የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! በኃጢአታችሁ ምክንያት የተሰናከላችሁ ስለ ሆነ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ። የኑዛዜ ቃል ይዛችሁ ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ፤ እንዲህም በሉት፦ “ኃጢአታችንን ሁሉ ይቅር በለን፤ በምሕረት ተቀበለን፤ እኛም የአንደበታችን መልካም ፍሬ የሆነውን ምስጋና እናቀርብልሃለን። አሦር አያድነንም፥ በጦር ፈረሶችም አንታመንም፤ ከእንግዲህ ወዲህ በእጃችን የሠራነውን ጣዖት ሁሉ ‘አምላክ’ ብለን አንጠራም፤ አምላክ ሆይ! ወላጆቻቸው የሞቱባቸው በአንተ ምሕረትን ያገኛሉ።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የሕዝቤን አለመታመን ፈውሼ፤ ወደ እኔ እመልሳቸዋለሁ ቊጣዬ ከእነርሱ ስለ ተመለሰ፥ እኔ በገዛ ፈቃዴ እወዳቸዋለሁ፤ ለእስራኤል ሕዝብ እንደሚወርድ ጠል እሆናለሁ። እነርሱ እንደ አበባ ይፈካሉ፤ እንደ ሊባኖስ ዛፎችም ሥር ይሰዳሉ። ቡቃያዎቻቸው ይለመልማሉ፤ እንደ ወይራ ዛፍ የሚያምሩ ይሆናሉ፤ እንደ ሊባኖስ ደን መልካም መዓዛ ይሰጣሉ። ተመልሰውም በእኔ ጥላ ሥር ይሆናሉ፤ እንደ እህል ቡቃያ ይለመልማሉ፤ እንደ ወይን ተክልም ያብባሉ፤ መዓዛቸውም እንደ ሊባኖስ የወይን ጠጅ ዝነኛ ይሆናል። የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! እኔ ከጣዖቶች ጋር ምን ግንኙነት አለኝ? ለጸሎታችሁ መልስ የምሰጥና የምንንከባከባችሁ እኔ ነኝ፤ እኔ ዘወትር ለምለም ሆኖ እንደሚታይ የጥድ ዛፍ ነኝ፤ ፍሬያማ የምትሆኑትም በእኔ አማካይነት ነው።” ጥበብ ያላቸው እነዚህን ነገሮች ይረዳሉ፤ አስተዋዮችም ያውቋቸዋል፤ የእግዚአብሔር መንገድ ትክክል ነው፤ ጻድቃን ይሄዱበታል፤ ኃጢአተኞች ግን ይሰናከሉበታል።
ትንቢተ ሆሴዕ 14 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ሆሴዕ 14:1-9
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች