የተበተኑትም አማኞች በሄዱበት ስፍራ ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ያስተምሩ ነበር። ፊልጶስም ወደ ሰማርያ ከተማ ሄዶ ሰዎቹን ስለ መሲሕ አስተማራቸው። ሰዎቹም የፊልጶስን ቃል በሰሙና የሚያደርጋቸውን ተአምራት ባዩ ጊዜ በአንድ ሐሳብ በጥንቃቄ ያዳምጡት ነበር። ርኩሳን መናፍስትም በታላቅ ድምፅ እየጮኹ ከብዙ ሰዎች ይወጡ ነበር፤ ብዙ ሽባዎችና አንካሶችም ይድኑ ነበር። ስለዚህ በዚያች ከተማ ታላቅ ደስታ ሆነ። በዚያች ከተማ ስምዖን የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ ይህ ሰው በከተማይቱ ውስጥ አስማት እያደረገ የሰማርያን ሕዝብ ሲያስደንቅ ቈይቶአል፤ “እኔ ትልቅ ሰው ነኝ!” እያለም ይናገር ነበር። ሰዎች ሁሉ ትንሹም ትልቁም “ይህ ሰው ታላቅ ተብሎ የሚጠራው የእግዚአብሔር ኀይል ነው!” እያሉ በጥንቃቄ ያዳምጡት ነበር። በጥንቃቄ ያዳምጡት የነበረውም ከብዙ ጊዜ ጀምሮ በጥንቈላ ያስደንቃቸው ስለ ነበረ ነው። ነገር ግን ፊልጶስ ስለ እግዚአብሔር መንግሥትና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተናገረውን መልካም ዜና በሰሙ ጊዜ ወንዶችም ሴቶችም አምነው ተጠመቁ። ስምዖን እንኳን ሳይቀር አምኖ ተጠመቀና ከፊልጶስ ጋር ተባባሪ ሆነ፤ የሚደረጉትንም ድንቅ ነገሮችና ታላላቅ ተአምራት በማየቱ ይገረም ነበር። በኢየሩሳሌም የነበሩት ሐዋርያት የሰማርያ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል መቀበላቸውን በሰሙ ጊዜ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ወደ ሰማርያ ላኩአቸው። ስለዚህ የሰማርያ ሰዎች መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበሉ ጴጥሮስና ዮሐንስ ሄደው ጸለዩላቸው። የሰማርያ ሰዎች በጌታ ኢየሱስ ስም ተጠምቀው ነበር እንጂ መንፈስ ቅዱስ ገና በአንዳቸውም ላይ አልወረደም ነበር። ስለዚህ ጴጥሮስና ዮሐንስ፥ እጆቻቸውን በጫኑባቸው ጊዜ ሰዎቹ መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ። ሐዋርያት እጆቻቸውን ሲጭኑባቸው መንፈስ ቅዱስ ለሰዎቹ መሰጠቱን ስምዖን ባየ ጊዜ ገንዘብ አመጣላቸውና፥ “እኔም እጄን የምጭንበት ሰው መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበል ይህን ሥልጣን ስጡኝ” አለ። ጴጥሮስ ግን እንዲህ አለው፦ “የእግዚአብሔርን ስጦታ በገንዘብ ለማግኘት በማሰብህ ገንዘብህ ካንተ ጋር ይጥፋ! ልብህ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ስላልሆነ አንተ ከዚህ ነገር ክፍል ወይም ዕጣ የለህም። እንግዲህ ከዚህ ከክፋትህ ተጸጽተህ ንስሓ ግባ፤ ምናልባት የልብህን ክፉ አሳብ ይቅር ይልልህ እንደ ሆነ እግዚአብሔርን ለምን። አንተ በመራራ ቅናት እንደ ተሞላህና የኃጢአት እስረኛ እንደ ሆንክ አያለሁ።” ስምዖንም “አሁን ከተናገራችሁት አንዳች እንኳን እንዳይደርስብኝ እናንተው ራሳችሁ ወደ ጌታ ጸልዩልኝ” አላቸው። ጴጥሮስና ዮሐንስ ከመሰከሩና የጌታንም ቃል ከተናገሩ በኋላ በብዙ የሰማርያ መንደሮች ወንጌልን እያበሠሩ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። የጌታ መልአክ ፊልጶስን፥ “ተነሥና ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ በሚወስደው መንገድ ወደ ደቡብ ሂድ” አለው፤ ያ መንገድ የበረሓ መንገድ ነበር። እርሱም ተነሥቶ ሄደ፤ እነሆ፥ አንድ ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ ለእግዚአብሔር ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ ነበር፤ ይህ ሰው ሕንደኬ ለተባለች የኢትዮጵያ ንግሥት ባለሟልና የገንዘብዋ ሁሉ ኀላፊ ነበረ። እርሱ ወደ አገሩ ሲመለስ በሠረገላ ተቀምጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብ ነበር። በዚህ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ፊልጶስን “ሂድ ወደዚያ ሠረገላ ቅረብና ተገናኘው” አለው። ስለዚህ ፊልጶስ ወደዚያ ሮጦ ሄደና ኢትዮጵያዊው የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ሲያነብ ሰምቶ “የምታነበው ትርጒሙ ይገባሃልን?” አለው። ኢትዮጵያዊውም “የሚያስረዳኝ ሰው ሳይኖር እንዴት ሊገባኝ ይችላል?” አለና ፊልጶስን “ወደ ሠረገላው ውጣና ከእኔ ጋር ተቀመጥ” አለው። እርሱም ያነበው የነበረው የቅዱስ መጽሐፍ ክፍል የሚከተለው ነበረ፦ “እርሱ ለመታረድ እንደሚነዳ በግ ነበረ፤ ሲሸልቱትም ዝም እንደሚል ጠቦት፤ እርሱም ለመናገር አፉን አልከፈተም። እርሱ ተዋረደ፤ ቅን ፍርድም አልተሰጠውም፤ ሕይወቱም ከምድር ተወግዶአልና ስለ ትውልዱ ማን ሊናገር ይችላል?” ጃንደረባውም ፊልጶስን፥ “ነቢዩ ይህን የተናገረው ስለ ማን ነው? ስለ ራሱ ነውን ወይስ ስለሌላ? እባክህን ንገረኝ” አለው። ፊልጶስም ከዚህ የቅዱስ መጽሐፍ ክፍል ጀምሮ ስለ ኢየሱስ መልካሙን ዜና አበሠረው። ሲሄዱም ውሃ ወዳለበት ቦታ ደረሱ፤ ጃንደረባውም “እነሆ፥ እዚህ ውሃ አለ፤ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ነገር ምንድን ነው?” አለ። [ ፊልጶስም “በሙሉ ልብህ ካመንክ መጠመቅ ትችላለህ” አለው። ጃንደረባውም “ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን አምናለሁ” አለ።] ጃንደረባው ሠረገላው እንዲቆም አዘዘ፤ ሁለቱም ወደ ውሃው ወረዱና ፊልጶስ ጃንደረባውን አጠመቀው። ከውሃው ከወጡ በኋላ የጌታ መንፈስ ፊልጶስን ወሰደው፤ ጃንደረባውም ዳግመኛ አላየውም፤ ይሁን እንጂ ደስ እያለው ጒዞውን ቀጠለ። ፊልጶስ ግን በአዞጦስ ተገኘ፤ ወደ ቂሳርያም እስከ መጣ ድረስ በየከተሞቹ ሁሉ እየሄደ ወንጌልን ይሰብክ ነበር።
የሐዋርያት ሥራ 8 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሐዋርያት ሥራ 8:4-40
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች