ማቴዎስ 4:18-25
ማቴዎስ 4:18-25 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በገሊላ ባሕር አጠገብ ሲመላለስም ሁለት ወንድማማች ጴጥሮስ የሚሉትን ስምዖንን ወንድሙንም እንድርያስን መረባቸውን ወደ ባሕር ሲጥሉ አየ፤ ዓሣ አጥማጆች ነበሩና። እርሱም “በኋላዬ ኑ፤ ሰዎችንም አጥማጆች እንድትሆኑ አደርጋችኋለሁ” አላቸው። ወዲያውም መረባቸውን ትተው ተከተሉት። ከዚያም እልፍ ብሎ ሌሎችን ሁለት ወንድማማች የዘብዴዎስን ልጅ ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ከአባታቸው ከዘብዴዎስ ጋር በታንኳ መረባቸውን ሲያበጁ አየ፤ ጠራቸውም። እነርሱም ወዲያው ታንኳይቱንና አባታቸውን ትተው ተከተሉት። ኢየሱስም በምኩራቦቻቸው እያስተማረ የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ በሕዝብም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ በገሊላ ሁሉ ይዞር ነበር። ዝናውም ወደ ሶርያ ሁሉ ወጣ፤ በልዩ ልዩ ደዌና ሥቃይም ተይዘው የታመሙትን ሁሉ አጋንንትም ያደሩባቸውን በጨረቃም የሚነሣባቸውን ሽባዎችንም ወደ እርሱ አመጡ፤ ፈወሳቸውም። ከገሊላም ከዐሥሩ ከተማም ከኢየሩሳሌምም ከይሁዳም ከዮርዳኖስም ማዶ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት።
ማቴዎስ 4:18-25 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኢየሱስ በገሊላ ባሕር አጠገብ ሲያልፍ፣ ሁለት ወንድማማቾች ማለትም፣ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንንና ወንድሙን እንድርያስን አያቸው። ዓሣ አጥማጆች ነበሩና መረባቸውን ወደ ባሕሩ ይጥሉ ነበር። ኢየሱስም፣ “ኑ፣ ተከተሉኝ፤ ሰዎችን አጥማጆች አደርጋችኋለሁ” አላቸው። ወዲያው መረባቸውን ትተው ተከተሉት። ዐለፍ እንዳለም፣ ሌሎች ሁለት ወንድማማቾች፣ የዘብዴዎስን ልጅ ያዕቆብንና ወንድሙን ዮሐንስን አየ። ከአባታቸው ከዘብዴዎስ ጋራ በጀልባ ሆነው መረባቸውን ያበጁ ነበር። ኢየሱስም ጠራቸው፤ ወዲያውኑ ጀልባቸውንም ሆነ አባታቸውን ትተው ተከተሉት። ኢየሱስም በምኵራቦቻቸው እያስተማረ፣ የእግዚአብሔርን መንግሥት የምሥራች ቃል እየሰበከ፣ በሕዝቡ መካከል ማንኛውንም ደዌና ሕመም እየፈወሰ በመላው ገሊላ ይዘዋወር ነበር። ከዚህም የተነሣ ዝናው በመላዋ ሶርያ ተሰማ፤ ሕዝቡም በተለያዩ በሽታዎች የታመሙትን፣ በክፉ ደዌ የሚሠቃዩትን፣ አጋንንት ያደሩባቸውን፣ የሚጥል በሽታ ያለባቸውን፣ ሽባዎችን ሁሉ ወደ እርሱ አመጡ፤ ፈወሳቸውም። ከዚህም የተነሣ ከገሊላ፣ ከ “ዐሥር ከተማ”፣ ከኢየሩሳሌም፣ ከይሁዳና ከዮርዳኖስ ማዶ የመጡ ብዙ ሰዎች ተከተሉት።
ማቴዎስ 4:18-25 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በገሊላ ባሕር አጠገብ ሲመላለስም ሁለት ወንድማማች ጴጥሮስ የሚሉትን ስምዖንን ወንድሙንም እንድርያስን መረባቸውን ወደ ባሕር ሲጥሉ አየ፥ ዓሣ አጥማጆች ነበሩና። እርሱም፦ በኋላዬ ኑና ሰዎችን አጥማጆች እንድትሆኑ አደርጋችኋለሁ አላቸው። ወዲያውም መረባቸውን ትተው ተከተሉት። ከዚያም እልፍ ብሎ ሌሎችን ሁለት ወንድማማች የዘብዴዎስን ልጅ ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ከአባታቸው ከዘብዴዎስ ጋር በታንኳ መረባቸውን ሲያበጁ አየ፤ ጠራቸውም። እነርሱም ወዲያው ታንኳይቱንና አባታቸውን ትተው ተከተሉት። ኢየሱስም በምኩራቦቻቸው እያስተማረ የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ በሕዝብም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ በገሊላ ሁሉ ይዞር ነበር። ዝናውም ወደ ሶርያ ሁሉ ወጣ፤ በልዩ ልዩ ደዌና ሥቃይም ተይዘው የታመሙትን ሁሉ አጋንንትም ያደሩባቸውን በጨረቃም የሚነሣባቸውን ሽባዎችንም ወደ እርሱ አመጡ፥ ፈወሳቸውም። ከገሊላም ከአሥሩ ከተማም ከኢየሩሳሌምም ከይሁዳም ከዮርዳኖስም ማዶ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት።
ማቴዎስ 4:18-25 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኢየሱስ በገሊላ ባሕር አጠገብ ሲያልፍ፥ ዓሣ አጥማጆች የነበሩትን ሁለት ወንድማማች እነርሱም ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንንና ወንድሙን እንድርያስን፥ መረባቸውን ወደ ባሕር ሲጥሉ አየ። ኢየሱስም “ኑ ተከተሉኝ፤ ዓሣን እንደምታጠምዱ ሁሉ ሰዎችን እንድትሰበስቡልኝ አደርጋችኋለሁ” አላቸው። እነርሱም ወዲያውኑ መረባቸውን ትተው ተከተሉት። ከዚያም እልፍ ብሎ፥ የዘብዴዎስ ልጆች የሆኑትን ሌሎች ሁለት ወንድማማች ያዕቆብንና ዮሐንስን አየ። እነርሱም ከአባታቸው ከዘብዴዎስ ጋር በጀልባ ላይ ሆነው መረባቸውን ሲጠግኑ ሳለ ጠራቸው። እነርሱም ወዲያውኑ ጀልባዋንና አባታቸውን ትተው ተከተሉት። ኢየሱስም በምኲራቦቻቸው እያስተማረና የእግዚአብሔርን መንግሥት የምሥራች ቃል እየሰበከ፥ በልዩ ልዩ በሽታና ደዌ የተያዙትንም ሰዎች እየፈወሰ በገሊላ ምድር ሁሉ ይዘዋወር ነበር። ዝናው በሶርያ አገር ሁሉ ስለ ተሰማ፥ ሰዎች በልዩ ልዩ በሽታና ደዌ የሚሠቃዩትን፥ ርኩሳን መናፍስት ያደሩባቸውን፥ የሚጥል በሽታ ያለባቸውንና ሽባዎችንም ሁሉ ወደ እርሱ አመጡ፤ እርሱም ፈወሳቸው። ከገሊላ ምድርና ከዐሥሩ ከተሞች ከኢየሩሳሌምና ከይሁዳ፥ ከዮርዳኖስም ወንዝ ማዶ የመጡ ብዙ ሰዎች ኢየሱስን ተከተሉት።
ማቴዎስ 4:18-25 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በገሊላ ባሕር አጠገብ ሲያልፍ ሳለ፥ ሁለት ወንድማማቾች፥ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንንና ወንድሙን እንድርያስን ዓሣ አጥማጆች ነበሩና መረባቸውን ወደ ባሕር ሲጥሉ አየ። እርሱም “ኑ ተከተሉኝ፤ ሰዎችን አጥማጆች አደርጋችኋለሁ” አላቸው። ወዲያውኑ መረባቸውን ጥለው ተከተሉት። ከዚያም እልፍ ብሎ ሌሎች ሁለት ወንድማማቾች የዘብዴዎስን ልጅ ያዕቆብንና ወንድሙን ዮሐንስን በታንኳ ውስጥ ከአባታቸው ከዘብዴዎስ ጋር መረባቸውን ሲጠግኑ አየና ጠራቸው። እነርሱም ወዲያውኑ ታንኳይቱንና አባታቸውን ትተው ተከተሉት። ኢየሱስም በምኵራቦቻቸው እያስተማረ፥ የመንግሥትን ወንጌል እየሰበከ፥ በሕዝቡ መካከል ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ በገሊላ ሁሉ ይዘዋወር ነበር። ዝናው በመላዋ ሶርያ ሁሉ ተሰማ፤ በልዩ ልዩ ደዌና ሥቃይ ተይዘው የታመሙትን ሁሉ፥ አጋንንት ያደሩባቸውን፥ በጨረቃ የሚነሣባቸውንና ሽባዎችን ወደ እርሱ አመጡ፤ እርሱም ፈወሳቸው። ከገሊላ፥ ከዐሥሩ ከተሞች፥ ከኢየሩሳሌም፤ ከይሁዳና ከዮርዳኖስ ማዶ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት።