ትንቢተ ዘካርያስ 14:16-21

ትንቢተ ዘካርያስ 14:16-21 አማ05

ከዚያም በኋላ ኢየሩሳሌምን ከወጉአት መንግሥታት መካከል ከጥፋት የተረፉት ለንጉሡ ለሠራዊት አምላክ ሊሰግዱለትና የዳስ በዓልንም ለማክበር በየዓመቱ ወደ ኢየሩሳሌም ይወጣሉ። ለንጉሡ ለሠራዊት አምላክ የማይሰግዱለት ሕዝቦች ቢኖሩ በምድራቸው ዝናብ አይዘንብላቸውም። ግብጻውያንም በዓሉን ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም ወጥተው በእግዚአብሔር ፊት መቅረብ ባይፈልጉ፥ “ወደ ኢየሩሳሌም ወጥተን የዳስ በዓል አናከብርም” በሚሉ መንግሥታት ላይ የሚደርሰው ቀሣፊ በሽታ ይመጣባቸዋል። ግብጻውያንም ሆኑ ሌሎች መንግሥታት “የዳስ በዓል አናከብርም” ቢሉ የሚደርስባቸው ቅጣት ይህ ነው። በዚያን ጊዜ በፈረሶች አንገት ላይ በሚንጠለጠል ቃጭል ሁሉ ላይ “ለእግዚአብሔር የተለየ” የሚል የጽሕፈት ምልክት ይቀረጽበታል፤ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ያለው የማብሰያ ማሰሮ በመሠዊያው ላይ እንደሚገኘው ሳሕን የተቀደሰ ይሆናል። በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ምድር የሚገኘው ማሰሮ ሁሉ ለሠራዊት አምላክ የተለየ ይሆናል፤ መሥዋዕት የሚያቀርቡ ሰዎች ሁሉ በማሰሮዎቹ ጥቂቱን የመሥዋዕቱን ሥጋ ያበስሉባቸዋል፤ በዚያን ጊዜ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር መቅደስ ውስጥ የሚነግድ ማንም ሰው አይኖርም።