በላባም ዘንድ እንደ ቀድሞው ተወዳጅ አለመሆኑን ተረዳ። በዚህን ጊዜ እግዚአብሔር ያዕቆብን “ወደ አባቶችህና ወደ ዘመዶችህ አገር ተመለስ፤ እኔም ከአንተ ጋር እሆናለሁ” አለው። ስለዚህ ያዕቆብ መንጋዎቹ ወደ ተሰማሩበት መስክ እንዲመጡ ራሔልንና ልያን አስጠራቸው፤ እንዲህም አላቸው፤ “አባታችሁ እንደ ቀድሞው ጊዜ እንደማይወደኝ ተረድቼአለሁ፤ ነገር ግን የአባቴ አምላክ ከእኔ ጋር አለ፤ ጒልበቴን ሳልቈጥብ በትጋት አባታችሁን እንዳገለገልኩ እናንተም ታውቃላችሁ፤ እርሱ ግን ዐሥር ጊዜ ደመወዜን በመለዋወጥ አታለለኝ፤ ሆኖም እኔን ለመጒዳት እግዚአብሔር አልፈቀደለትም፤ ላባ ‘ዝንጒርጒሮቹ ሁሉ ለአንተ ደመወዝ ይሁኑ’ ባለኝ ጊዜ፥ መንጋዎቹ ሁሉ ዝንጒርጒር ወለዱ፤ ደግሞም ‘ሽመልመሌ መሳዮቹ ሁሉ ለአንተ ደመወዝ ይሁኑ’ ባለኝ ጊዜ፥ መንጋዎቹ ሁሉ ሽመልመሌ መሳዮች ወለዱ። እግዚአብሔር የአባታችሁን የላባን መንጋዎች ወስዶ ለእኔ የሰጠኝ በዚህ ዐይነት ነው። “እንስሶቹ ለመፅነስ ፍትወት በሚያድርባቸው ወራት የሚያጠቁአቸው አውራ ፍየሎች ሽመልመሌ፥ ዝንጒርጒርና ነቊጣ መሆናቸውን በሕልም አየሁ። በዚያው ሕልም የእግዚአብሔር መልአክ ‘ያዕቆብ!’ ብሎ ጠራኝ፤ እኔም ‘እነሆ፥ አለሁ!’ አልኩ። እርሱም እንዲህ አለኝ፤ ‘መንጋዎቹን የሚያጠቁአቸው አውራ ፍየሎች ሽመልመሌ፥ ዝንጒርጒርና ነቊጣ ያለባቸው መሆናቸውን ተመልከት፤ ላባ የፈጸመብህን በደል ስላየሁ ይህን ያደረግኹት እኔ ነኝ፤ የመታሰቢያ ድንጋይ አቁመህ ዘይት በመቀባት በተሳልክበት ቦታ በቤትኤል የተገለጥኩልህ አምላክህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ፤ አሁንም ከዚህ አገር በፍጥነት ወጥተህ ወደ ተወለድክበት አገር ተመለስ።’ ” ራሔልና ልያ ለያዕቆብ እንዲህ ሲሉ መለሱለት፦ “በአባታችን ቤት የውርስ ድርሻ ቀርቶልናልን? እርሱ እኛን የሚያየን እንደ ባዕድ አይደለምን? አስቀድሞ ሸጦን ነበር፤ አሁን ደግሞ ለእኛ ዋጋ የተከፈለውን ሁሉ አጥፍቶታል፤ አሁንም እግዚአብሔር ከአባታችን ወስዶ ለአንተ የሰጠህ ሀብት ሁሉ የእኛና የልጆቻችን ነው፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ያዘዘህን ሁሉ አድርግ።” ያዕቆብም ተነሥቶ ልጆቹንና ሚስቶቹን በግመሎች ላይ አስቀመጠ፤ በመስጴጦምያ ሳለ ያገኛቸውን መንጋዎችና ዕቃዎችን ሁሉ ይዞ ወደ ከነዓን ምድር ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅ ሄደ። ላባ በጎች ሊሸልት ሄዶ ስለ ነበር፥ እርሱ በሌለበት ራሔል በቤት የነበሩትን የአባቷን ጣዖቶች ሰርቃ ሄደች። ያዕቆብ መሄዱን ለላባ ሳይገልጥለት አታሎት ሄደ፤ የራሱ የሆነውን ሀብት ይዞ በፍጥነት ተጓዘ፤ የኤፍራጥስንም ወንዝ ተሻግሮ ወደ ኮረብታማው አገር ወደ ገለዓድ ሄደ።
ኦሪት ዘፍጥረት 31 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 31:2-21
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች