እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ! እኔ አምላክህ ነኝ፥ ተስፋ አትቊረጥ! እኔ አበረታሃለሁ፥ እረዳህማለሁ፤ ድል ነሺ በሆነ ክንዴ እደግፍሃለሁ። በአንተ ላይ የተቈጡ ሁሉ ተሸንፈው ያፍራሉ፤ አንተንም ለመጒዳት የሚነሡ ጠፍተው እንዳልነበሩ ይሆናሉ። ጠላቶችህን ትፈልጋቸዋለህ፤ ነገር ግን አታገኛቸውም፤ በአንተ ላይ ጦርነት አስነሥተው የነበሩትም ፈጽሞ እንዳልነበሩ ይሆናሉ። ‘አይዞህ አትፍራ፥ አትደንግጥ፥ ቀኝ እጅህን ይዤ እረዳሃለሁ’ እያልኩ የማበረታታህ፥ እኔ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እንደ ትል ደካማ የሆንክ እስራኤል ሆይ! እኔ ስለምረዳህ አትፍራ፤ የምታደግህ የእስራኤል ቅዱስ እኔ ነኝ። እነሆ፥ እኔ እንደ ስለታም፥ አዲስና፥ ጥርስ እንዳለው የመውቂያ መሣሪያ አደርግሃለሁ፤ ተራራዎችንም በማበራየት ታደቃቸዋለህ፤ ኰረብቶችንም ዳምጠህ እንደ ገለባ ታደርጋቸዋለህ። ወደ ሰማይ ትበትናቸዋለህ፤ ነፋስም ጠራርጎ ይወስዳቸዋል፤ ዐውሎ ነፋስም ይበትናቸዋል፤ በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር ደስ ይልሃል፤ በእኔ በእስራኤል ቅዱስም ትመካለህ። “ድኾችና ችግረኞች ውሃ ይፈልጋሉ፤ አያገኙም፤ ጒሮሮአቸው ከጥማት የተነሣ ሲደርቅ፥ እኔ እግዚአብሔር ጸሎታቸውን እሰማለሁ፤ እኔም የእስራኤል አምላክ ከቶ አልተዋቸውም። በደረቁ ኰረብቶች ላይ ወንዞች እንዲፈስሱ አደርጋለሁ፤ በሸለቆዎችም ውስጥ የውሃ ምንጮች ያልፋሉ፤ በረሓዎችንም የኲሬ ውሃ መከማቻ እንዲሆኑ አደርጋቸዋለሁ፤ ደረቁም ምድር የምንጭ ውሃ መፍሰሻ ይሆናል። የሊባኖስ ዛፎችን፥ የግራር እንጨቶችን፥ ባርሰነቱንና የወይራ ዛፎችን በበረሓ አበቅላለሁ፤ በምድረ በዳ ዝግባ፥ አስታና ጥድ፥ ወይራ የሞላበት ደን አበቅላለሁ። ይህን የማደርገው የእኔ የእግዚአብሔር እጅ ይህን እንዳደረገና እኔም የእስራኤል ቅዱስ እንደ ፈጠርኩት ሁሉም አይተው ያውቁ ዘንድ፥ አስተውለውም ይረዱ ዘንድ ነው።”
ትንቢተ ኢሳይያስ 41 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ኢሳይያስ 41:10-20
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች