ሐዋርያት ሥራ 8:4-40

ሐዋርያት ሥራ 8:4-40 NASV

የተበተኑትም በሄዱበት ሁሉ ቃሉን ሰበኩ፤ ፊልጶስም ወደ አንዲት የሰማርያ ከተማ ወርዶ ክርስቶስን ሰበከላቸው። ብዙ ሕዝብም ፊልጶስ የተናገረውን ሲሰሙና ያደረገውንም ታምራዊ ምልክቶች ሲያዩ፣ አንድ ልብ ሆነው ያዳምጡት ነበር። ርኩሳን መናፍስትም እየጮኹ ከብዙ ሰዎች ወጡ፤ ብዙ ሽባዎችና ዐንካሶችም ተፈወሱ፤ ከዚህ የተነሣም በከተማዪቱ ታላቅ ደስታ ሆነ። ነገር ግን ከዚህ ቀደም ሲል በከተማዪቱ ውስጥ እየጠነቈለ የሰማርያን ሰዎች ሁሉ ያስገረመ፣ ሲሞን የሚሉት አንድ ሰው ነበር፤ እርሱም ራሱን እንደ ታላቅ ሰው ይቈጥር ነበር። ከታናሽ እስከ ታላቅ ያለው ሰው ሁሉ፣ “ይህ ሰው ‘ታላቁ ኀይል’ በመባል የሚታወቀው መለኮታዊ ኀይል ነው” በማለት ከልብ ያዳምጡት ነበር፤ ከብዙ ጊዜ ጀምሮ በጥንቈላ ሥራው ስላስገረማቸውም ትኵረት ሰጥተው ይከተሉት ነበር። ነገር ግን ፊልጶስ ስለ እግዚአብሔር መንግሥትና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም የሰበከላቸውን አምነው በመቀበላቸው ወንዶችም ሴቶችም ተጠመቁ፤ ራሱ ሲሞን እንኳ ሳይቀር አምኖ ተጠመቀ፤ ፊልጶስንም ተከትሎ ሄደ፤ የሚደረገውን ምልክትና ታላቅ ታምራት አይቶም ተገረመ። በኢየሩሳሌም የነበሩት ሐዋርያት የሰማርያ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል መቀበላቸውን በሰሙ ጊዜ፣ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ወደ እነርሱ ላኳቸው። እነርሱም ሰማርያ በደረሱ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበሉ ለሰማርያ ሰዎች ጸለዩላቸው፤ ምክንያቱም በዚያ ጊዜ በጌታ ኢየሱስ ስም ተጠምቀው ነበር እንጂ ገና መንፈስ ቅዱስ በአንዳቸውም ላይ አልወረደም ነበር። ስለዚህ ጴጥሮስና ዮሐንስ እጃቸውን ጫኑባቸው፤ እነርሱም መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ። ሲሞንም ሐዋርያት እጃቸውን በሚጭኑበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ እንደሚሰጥ አይቶ፣ ገንዘብ አመጣላቸውና እንዲህ አላቸው፤ “እጄን የምጭንበት ሰው ሁሉ መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበል ይህን ሥልጣን ለእኔም ስጡኝ።” ጴጥሮስ ግን እንዲህ አለው፤ “የእግዚአብሔርን ስጦታ በገንዘብ ለመግዛት አስበሃልና፣ አንተም ገንዘብህም ዐብራችሁ ጥፉ! ልብህ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ስላልሆነ፣ አንተ በዚህ አገልግሎት ድርሻ ወይም ዕድል ፈንታ የለህም። አሁንም ስለዚህ ክፋትህ ንስሓ ግባ፤ ወደ ጌታም ጸልይ፤ ምናልባት ይህን የልብህን ሐሳብ ይቅር ይልህ ይሆናል፤ ምክንያቱም በመራራነት ተሞልተህ፣ በዐመፅ ሰንሰለት ተይዘህ አይሃለሁና።” ሲሞንም መልሶ፣ “ከተናገራችሁት ምንም ነገር እንዳይደርስብኝ ጌታን ለምኑልኝ” አላቸው። ጴጥሮስና ዮሐንስም የጌታን ቃል ከመሰከሩና ገልጠው ከተናገሩ በኋላ፣ በብዙ የሰማርያ መንደሮች ወንጌልን እየሰበኩ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። የጌታም መልአክ ፊልጶስን፣ “ተነሥተህ በደቡብ በኩል ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ በሚያወርደው በምድረ በዳው መንገድ ሂድ” አለው፤ እርሱም ተነሥቶ ሄደ። እነሆ፤ የኢትዮጵያ ንግሥት የህንደኬ ባለሟልና የሀብት ንብረቷ ሁሉ አዛዥ የሆነ አንድ ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ አገኘ። ይህም ሰው ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ነበር። ሲመለስም በሠረገላ ተቀምጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብብ ነበር። መንፈስም ፊልጶስን፣ “ሂድ፤ ወደዚህ ሠረገላ ቅረብ” አለው። ፊልጶስም ፈጥኖ ወደ ሠረገላው ሄደ፤ ጃንደረባውም የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ሲያነብብ ሰምቶ፣ “ለመሆኑ፣ የምታነብበውን ታስተውለዋለህን?” አለው። ጃንደረባውም፣ “የሚያስረዳኝ ሰው ሳይኖር እንዴት አድርጌ አስተውላለሁ” አለው፤ እርሱም ወደ ሠረገላው ወጥቶ ዐብሮት እንዲቀመጥ ፊልጶስን ለመነው። ጃንደረባው ያነብብ የነበረው የመጽሐፍ ክፍል ይህ ነበር፤ “እንደ በግ ወደ መታረድ ተነዳ፤ በሸላቹ ፊት ዝም እንደሚል በግ፣ አፉን አልከፈተም። ራሱን በማዋረዱም ፍትሕን ተነፈገ፤ ሕይወቱ ከምድር ተወግዳለችና፣ ስለ ትውልዱ ማን ሊናገር ይችላል?” ጃንደረባውም መልሶ ፊልጶስን፣ “ነቢዩ ይህን የሚናገረው ስለ ማን ነው? ስለ ራሱ ነው ወይስ ስለ ሌላ ሰው? እባክህ ንገረኝ” አለው። ፊልጶስም አፉን ከፈተ፤ ከዚሁም መጽሐፍ ክፍል ጀምሮ ስለ ኢየሱስ ወንጌል ሰበከለት። በመጓዝ ላይ ሳሉም ውሃ ካለበት ስፍራ ደረሱ፤ ጃንደረባውም፣ “እነሆ፤ ውሃ እዚህ አለ፤ ታዲያ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምን ነገር አለ?” አለው። [ፊልጶስም፣ “በፍጹም ልብህ ካመንህ መጠመቅ ትችላለህ” አለው። ጃንደረባውም፣ “ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ አምናለሁ” ሲል መለሰለት፤] ሠረገላውም እንዲቆም አዘዘ። ከዚያም ሁለቱ ዐብረው ወደ ውሃው ወረዱ፤ ፊልጶስም ጃንደረባውን አጠመቀው። ከውሃውም በወጡ ጊዜ፣ የጌታ መንፈስ ፊልጶስን ነጥቆ ወሰደው፤ ጃንደረባውም ከዚህ በኋላ አላየውም፤ ሆኖም ደስ እያለው ጕዞውን ቀጠለ። ከዚያ በኋላ ግን ፊልጶስ በአዛጦን ታየ፤ ቂሳርያም እስኪደርስ ድረስ በሚያልፍባቸው ከተሞች ሁሉ ወንጌልን ይሰብክ ነበር።