በዚያን ጊዜ ሳውል የጌታን ደቀ መዛሙርት ለመግደል ገና እየዛተ ወደ ካህናት አለቃው ሄደ። የጌታንም መንገድ የሚከተሉትን ሰዎች ወንዶችንም ሴቶችንም ሲያገኝ እያሰረ ወደ ኢየሩሳሌም ለማምጣት የሚያስችል ደብዳቤ ለደማስቆ ምኵራቦች ተጽፎ እንዲሰጠው ሊቀ ካህናቱን ጠየቀ። ሲሄድም ወደ ደማስቆ በቀረበ ጊዜ በእርሱ ዙሪያ በድንገት ከሰማይ ብርሃን አንጸባረቀ። በዚያን ጊዜ በምድር ላይ ወደቀ፤ “ሳውል፥ ሳውል፥ ለምን ታሳድደኛለህ?” የሚል ድምፅም ሰማ። ሳውልም “ጌታ ሆይ! አንተ ማን ነህ?” አለ፤ እርሱም “እኔ አንተ የምታሳድደኝ ኢየሱስ ነኝ፤ አሁን ግን ተነሥና ወደ ከተማ ግባ፤ ልታደርገው የሚገባህም እዚያ ይነገርሃል” አለው። ከሳውል ጋር ይሄዱ የነበሩ ሰዎች ድምፅ እየሰሙ ማንንም ባለማየታቸው የሚናገሩትን አጥተው፥ ዝም ብለው ቆሙ። ሳውልም ከወደቀበት መሬት ተነሣ፤ ዐይኖቹን በገለጠ ጊዜ ግን ምንም ማየት አልቻለም፤ ስለዚህ ሰዎቹ እጁን ይዘው እየመሩ ወደ ደማስቆ ወሰዱት። ሦስት ቀን ሙሉ ምንም ማየት ሳይችል፥ ሳይበላና ሳይጠጣም ቈየ። በዚያን ጊዜ በደማስቆ ሐናንያ የሚባል አንድ ደቀ መዝሙር ነበር፤ ጌታ በራእይ “ሐናንያ!” ብሎ ጠራው፤ እርሱም “እነሆኝ ጌታ ሆይ!” አለ። ጌታም እንዲህ አለው፦ “ቀጥተኛ ወደምትባለው መንገድ ሂድ፤ እዚያ በይሁዳ ቤት ሳውል የሚባለውን የጠርሴስ ሰው ፈልግ፤ እርሱ አሁን በጸሎት ላይ ነው።” ሳውልም ዐይኖቹ እንደገና ማየት እንዲችሉ ሐናንያ የተባለ ሰው ወደ እርሱ ገብቶ እጁን ሲጭንበት በራእይ አየ። ሐናንያ ግን እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ጌታ ሆይ! ይህ ሰው በኢየሩሳሌም በሚኖሩ ምእመናንህ ላይ ብዙ ክፉ ነገር ማድረጉን ከብዙዎች ሰምቻለሁ። እዚህም ስምህን የሚጠሩትን ሁሉ ለማሰር ከካህናት አለቆች ሥልጣን ተቀብሎአል።” ጌታም ሐናንያን እንዲህ አለው፦ “እርሱ ስሜን ለአረማውያን፥ ለነገሥታትና ለእስራኤል ሰዎች የሚያሳውቅ፥ የእኔ ምርጥ መሣሪያ ስለ ሆነ ወደ እርሱ ሂድ፤ ስለ እኔ ምን ያኽል ብዙ መከራ እንደሚቀበል እገልጥለታለሁ።” ስለዚህ ሐናንያ ወደዚያ ሄዶ እርሱ ወደ ነበረበትም ቤት ገባ፤ እጁንም በሳውል ላይ ጭኖ፥ “ወንድሜ ሳውል ሆይ! ወደዚህ ስትመጣ ሳለ በመንገድ የተገለጠልህ ጌታ ኢየሱስ እንደገና ማየት እንድትችልና መንፈስ ቅዱስም እንዲሞላብህ ወደ አንተ ልኮኛል” አለው። ወዲያውኑ ቅርፊት የሚመስል ነገር ከዐይኑ ወደቀና ማየት ቻለ፤ ተነሥቶም ተጠመቀ። መብልም በላና በረታ፤ በደማስቆ ከነበሩት ደቀ መዛሙርት ጋር ለጥቂት ቀኖች ቈየ። ወዲያውም ሳውል በደማስቆ “ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው” እያለ በየምኲራቡ ማስተማር ጀመረ። የሰሙትም ሁሉ፥ “ይህ ሰው በኢየሩሳሌም ይህን ስም የሚጠሩትን ሁሉ የሚያጠፋ የነበረ አይደለምን? ወደዚህስ የመጣው እነርሱን እያሰረ ወደ ካህናት አለቆች ለመውሰድ አይደለምን?” በማለት ይደነቁ ነበር። ሳውል ግን ይበልጥ እየበረታ ሄደ፤ ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን በማስረዳት በደማስቆ ይኖሩ የነበሩትን አይሁድ መልስ ያሳጣቸው ነበር። ከብዙ ቀን በኋላ አይሁድ ሳውልን ለመግደል ተማከሩ፤ እርሱ ግን የተንኰል ዐድማቸውን ዐወቀ፤ እነርሱም እርሱን ለመግደል ሌት ተቀን እርሱ የሚወጣባቸውን በሮች ይጠብቁ ነበር። ነገር ግን በሌሊት የራሱ ደቀ መዛሙርት ሳውልን በቅርጫት አድርገው በግንቡ አጥር መስኮት ወደታች አወረዱት። ሳውል ወደ ኢየሩሳሌም በሄደ ጊዜ እዚያ ካሉት ደቀ መዛሙርት ጋር ለመደባለቅ ሞከረ፤ እነርሱ ግን የእርሱ በክርስቶስ ማመን እውነት ስላልመሰላቸው ሁሉም ፈሩት። በርናባስ ግን ሳውልን ወደ ሐዋርያት አቀረበውና በመንገድ ሳለ ጌታ እንዴት እንደ ተገለጠለትና እንዳነጋገረው በደማስቆም በኢየሱስ ስም እንዴት በድፍረት እንዳስተማረ ነገራቸው። ስለዚህ ሳውል ከእነርሱ ጋር ሆኖ በኢየሩሳሌም ይዘዋወር ነበር። በጌታም ስም በድፍረት ያስተምር ነበር፤ የግሪክ ቋንቋ ተናጋሪ ከሆኑት አይሁድ ጋር እየተናገረ ይከራከር ነበር፤ እነርሱ ግን ሊገድሉት ዐቅደው ነበር። ወንድሞች ይህን ባወቁ ጊዜ ወደ ቂሣርያ ወሰዱት፤ ከዚያም ወደ ጠርሴስ እንዲሄድ አደረጉ። በይሁዳ፥ በገሊላና በሰማርያ ሁሉ ያለችው ቤተ ክርስቲያን ሰላም አገኘች፤ በረታችም፤ ጌታን እያከበረችና በመንፈስ ቅዱስ እየተጽናናች በቊጥር አደገች።
የሐዋርያት ሥራ 9 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሐዋርያት ሥራ 9:1-31
18 ቀናት
ሐዋርያው ጳውሎስ ለአንባቢዎቹ “ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል” (የሐዋርያት ሥራ 14:22) ይላል። የሐዋርያት ሥራን ማንበብ ወይም በዓለም ዙሪያ ካሉ ክርስቲያኖችን ምስክርነት መስማት፣ የዚህን ቃል እውነት አረጋግጠዋል። አማኞች ተቃውሞ እና ስደት ይደርስባቸዋል። ምናልባት እርሶም መከራ አጋጥሞት ይሆናል። በዚህ የንባብ እቅድ ውስጥ፣ ልናበረታታዎት እና በመከራን እንዴት መቋቋም እንደሚቻል ማስተማር እንፈልጋለን።
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች