ወደ ቆላስይስ ሰዎች 2:1-7

ወደ ቆላስይስ ሰዎች 2:1-7 አማ05

ስለ እናንተና በሎዶቅያ ስላሉት ሰዎች እንዲሁም ፊቴን እንኳ አይተውት ስለማያውቁ ሰዎች ሁሉ ምን ያኽል ብርቱ ትግል እንደማደርግ ልታውቁ እወዳለሁ። የምታገለውም ልባቸው ተጽናንቶና በፍቅር ተሳስረው፥ ፍጹም ማስተዋልን ሁሉ በማትረፍ የእግዚአብሔር ምሥጢር የሆነውን ክርስቶስን እንዲያውቁ ነው። የጥበብና የዕውቀት ሀብት ተሰውሮ የሚገኘው በክርስቶስ ዘንድ ነው። ይህንንም የምላችሁ ማንም በሽንገላ ቃል እንዳያታልላችሁ ብዬ ነው፤ በሥጋ ከእናንተ ብርቅም እንኳ በመንፈስ ከእናንተ ጋር ነኝ፤ በመልካም ሥነ ሥርዓት መኖራችሁንና በክርስቶስ ላይ ያላችሁን ጽኑ እምነት በማየትም ደስ ይለኛል። ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደተቀበላችሁት በእርሱ ኑሩ፤ በእርሱ ተመሥርታችሁና ታንጻችሁ፥ በተማራችሁት መሠረት፥ በእምነታችሁ ጸንታችሁ ኑሩ፤ ሞልቶ የሚተርፍ ምስጋናም አቅርቡ።