የማቴዎስ ወንጌል 8:1-12

የማቴዎስ ወንጌል 8:1-12 አማ05

ኢየሱስ ከተራራው በወረደ ጊዜ፥ እጅግ ብዙ ሰዎች ተከተሉት። በዚህ ጊዜ አንድ ለምጻም ሰው መጥቶ ሰገደለትና “ጌታ ሆይ! ብትፈቅድስ ልታነጻኝ ትችላለህ” አለ። ኢየሱስም እጁን ዘርግቶ ዳሰሰውና “ፈቅጃለሁ፤ ንጻ!” አለው። ለምጻሙም ወዲያውኑ ከለምጹ ነጻ። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ፥ ከለምጹ የዳነውን ሰው እንዲህ አለው፤ “ይህን ነገር ለማንም አትናገር፤ ነገር ግን ሄደህ መዳንህን ለካህን አሳይ፤ ምስክር ይሆንባቸው ዘንድ፥ ስለ መዳንህ ሙሴ ያዘዘውን መባ ለእግዚአብሔር አቅርብ” አለው። ኢየሱስ ወደ ቅፍርናሆም ከተማ በገባ ጊዜ፥ አንድ ሮማዊ የመቶ አለቃ ወደ እርሱ ቀርቦ በመለመን፥ “ጌታ ሆይ፥ አገልጋዬ ሽባ ሆኖ፥ እጅግ በመሠቃየት በቤት ተኝቶአል” አለው። ኢየሱስም “እኔ መጥቼ እፈውሰዋለሁ” አለው። የመቶ አለቃው ግን እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ጌታ ሆይ! አንተ ወደ ቤቴ እንድትገባ እኔ የተገባሁ ሰው አይደለሁም፤ ነገር ግን አንዲት ቃል ብቻ ተናገር፤ አገልጋዬም ይድናል። እኔ ራሴ ለባለ ሥልጣኖች ታዛዥ ስሆን፥ ከእኔ በታች የማዛቸው ወታደሮች አሉኝ፤ ከእነርሱ አንዱን ‘ሂድ!’ ስለው ይሄዳል፤ ሌላውንም ‘ና!’ ስለው ይመጣል፤ አገልጋዬም ‘ይህን አድርግ!’ ስለው ያደርጋል።” ኢየሱስ ይህን በሰማ ጊዜ ተደነቀ፤ ይከተሉት የነበሩትን ሰዎች እንዲህ አላቸው፤ “በእውነት እላችኋለሁ፤ ይህን የሚያኽል ትልቅ እምነት ያለው አንድም ሰው በእስራኤል ስንኳ አላገኘሁም። ብዙዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ፤ ከአብርሃም፥ ከይስሐቅ፥ ከያዕቆብ ጋር በመንግሥተ ሰማይ በማዕድ ይቀመጣሉ እላችኋለሁ። የዚህ መንግሥት ወራሾች መሆን ይገባቸው የነበሩት ግን ውጪ ወደ አለው ጨለማ ይጣላሉ። በዚያም ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።”

ተዛማጅ ቪዲዮዎች