለላ የወይንም ጠጅ ዘይትም በሬዎችንና በጎችንም በብዛት ያመጡ ነበር።
Currently Selected:
1ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 12: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ