ኦሪት ዘፍጥረት 32:13-21

ኦሪት ዘፍጥረት 32:13-21 አማ05

እዚያም ዐደረ፤ በማግስቱም ካለው ነገር ሁሉ ለወንድሙ ለዔሳው ስጦታ የሚሆን ነገር መርጦ አዘጋጀ፤ በዚህ ዐይነት ሁለት መቶ እንስት ፍየሎች፥ ኻያ ተባዕት ፍየሎች፥ ሁለት መቶ እንስት በጎች፥ ኻያ ተባዕት በጎች፤ ሠላሳ የሚያጠቡ ግመሎች ከነግልገሎቻቸው፥ አርባ ላሞች፥ ዐሥር ኰርማዎች፥ ኻያ እንስት አህዮችና ዐሥር ተባዕት አህዮች መረጠ፤ እነዚህንም በየመንጋው ከፈለና ለእያንዳንዳቸው እረኞች መደበላቸው፤ እረኞቹንም “ከእኔ ቀድማችሁ ሂዱ፤ በየመንጋው መካከል ርቀት እንዲኖር አድርጋችሁ፥ በመከታተል ሂዱ” አላቸው። የመጀመሪያዎቹንም እረኞች እንዲህ በማለት አዘዛቸው፤ “ወንድሜ ዔሳው በመንገድ አግኝቶ ‘የማን ሰዎች ናችሁ? ወዴትስ ትሄዳላችሁ? እነዚህ የምትነዱአቸው ከብቶች የማን ናቸው?’ ብሎ የጠየቃችሁ እንደ ሆነ፥ ‘እነዚህ ከብቶች የአገልጋይህ የያዕቆብ ናቸው፤ እርሱ እነዚህን የላከው ለጌታዬ ለዔሳው ስጦታ የሚሆን ነው፤ እነሆ ያዕቆብ ከኋላችን ነው’ ብላችሁ ንገሩት።” ለሁለተኛውም ለሦስተኛውም ክፍል እረኞችና ለቀሩትም የመንጋ ጠባቂዎች “እናንተም ዔሳውን ስታገኙት እንደዚሁ ንገሩት፤ ‘በተለይም አገልጋይህ ያዕቆብ ከበስተኋላ እየመጣ ነው’ ብላችሁ ንገሩት” አላቸው። ይህንንም ያለበት ምክንያት “እኔ ከመድረሴ በፊት በሚደርስለት ስጦታ ቊጣውን አበርድ ይሆናል፤ በኋላም በማገኘው ጊዜ በደስታ ይቀበለኛል” በሚል ሐሳብ ነው። በዚህ ዐይነት ስጦታውን አስቀድሞ ከላከ በኋላ፥ እዚያው በሰፈሩበት ቦታ ዐደረ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}