2 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 7:4-9

2 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 7:4-9 አማ05

በእናንተ ላይ ያለኝ እምነት ከፍተኛ ነው፤ በእናንተ ላይ ያለኝ ትምክሕት ትልቅ ነው፤ በእናንተም እጽናናለሁ፤ በመከራችን ሁሉ በጣም እደሰታለሁ። መቄዶንያ በደረስን ጊዜ እንኳ ከብዙ አቅጣጫ ችግር ደረሰብን እንጂ ምንም ዕረፍት አላገኘንም፤ በውጭ ጠብ በውስጥም ፍርሀት ነበረብን። ነገር ግን የተዋረዱትን የሚያጽናና አምላክ በቲቶ መምጣት አጽናናን። የተጽናናነውም በእርሱ መምጣት ብቻ ሳይሆን እናንተ እርሱን ያጽናናችሁት መሆኑን በመስማታችንም ጭምር ነው፤ ስለ እኔ ያላችሁን ናፍቆትና ሐዘን ጭንቀትም በነገረን ጊዜ ይበልጥ ደስ አለኝ። ከዚህ በፊት የጻፍኩላችሁ መልእክት ያሳዘናችሁ ቢሆንም እንኳ መልእክቱን በመጻፌ አልጸጸትም፤ ተጸጽቼም ብሆን እንኳ የተጸጸትኩት መልእክቴ ለጥቂት ጊዜ ስላሳዘናችሁ ነው። አሁን ግን ደስ ብሎኛል፤ የተደሰትኩበትም ምክንያት እናንተን ስላሳዘንኳችሁ ሳይሆን በሐዘናችሁ ምክንያት ንስሓ ገብታችሁ በመለወጣችሁ ነው፤ እንግዲህ ሐዘናችሁ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ሆነ እኛ ምንም አልበደልናችሁም ማለት ነው።