ትንቢተ ሆሴዕ 4:1-7
ትንቢተ ሆሴዕ 4:1-7 አማ05
በዚህች ምድር በሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ላይ እግዚአብሔር የሚያቀርበው ወቀሳ አለው፤ ስለዚህ የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! እርሱ የሚልህን ሁሉ ስማ፦ “በምድሪቱ ላይ ታማኝነትና ፍቅር እግዚአብሔርንም ማወቅ ጠፍቶአል። በመሐላ የገቡትን ቃል ኪዳን አፍርሰው ይዋሻሉ፤ ይገድላሉ፤ ይሰርቃሉ፤ ያመነዝራሉም፤ ግፍና ግድያ እየበዛ ሄዶአል። በዚህም ምክንያት በምድሪቱ ላይ ድርቅ ይመጣል፤ በእርስዋ የሚኖሩ ሁሉ ይደክማሉ፤ እንስሶች፥ ወፎችና የባሕር ዓሣዎች ሁሉ ያልቃሉ።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እኔ የምወቅሰው እናንተን ካህናትን ስለ ሆነ ሕዝቡን የሚከስ ወይም የሚወቀስ አይኑር። እናንተ ካህናት ሆይ! በቀን ብርሃን ትደናበራላችሁ፤ ነቢያትም ሌሊት ከእናንተ ጋር በጨለማ ይደናበራሉ፤ ስለዚህ እናት አገራችሁን አጠፋታለሁ። ሕዝቤ እኔን በሚገባ ካለማወቁ የተነሣ ጠፍቶአል፤ እናንተ እኔን ለማወቅ ስላልፈለጋችሁ እኔም ካህናት ሆናችሁ እንድታገለግሉኝ አልፈልጋችሁም፤ ሕጌንም ስላቃለላችሁና ስለ ረሳችሁ ልጆቻችሁ በእኔ ዘንድ የተረሱ ይሆናሉ። “እናንተ ካህናት ቊጥራችሁ በበዛ መጠን በደላችሁም በፊቴ እየበዛ ሄዶአል፤ ስለዚህ ክብራችሁን ገፍፌ አዋርዳችኋለሁ።

