እረዳቸው ዘንድ ወደ እኔ ጮኹ፤ እኔም በእነርሱና በግብጻውያን መካከል ጨለማ እንዲሆን አደረግሁ። ባሕሩም እንዲከነበልባቸው አድርጌ ግብጻውያንን አሰጠምሁ፤ በግብጻውያን ላይ ምን እንዳደረግሁ በዐይኖቻችሁ አይታችኋል፤ ከዚያም በኋላ እናንተ ለብዙ ጊዜ በበረሓ ኖራችሁ። ከዚህም በኋላ ከዮርዳኖስ በስተምሥራቅ ወደሚኖሩት ወደ አሞራውያን ምድር አመጣኋችሁ፤ እነርሱ ተዋጉአችሁ፤ እኔ ግን በእነርሱ ላይ ድልን አቀዳጀኋቸው፤ ከፊታችሁም አጠፋኋቸው፤ ምድራቸውንም ወረሳችሁ። ከዚህም በኋላ የሞአብ ንጉሥ የነበረው የጲፖር ልጅ ባላቅ ሊወጋችሁ በእናንተ ላይ ተነሣሣ፤ እናንተንም ይረግምለት ዘንድ በለዓም ተብሎ ወደሚጠራው ወደ ቢዖር ልጅ መልእክት ላከ፤ እኔ ግን በለዓምን አልሰማሁትም፤ ስለዚህም በመርገም ፈንታ ባረካችሁ፤ በዚህም ዐይነት ከባላቅ እጅ አዳንኳችሁ፤ እናንተም የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግራችሁ ወደ ኢያሪኮ መጣችሁ፤ የኢያሪኮም ሰዎች፥ እንዲሁም አሞራውያን፥ ፈሪዛውያን፥ ከነዓናውያን፥ ሒታውያን፥ ጌርጌሳውያን፥ ሒዋውያንና ኢያቡሳውያን እናንተን ለመውጋት ተነሡ፤ እኔ ግን በእነርሱ ላይ ድልን አቀዳጀኋችሁ። በሁለቱ አሞራውያን ነገሥታት ላይ እንዳደረግሁት አስቀድሜ ከፊታችሁ ያባረራቸውን ተርብ ሰደድኩባቸው፤ ይህ በእናንተ ሰይፍ ወይም በእናንተ ቀስት የሆነ አይደለም። እናንተ በማረስ ያልደከማችሁበትን የለማ ምድርና ያልሠራችኋቸውንም ከተሞች መኖሪያ አድርጌ ሰጠኋችሁ፤ እነሆ፥ አሁን ያልተከላችሁትን የወይን ተክልና ያልደከማችሁበትን የወይራ ዛፍ ፍሬ እየተመገባችሁ ትኖራላችሁ።’ ” ኢያሱ ንግግሩን በመቀጠል እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ እግዚአብሔርን አክብሩት፤ በፍጹም ቅንነትና በታማኝነት አገልግሉት፤ የቀድሞ አባቶቻችሁ ከኤፍራጥስ ወንዝ ማዶና በግብጽ ይሰግዱላቸው የነበሩትን ባዕዳን አማልክት አስወግዳችሁ እግዚአብሔርን ብቻ አምልኩ፤ እርሱን ማምለክ መልካም መስሎ ካልታያችሁ ግን የቀድሞ አባቶቻችሁ ከኤፍራጥስ ወንዝ ማዶ በነበሩበት ጊዜ ያመልኩአቸው የነበሩትን ወይም አሁን በምድራቸው የምትኖሩባቸውን የአሞራውያንን አማልክት ታመልኩ እንደሆን የምታመልኩትን ዛሬውኑ ምረጡ፤ እኔና ቤተሰቤ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን።”
መጽሐፈ ኢያሱ 24 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ኢያሱ 24:7-15
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች