የማቴዎስ ወንጌል 4:18-25

የማቴዎስ ወንጌል 4:18-25 አማ05

ኢየሱስ በገሊላ ባሕር አጠገብ ሲያልፍ፥ ዓሣ አጥማጆች የነበሩትን ሁለት ወንድማማች እነርሱም ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንንና ወንድሙን እንድርያስን፥ መረባቸውን ወደ ባሕር ሲጥሉ አየ። ኢየሱስም “ኑ ተከተሉኝ፤ ዓሣን እንደምታጠምዱ ሁሉ ሰዎችን እንድትሰበስቡልኝ አደርጋችኋለሁ” አላቸው። እነርሱም ወዲያውኑ መረባቸውን ትተው ተከተሉት። ከዚያም እልፍ ብሎ፥ የዘብዴዎስ ልጆች የሆኑትን ሌሎች ሁለት ወንድማማች ያዕቆብንና ዮሐንስን አየ። እነርሱም ከአባታቸው ከዘብዴዎስ ጋር በጀልባ ላይ ሆነው መረባቸውን ሲጠግኑ ሳለ ጠራቸው። እነርሱም ወዲያውኑ ጀልባዋንና አባታቸውን ትተው ተከተሉት። ኢየሱስም በምኲራቦቻቸው እያስተማረና የእግዚአብሔርን መንግሥት የምሥራች ቃል እየሰበከ፥ በልዩ ልዩ በሽታና ደዌ የተያዙትንም ሰዎች እየፈወሰ በገሊላ ምድር ሁሉ ይዘዋወር ነበር። ዝናው በሶርያ አገር ሁሉ ስለ ተሰማ፥ ሰዎች በልዩ ልዩ በሽታና ደዌ የሚሠቃዩትን፥ ርኩሳን መናፍስት ያደሩባቸውን፥ የሚጥል በሽታ ያለባቸውንና ሽባዎችንም ሁሉ ወደ እርሱ አመጡ፤ እርሱም ፈወሳቸው። ከገሊላ ምድርና ከዐሥሩ ከተሞች ከኢየሩሳሌምና ከይሁዳ፥ ከዮርዳኖስም ወንዝ ማዶ የመጡ ብዙ ሰዎች ኢየሱስን ተከተሉት።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች