ሳውል ግን የጌታን ደቀ መዛሙርት ለመግደል አሁንም እየዛተ ወደ ሊቀ ካህናቱ ሄደ፤ የጌታን መንገድ የሚከተሉትን ወንዶችንም ሆነ ሴቶችን በዚያ ካገኘ አስሮ ወደ ኢየሩሳሌም ለመውሰድ እንዲችል፣ በደማስቆ ለነበሩት ምኵራቦች ደብዳቤ እንዲሰጠው ሊቀ ካህናቱን ለመነው። ደማስቆ ለመድረስ ጥቂት ሲቀረው፣ ብርሃን ከሰማይ ድንገት በዙሪያው አንጸባረቀበት፤ እርሱም በመሬት ላይ ወደቀ፤ በዚያ ጊዜም “ሳውል፤ ሳውል፤ ለምን ታሳድደኛለህ?” የሚል ድምፅ ሰማ። ሳውልም፣ “ጌታ ሆይ፤ አንተ ማን ነህ?” አለው። እርሱም እንዲህ አለው፤ “እኔማ አንተ የምታሳድደኝ ኢየሱስ ነኝ። ነገር ግን ተነሣና ወደ ከተማዪቱ ግባ፤ ማድረግ የሚገባህም ይነገርሃል።” ከሳውል ጋራ ይጓዙ የነበሩትም ሰዎች ድምፁን እየሰሙ ማንንም ባላዩ ጊዜ፣ አፋቸውን ይዘው ቆሙ። ሳውልም ከመሬት ላይ ተነሥቶ ዐይኑን ሲገልጥ ምንም ማየት አልቻለም፤ ስለዚህ ሰዎቹ እጁን ይዘው እየመሩ ወደ ደማስቆ አስገቡት። ሦስት ቀንም ታወረ፤ እህል ውሃም አልቀመሰም። በደማስቆ ሐናንያ የሚባል አንድ ደቀ መዝሙር ነበር፤ ጌታም በራእይ፣ “ሐናንያ!” ብሎ ጠራው። እርሱም፣ “ጌታ ሆይ፤ እነሆኝ” አለ። ጌታም እንዲህ አለው፤ “ተነሣና ‘ቀጥተኛ ጐዳና’ በተባለው መንገድ ይሁዳ ወደ ተባለ ሰው ቤት ሂድ፤ እዚያም ሳውል የሚባል አንድ የጠርሴስ ሰው እየጸለየ ነውና ፈልገው፤ እርሱም ሐናንያ የሚባል ሰው እርሱ ወዳለበት መጥቶ እጁን እንደሚጭንበትና ዐይኑ እንደሚበራለት በራእይ አይቷል።” ሐናንያም መልሶ እንዲህ አለው፤ “ጌታ ሆይ፤ ይህ ሰው እኮ በኢየሩሳሌም ባሉ ቅዱሳንህ ላይ ምን ያህል ጕዳት እንዳደረሰ ከብዙ ሰው ሰምቻለሁ፤ ወደዚህም የመጣው ስምህን የሚጠሩትን ሁሉ ለማሰር ከካህናት አለቆች ሥልጣን ተቀብሎ ነው።” ጌታም እንዲህ አለው፤ “ሂድ! ይህ ሰው በአሕዛብና በነገሥታት ፊት እንዲሁም በእስራኤል ሕዝብ ፊት ስሜን እንዲሸከም የተመረጠ ዕቃዬ ነው፤ እኔም ስለ ስሜ ምን ያህል መከራ መቀበል እንዳለበት አሳየዋለሁ።” ሐናንያ ሄዶ፣ ወደተባለውም ቤት ገባ፤ በሳውልም ላይ እጁን ጭኖ፣ “ወንድሜ ሳውል ሆይ፤ ወደዚህ ስትመጣ በመንገድ ላይ የተገለጠልህ ጌታ ኢየሱስ፣ ዐይንህ እንዲበራና በመንፈስ ቅዱስም እንድትሞላ እኔን ልኮኛል” አለው። ወዲያውም ከሳውል ዐይን ላይ ቅርፊት የመሰለ ነገር ወደቀ፤ እንደ ገና ማየት ቻለ፤ ተነሥቶም ተጠመቀ፤ ምግብም በልቶ በረታ። ሳውል በደማስቆ ከነበሩት ደቀ መዛሙርት ጋራ አያሌ ቀን ተቀመጠ። ወዲያውም፣ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን በየምኵራቦቹ መስበክ ጀመረ። የሰሙትም ሁሉ በመገረም፣ ይህ ሰው “በኢየሩሳሌም ይህን ስም የሚጠሩትን ሲያጠፋ የነበረ አይደለምን? ደግሞም ወደዚህ የመጣው እነርሱን አስሮ ወደ ካህናት አለቆች ሊወስዳቸው አልነበረምን?” አሉ። ሳውል ግን እየበረታ ሄደ፤ በደማስቆ ለሚኖሩትም አይሁድ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ መሆኑን ማስረጃ እያቀረበ አፋቸውን ያስይዛቸው ነበር። ከብዙ ቀንም በኋላ፣ አይሁድ ሳውልን ለመግደል አሤሩ፤ ሳውል ግን ዕቅዳቸውን ዐውቆ ነበር፤ እነርሱም ሊገድሉት የከተማዋን በር ቀንና ሌሊት ይጠብቁ ነበር፤ የርሱ ደቀ መዛሙርት ግን በሌሊት በከተማዪቱ ቅጥር ቀዳዳ አሹልከው በቅርጫት አወረዱት። ሳውልም ወደ ኢየሩሳሌም በመጣ ጊዜ፣ ከደቀ መዛሙርት ጋራ ለመቀላቀል ሞከረ፤ እነርሱ ግን በርግጥ ደቀ መዝሙር መሆኑን ስላላመኑ ሁሉም ፈሩት። ይሁን እንጂ በርናባስ ወስዶ ወደ ሐዋርያት አመጣው፤ ሳውልም በጕዞው ላይ ሳለ ጌታን እንዴት እንዳየው፣ ጌታም እንዴት እንደ ተናገረው እንዲሁም በደማስቆ በኢየሱስ ስም እንዴት በድፍረት እንደ ሰበከ ነገራቸው። ስለዚህ ሳውል ዐብሯቸው ተቀመጠ፤ በኢየሩሳሌምም በመዘዋወር በጌታ ስም በድፍረት ይናገር ነበር። ከግሪክ አገር ከመጡት አይሁድ ጋራ እየተነጋገረ ይከራከር ነበር፤ እነርሱ ግን ሊገድሉት ጥረት ያደርጉ ነበር። ወንድሞችም ይህን ባወቁ ጊዜ፣ ወደ ቂሳርያ አውርደው ወደ ጠርሴስ ሰደዱት። በዚህ ጊዜ በይሁዳ፣ በገሊላና በሰማርያ ያለችው ቤተ ክርስቲያን በሰላም መኖር ጀመረች፤ ተጠናከረችም። ደግሞም ጌታን በመፍራት እየተመላለሰችና በመንፈስ ቅዱስ እየተጽናናች በቍጥር እየበዛች ሄደች።
ሐዋርያት ሥራ 9 ያንብቡ
ያዳምጡ ሐዋርያት ሥራ 9
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሐዋርያት ሥራ 9:1-31
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች