ኢያሱ 24:7-15

ኢያሱ 24:7-15 NASV

እነርሱ ግን ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እርሱም በእናንተና በግብጻውያን መካከል ጨለማ እንዲሆን አደረገ። ባሕሩን በላያቸው አመጣ፤ አሰጠማቸውም። በግብጻውያን ላይ ያደረግሁትንም ራሳችሁ በዐይናችሁ አያችሁ፤ በምድረ በዳም ብዙ ጊዜ ኖራችሁ። “ ‘በምሥራቅ ዮርዳኖስ ወደሚኖሩት ወደ አሞራውያን ምድር አመጣኋችሁ፤ እነርሱ ወጓችሁ፤ እኔ ግን አሳልፌ በእጃችሁ ሰጠኋቸው፤ ከፊታችሁ አጠፋኋቸው፤ እናንተም ምድራቸውን ወረሳችሁ። የሞዓብ ንጉሥ የሴፎር ልጅ ባላቅ፣ እስራኤልን ለመውጋት ተነሣ፣ እናንተንም መጥቶ ይረግማችሁ ዘንድ ወደ ቢዖር ልጅ ወደ በለዓም መልእክተኛ ላከ፤ እኔ ግን በለዓምን ልሰማው አልፈለግሁም፤ ስለዚህ ደግሞ ደጋግሞ መረቃችሁ፤ እኔም፤ ከባላቅ እጅ ታደግኋችሁ። “ ‘ከዚያም ዮርዳኖስን ተሻገራችሁ፤ ወደ ኢያሪኮ መጣችሁ፤ አሞራውያን፣ ፌርዛውያን፣ ከነዓናውያን፣ ኬጢያውያን፣ ጌርጌሳውያን፣ ኤዊያውያንና ኢያቡሳውያን እንደ ወጓችሁ ሁሉ፣ የኢያሪኮም ገዦች ወጓችሁ፤ እኔ ግን አሳልፌ በእጃችሁ ሰጠኋቸው። በፊታችሁ ተርብ ላክሁ፤ ይህም እነርሱንና ሁለቱን የአሞራውያን ነገሥታት ጭምር ከፊታችሁ አሳደደ፤ ይህ ደግሞ በራሳችሁ ሰይፍና ቀስት ያደረጋችሁት አይደለም። ስለዚህ ያልደከማችሁበትን ምድርና ያልሠራችኋቸውን ከተሞች ሰጠኋችሁ። እነሆ፣ በከተሞቹ ትኖራላችሁ፤ ካልተከላችሁት የወይን ተክልና የወይራ ዛፍ ትበላላችሁ።’ “አሁንም እግዚአብሔርን ፍሩ፤ በፍጹም ታማኝነትም ተገዙለት። የቀድሞ አባቶቻችሁ ከወንዙ ማዶና በግብጽ ያመለኳቸውን አማልክት ከእናንተ አርቁ፤ እግዚአብሔርን ብቻ አምልኩ። እግዚአብሔርን ማምለክ የማያስፈልግ መስሎ ከታያችሁ ግን፣ የቀድሞ አባቶቻችሁ ከወንዙ ማዶ ካመለኳቸው አማልክት ወይም በምድራቸው የምትኖሩባቸው አሞራውያን ከሚያመልኳቸው አማልክት ታመልኩ እንደ ሆነ የምታመልኩትን ዛሬውኑ ምረጡ፤ እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን።”