ኦሪት ዘፍጥረት 33:1-9

ኦሪት ዘፍጥረት 33:1-9 አማ05

ያዕቆብ ቀና ብሎ ሲመለከት፥ ዔሳው አራት መቶ ሰዎችን አስከትሎ ሲመጣ አየ፤ ያዕቆብም ልጆቹን ከልያ፥ ከራሔልና ከሁለቱ ሴቶች አገልጋዮቹ ጋር ከፋፈላቸው። በመጀመሪያ ሁለቱን ሴቶች አገልጋዮቹንና ልጆቻቸውን አስቀደመ፤ ቀጥሎ ልያንና ልጆችዋን አስከተለ፤ በመጨረሻም ራሔልንና ዮሴፍን ከሁሉ በኋላ አደረገ። ያዕቆብ ከሁሉ ቀድሞ ተጓዘ፤ ወደ ወንድሙ ወደ ዔሳው ሲቀርብ ወደ መሬት በመጐንበስ ሰባት ጊዜ እጅ ነሣ፤ ዔሳው ግን ሊገናኘው ወደ እርሱ ሮጠ፤ በአንገቱም ላይ ተጠምጥሞ ዕቅፍ አድርጎ ሳመው፤ ሁለቱም ተላቀሱ። ዔሳው በዙሪያው ተመልክቶ ሴቶቹንና ልጆቹን ባየ ጊዜ “እነዚህ ሁሉ ከአንተ ጋር ያሉ ሰዎች የማን ናቸው?” አለ። ያዕቆብም “ጌታዬ ሆይ፥ እነዚህ እግዚአብሔር በቸርነቱ የሰጠኝ ልጆች ናቸው” ሲል መለሰ። ከዚህ በኋላ ሴቶች አገልጋዮቹ ከልጆቻቸው ጋር መጥተው እጅ ነሡ። ቀጥሎም ልያና ልጆችዋ ቀርበው እጅ ነሡ፤ በመጨረሻም ዮሴፍና ራሔል ቀርበው እጅ ነሡ። ዔሳውም “እፊት እፊትስ እየተነዳ ሲሄድ ያየሁት የእንስሶች መንጋ ምንድን ነው?” አለ። ያዕቆብም “ጌታዬ ሆይ፥ እርሱ በአንተ ፊት ሞገስ እንዳገኝ የላክሁልህ ነው” አለ። ዔሳውም “ወንድሜ ሆይ፥ እኔ በቂ ሀብት አለኝ፤ የአንተ ለራስህ ይሁን” አለው።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}