1ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 10

10
ሳኦልና ልጆቹ መሞታቸው
1ፍልስጥኤማውያንም ከእስራኤል ጋር ተዋጉ፤ የእስራኤልም ሰዎች ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፥ ተወግተውም በጊልቦዓ ተራራ ላይ ወደቁ። 2ፍልስጥኤማውያንም ሳኦልንና ልጆቹን ተከታትለው አባረሩአቸው፤ የፍስጥኤማውያንም የሳኦልን ልጆች ዮናታንንና አሚናዳብን ሜልኪሳንም ገደሉ። 3ውጊያውም በሳኦል ላይ ጠነከረ፥ ቀስተኞችም አገኙት፤ እነርሱም አቈሰሉት። 4ሳኦልም ጋሻ ጃግሬውን፦ “እነዚህ ቈላፋን#10፥4 ያልተገረዙ፤ መጥተው እንዳይዘብቱብኝ ሰይፍህን መዝዘህ ውጋኝ” አለው። ጋሻ ጃግሬው ግን እጅግ ፈርቶ ነበርና እንቢ አለ። ሳኦልም ሰይፉን ወስዶ በላዩ ወደቀ። 5ጋሻ ጃግሬውም ሳኦል እንደ ሞተ ባየ ጊዜ እርሱ ደግሞ በሰይፉ ላይ ወድቆ ሞተ። 6ሳኦልና ሦስቱም ልጆቹ የቤቱም ሰዎች ሁሉ በአንድ ላይ ሞቱ።
7በሸለቆውም የነበሩት የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ሠራዊቱ እንደ ሸሸ፥ ሳኦልና ልጆቹም እንደሞቱ ባዩ ጊዜ ከተሞቻቸውን ለቅቀው ሸሹ፤ ፍልስጥኤማውያንም መጥተው ተቀመጡባቸው። 8በማግስቱም ፍልስጥኤማውያን የሞቱትን ለመግፈፍ በመጡ ጊዜ ሳኦልንና ልጆቹን በጊልቦዓ ተራራ ላይ ወድቀው አገኙአቸው። 9ገፈፉትም፥ ራሱንና መሣሪያውንም አንሥተው ለጣዖቶቻቸውና ለሕዝቡ የምሥራች እንዲናገሩ ወደ ፍልስጥኤማውያን አገር ዙሪያ መልእክተኞችን ላኩ። 10መሣሪያውንም በአምላኮቻቸው ቤት ውስጥ አኖሩ፤ ራሱንም በዳጎን ቤት ውስጥ ቸነከሩት። 11የኢያቢስ-ገለዓድም ሰዎች ሁሉ ፍልስጥኤማውያን በሳኦል ላይ ያደረጉትን ሁሉ በሰሙ ጊዜ፥ 12ጽኑዓን ሰዎች ሁሉ ተነሥተው የሳኦልን ሬሳ የልጆቹንም ሬሳ ወሰዱ፥ ወደ ኢያቢስም አመጡአቸው፤ በኢያቢስም ካለው ከባሉጥ ዛፍ በታች አጥንቶቻቸውን ቀበሩ፥ ሰባት ቀንም ጾሙ።
13 # 1ሳሙ. 13፥8-14፤ 15፥1-24፤ ዘሌ. 19፥31፤ 20፥6፤ 1ሳሙ. 28፥7፤8። እንዲሁ ሳኦል በጌታ ላይ ስላደረገው ኃጢአት፥ የጌታንም ቃል ስላልጠበቀ ሞተ። ደግሞም መናፍስት ጠሪ ስለ ጠየቀ፥ 14ጌታንም ስላልጠየቀ፥ ስለዚህ ገደለው፥ መንግሥቱንም ወደ እሴይ ልጅ ወደ ዳዊት አስተላለፈ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ