2 ቆሮንቶስ 7:4-9

2 ቆሮንቶስ 7:4-9 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

በእ​ና​ንተ ዘንድ እን​ዲሁ ብዙ መወ​ደድ አለኝ፤ ስለ እና​ን​ተም የም​መ​ካ​በት ብዙ ነው፤ መጽ​ና​ና​ት​ንም አገ​ኘሁ፤ ከመ​ከ​ራ​ዬም ሁሉ ይልቅ ደስ​ታዬ በዛ​ልኝ። ወደ መቄ​ዶ​ን​ያም በደ​ረ​ስን ጊዜ ለሰ​ው​ነ​ታ​ችን ጥቂት ስን​ኳን ዕረ​ፍት አላ​ገ​ኘ​ንም፤ በሁ​ሉም መከራ አጸ​ኑ​ብን እንጂ፤ በው​ጭም መጋ​ደል ነበር፤ በው​ስ​ጥም ፍር​ሀት ነበር። ነገር ግን ያዘ​ኑ​ትን የሚ​ያ​ጽ​ናና እርሱ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በቲቶ መም​ጣት አጽ​ና​ናን። በመ​ም​ጣቱ ብቻ አይ​ደ​ለም፤ በአ​ጽ​ና​ና​ች​ሁት ማጽ​ና​ና​ትም ነው እንጂ፤ ለእኛ እን​ደ​ም​ታ​ስ​ቡና እን​ደ​ም​ት​ቀኑ ፍቅ​ራ​ች​ሁን ነግ​ሮ​ናል፤ ይህ​ንም ሰምቼ ደስ​ታዬ በእ​ና​ንተ በዛ። መጀ​መ​ሪያ በጻ​ፍ​ሁት መል​እ​ክት ባሳ​ዝ​ና​ች​ሁም እንኳ አያ​ጸ​ጽ​ተ​ኝም፤ ብጸ​ጸ​ትም፥ እነሆ ያች መል​እ​ክት ለጥ​ቂት ጊዜ ብቻ እን​ዳ​ሳ​ዘ​ነ​ቻ​ችሁ አያ​ለሁ። አሁን ግን እኔ ስለ እርሷ በብዙ ደስ ይለ​ኛል፤ ደስ​ታ​ዬም ስለ አዘ​ና​ችሁ አይ​ደ​ለም፤ ንስሓ ልት​ገቡ ስለ አዘ​ና​ችሁ እንጂ፤ ከእ​ና​ንተ አንዱ ስንኳ እን​ዳ​ይ​ጠፋ፥ ስለ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ብላ​ችሁ አዝ​ና​ች​ኋ​ልና።

2 ቆሮንቶስ 7:4-9 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በእናንተ ላይ ያለኝ እምነት ትልቅ ነው፤ በእናንተም ላይ ያለኝ ትምክሕት ትልቅ ነው፤ እንዲሁም እጅግ ተጽናንቻለሁ፤ በመከራችንም ሁሉ ደስታዬ ወሰን የለውም። ወደ መቄዶንያ በመጣን ጊዜ፣ ከየአቅጣጫው መከራ ደረሰብን እንጂ ሰውነታችን ዕረፍት አላገኘም፤ ከውጭ ጠብ፣ ከውስጥ ደግሞ ፍርሀት ነበረብን። ይሁን እንጂ ሐዘንተኞችን የሚያጽናና አምላክ በቲቶ መምጣት አጽናናን። የተጽናናነውም በመምጣቱ ብቻ ሳይሆን፣ እርሱንም ልታጽናኑት በመቻላችሁ ጭምር ነው። ስለ ናፍቆታችሁ፣ ስለ ሐዘናችሁና ለእኔም ስላላችሁ ቅናት ነግሮናል፤ ስለዚህ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ደስ ብሎኛል። በመልእክቴ ባሳዝናችሁም በዚህ አልጸጸትም፤ ብጸጸትም እንኳ መልእክቴ ያሳዘናችሁ ለጥቂት ጊዜ እንደ ሆነ ተረድቻለሁ። አሁን ግን ደስ ብሎኛል፤ ደስታዬም ስላዘናችሁ ሳይሆን፣ ሐዘናችሁ ንስሓ ለመግባት ስላበቃችሁ ነው፤ ምክንያቱም ሐዘናችሁ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ ከእኛ የተነሣ ምንም አልተጐዳችሁም።

2 ቆሮንቶስ 7:4-9 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

በእናንተ ላይ ያለኝ እምነት ከፍተኛ ነው፤ በእናንተ ላይ ያለኝ ትምክሕት ትልቅ ነው፤ በእናንተም እጽናናለሁ፤ በመከራችን ሁሉ በጣም እደሰታለሁ። መቄዶንያ በደረስን ጊዜ እንኳ ከብዙ አቅጣጫ ችግር ደረሰብን እንጂ ምንም ዕረፍት አላገኘንም፤ በውጭ ጠብ በውስጥም ፍርሀት ነበረብን። ነገር ግን የተዋረዱትን የሚያጽናና አምላክ በቲቶ መምጣት አጽናናን። የተጽናናነውም በእርሱ መምጣት ብቻ ሳይሆን እናንተ እርሱን ያጽናናችሁት መሆኑን በመስማታችንም ጭምር ነው፤ ስለ እኔ ያላችሁን ናፍቆትና ሐዘን ጭንቀትም በነገረን ጊዜ ይበልጥ ደስ አለኝ። ከዚህ በፊት የጻፍኩላችሁ መልእክት ያሳዘናችሁ ቢሆንም እንኳ መልእክቱን በመጻፌ አልጸጸትም፤ ተጸጽቼም ብሆን እንኳ የተጸጸትኩት መልእክቴ ለጥቂት ጊዜ ስላሳዘናችሁ ነው። አሁን ግን ደስ ብሎኛል፤ የተደሰትኩበትም ምክንያት እናንተን ስላሳዘንኳችሁ ሳይሆን በሐዘናችሁ ምክንያት ንስሓ ገብታችሁ በመለወጣችሁ ነው፤ እንግዲህ ሐዘናችሁ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ሆነ እኛ ምንም አልበደልናችሁም ማለት ነው።

2 ቆሮንቶስ 7:4-9 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ስለ እናንተ እምነቴ ታላቅ ነው፤ በእናንተ ምክንያት ትምክህቴ ታላቅ ነው፤ እኔም በመጽናናት ተሞልቻለሁ፤ በመከራችን ሁሉ ደስታዬ ወሰን የለውም። ወደ መቄዶንያም በመጣን ጊዜ፥ በሁሉ ነገር መከራን ተቀበልን እንጂ ሰውነታችን ዕረፍት አልነበረውም፤ ከውጭ ጠብ ነበረ፤ ከውስጥ ደግሞ ፍርሃት ነበረብን። ነገር ግን ኀዘንተኞችን የሚያጽናና አምላክ በቲቶ መምጣት አጽናናን፤ በመምጣቱም ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን ናፍቆታችሁንና ልቅሶአችሁን ስለ እኔም የነበራችሁን ቅንዓት ሲነገረን በእናንተ ስለተጽናናን ማለቴ ነው፤ ስለዚህም ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ደስ አለኝ። በመልእክቴ ያሳዘንኋችሁ ብሆን እንኳ አልጸጸትም፤ የተጸጸትሁ ብሆን እንኳ፥ ያ መልእክት ለጥቂት ጊዜ ብቻ እንዳሳዘናችሁ ተረድቻለሁ፤ አሁን ግን ሐዘናችሁ ወደ ንስሓ ስለመራችሁ ደስ ብሎኛል እንጂ ደስታዬ ስለ ሐዘናችሁ አይደለም፤ በማንኛውም መንገድ በእኛ በኩል እንድትጎዱ አንፈልግም።