ሆሴዕ 4:1-7
ሆሴዕ 4:1-7 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እናንተ የእስራኤል ልጆች ሆይ! እውነትና ምሕረት፥ እግዚአብሔርንም ማወቅ በምድር ስለሌለ እግዚአብሔር በምድር ላይ የሚኖሩትን ይወቅሳልና የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። ነገር ግን ሐሰት፥ ግዳይና ስርቆት፥ ምንዝርናም ምድርን ሞልተዋል፤ ደምንም ከደም ጋር ይቀላቅላሉ። ስለዚህ ምድሪቱ ታለቅሳለች፤ በእርስዋም ከሚቀመጡ ሁሉ ከምድር አራዊትና ከሰማይ ወፎች፤ ከምድርም ተንቀሳቃሾች ጋር ትጠፋለች፤ የባሕሩም ዓሦች ያልቃሉ። ነገር ግን ሕዝቤ እንደሚከራከር ካህን ነውና እንግዲህ የሚከራከር፥ ማንም አይኑር፥ የሚዘልፍም ማንም አይኑር። በቀንም ትደክማለህ፤ ነቢዩም ከአንተ ጋር ይደክማል፤ እናታችሁም ሌሊትን ትመስላለች። ሕዝቤ አእምሮ እንደሌላቸው ይመስላሉ፤ አንተም አእምሮህ ተለይቶሃልና እኔ ካህን እንዳትሆነኝ እተውሃለሁ፤ የአምላክህንም ሕግ ረስተሃልና እኔ ደግሞ ልጆችህን እረሳለሁ። እንደ ብዛታቸው መጠን ኀጢአት ሠሩብኝ፤ እኔም ክብራቸውን ወደ ውርደት እለውጣለሁ።
ሆሴዕ 4:1-7 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እናንተ የእስራኤል ልጆች፣ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እግዚአብሔር በምድሪቱ በምትኖሩት ላይ የሚያቀርበው ክስ አለውና፤ ምክንያቱም ታማኝነት የለም፤ ፍቅርም የለም፤ እግዚአብሔርንም ማወቅ በምድሪቱ የለም። በዚያ ያለው ርግማን፣ መዋሸት፣ መግደል፣ መስረቅና ማመንዘር ብቻ ነው፤ ቃል ኪዳንን ሁሉ ያፈርሳሉ፤ ደም ማፍሰስና ግድያ ይበዛል። ስለዚህ ምድሪቱ አለቀሰች፤ በውስጧም የሚኖሩ ሁሉ ኰሰመኑ፤ የምድር አራዊት፣ የሰማይ ወፎች፣ የባሕርም ዓሦች ዐለቁ። “ነገር ግን ማንም ሰው አይከራከር፤ ማንም ሌላውን አይወንጅል፤ በካህናት ላይ ክስን እንደሚያቀርቡ፣ ሕዝብህ እንደዚያው ናቸውና። ቀንና ሌሊት ትደናበራላችሁ፤ ነቢያትም ከእናንተ ጋራ ይደናበራሉ። ስለዚህ እናታችሁን አጠፋታለሁ፤ ሕዝቤ ዕውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቷል። ዕውቀትን ስለ ናቃችሁ፣ እኔም ካህናት እንዳትሆኑ ናቅኋችሁ፤ የአምላካችሁን ሕግ ስለ ረሳችሁ፣ እኔም ልጆቻችሁን እረሳለሁ። ካህናት በበዙ ቍጥር በእኔ ላይ የሚያደርጉት ኀጢአት በዝቷል፤ ክብራቸውንም በውርደት ለውጠዋል።
ሆሴዕ 4:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እናንተ የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ እውነትና ምሕረት እግዚአብሔርንም ማወቅ በምድር ስለሌለ እግዚአብሔር በምድሩ ላይ ከሚኖሩ ጋር ክርክር አለውና የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። እርግማንና ሐሰት ግዳይና ስርቆት ምንዝርናም ወጥተዋል፥ ደምም ወደ ደም ደርሶአል። ስለዚህ ምድሪቱ ታለቅሳለች፥ በእርስዋም የሚቀመጡ ሁሉ ከምድር አራዊትና ከሰማይ ወፎች ጋር ይደክማሉ፥ የባሕሩም ዓሦች ያልቃሉ። ነገር ግን ሕዝብህ ከካህን ጋር እንደሚከራከሩ ናቸውና ማንም አይከራከር፥ ማንም አይዝለፍ። በቀንም ትሰናከላለህ፥ ነቢዩም ከአንተ ጋር በሌሊት ይሰናከላል፥ እናትህንም አጠፋታለሁ። ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቶአል፥ አንተም እውቀትን ጠልተሃልና እኔ ካህን እንዳትሆነኝ እጠላሃለሁ፥ የአምላክህንም ሕግ ረስተሃልና እኔ ደግሞ ልጆችህን እረሳለሁ። እንደ ብዛታቸው መጠን ኃጢአት ሠሩብኝ፥ እኔም ክብራቸውን ወደ ነውር እለውጣለሁ።
ሆሴዕ 4:1-7 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በዚህች ምድር በሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ላይ እግዚአብሔር የሚያቀርበው ወቀሳ አለው፤ ስለዚህ የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! እርሱ የሚልህን ሁሉ ስማ፦ “በምድሪቱ ላይ ታማኝነትና ፍቅር እግዚአብሔርንም ማወቅ ጠፍቶአል። በመሐላ የገቡትን ቃል ኪዳን አፍርሰው ይዋሻሉ፤ ይገድላሉ፤ ይሰርቃሉ፤ ያመነዝራሉም፤ ግፍና ግድያ እየበዛ ሄዶአል። በዚህም ምክንያት በምድሪቱ ላይ ድርቅ ይመጣል፤ በእርስዋ የሚኖሩ ሁሉ ይደክማሉ፤ እንስሶች፥ ወፎችና የባሕር ዓሣዎች ሁሉ ያልቃሉ።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እኔ የምወቅሰው እናንተን ካህናትን ስለ ሆነ ሕዝቡን የሚከስ ወይም የሚወቀስ አይኑር። እናንተ ካህናት ሆይ! በቀን ብርሃን ትደናበራላችሁ፤ ነቢያትም ሌሊት ከእናንተ ጋር በጨለማ ይደናበራሉ፤ ስለዚህ እናት አገራችሁን አጠፋታለሁ። ሕዝቤ እኔን በሚገባ ካለማወቁ የተነሣ ጠፍቶአል፤ እናንተ እኔን ለማወቅ ስላልፈለጋችሁ እኔም ካህናት ሆናችሁ እንድታገለግሉኝ አልፈልጋችሁም፤ ሕጌንም ስላቃለላችሁና ስለ ረሳችሁ ልጆቻችሁ በእኔ ዘንድ የተረሱ ይሆናሉ። “እናንተ ካህናት ቊጥራችሁ በበዛ መጠን በደላችሁም በፊቴ እየበዛ ሄዶአል፤ ስለዚህ ክብራችሁን ገፍፌ አዋርዳችኋለሁ።
ሆሴዕ 4:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እናንተ የእስራኤል ልጆች ሆይ! እውነትና ጽኑ ፍቅር አምላክንም ማወቅ በምድሪቱ ስለ ሌለ ጌታ በምድሪቱ ላይ ከሚኖሩ ጋር ሙግት አለውና የጌታን ቃል ስሙ። መራገምና መዋሸት፥ መግደልና መስረቅ፥ ማመንዘርም ገደባቸውን አልፈዋል፤ ደም ማፍሰስ ደም ማፍሰስን አስከትሏል። ስለዚህ ምድሪቱ ታለቅሳለች፥ በእርሷም የሚቀመጡ ሁሉ ከምድር አራዊትና ከሰማይ ወፎች ጋር በድካም ይዝላሉ፤ የባሕሩም ዓሦች እንኳ ያልቃሉ። ነገር ግን ሙግቴ ከካህን ጋር ነውና ማንም አይከራከር፥ ማንም አይዝለፍ። በቀንም ትሰናከላለህ፥ እንዲሁም ነቢይ ከአንተ ጋር በሌሊት ይሰናከላል፤ እናትህንም አጠፋታለሁ። ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቶአል፤ አንተም እውቀትን ትተሃልና ለእኔ ካህን እንዳትሆን ትቼሃለሁ፤ የአምላክህንም ሕግ ረስተሃልና እኔ ደግሞ ልጆችህን እረሳለሁ። እነርሱም እጅግ በበዙ ቍጥር አብዝተው ኃጢአትን በእኔ ላይ ሠሩ፤ እኔም ክብራቸውን ወደ ውርደት እለውጣለሁ።