ዘካርያስ 14:16-21

ዘካርያስ 14:16-21 NASV

ከዚያም ኢየሩሳሌምን ከወጓት አሕዛብ ከሞት የተረፉት ሁሉ ለንጉሡ፣ ለሰራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር ለመስገድና የዳስን በዓል ለማክበር በየዓመቱ ይወጣሉ። የምድር ሕዝብ ሁሉ ለንጉሡ፣ ለሰራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር ሊሰግዱ ወደ ኢየሩሳሌም የማይወጡ ከሆነ ዝናብ አያገኙም። የግብጽም ሰዎች ወደዚያ ሳይወጡ ቢቀሩ፣ ዝናብ አያገኙም፤ እግዚአብሔር ወጥተው የዳስ በዓልን በማያከብሩ አሕዛብ ላይ የሚያደርሰውን መቅሠፍት በእነርሱም ላይ ያመጣል። የዳስን በዓል ወጥተው ለማያከብሩ ግብጻውያንና አሕዛብ ሁሉ የተወሰነው ቅጣት ይህ ነው። በዚያ ቀን በፈረሶች ሻኵራ ላይ፣ “ቅዱስ ለእግዚአብሔር” የሚል ጽሑፍ ይቀረጻል፤ በእግዚአብሔር ቤት ያሉ የማብሰያ ምንቸቶች ከመሠዊያው ፊት ለፊት እንዳሉ ሳሕኖች የተቀደሱ ይሆናሉ። በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ያሉ ምንቸቶች ሁሉ ለሰራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር የተቀደሱ ይሆናሉ፤ መሥዋዕት ለማቅረብ የሚመጡ ሁሉ ምንቸቶቹን በመውሰድ ያበስሉባቸዋል፤ በዚያ ቀን በእግዚአብሔር ጸባኦት ቤት ከእንግዲህ ወዲያ ከነዓናዊ አይገኝም።