ደግሞም ወደ ላይ ተመለከትሁ፤ እነሆ፤ በእጁ የመለኪያ ገመድ የያዘ ሰውም በፊቴ አየሁ፤ እኔም፣ “የት ልትሄድ ነው?” አልሁት። እርሱም፣ “የኢየሩሳሌም ርዝመትና ስፋት ምን ያህል እንደ ሆነ ለመለካት መሄዴ ነው፤” አለኝ። ከእኔ ጋራ ይነጋገር የነበረው መልአክም ሄደ፤ ሌላም መልአክ ሊገናኘው መጣ፤ እንዲህም አለው፣ “ሩጥና ለዚያ ጕልማሳ እንዲህ ብለህ ንገረው፤ ‘በውስጧ ካለው የሰውና የከብት ብዛት የተነሣ፣ ኢየሩሳሌም ቅጥር እንደሌላት ከተማ ትሆናለች፤ እኔ ራሴ በዙሪያዋ የእሳት ቅጥር እሆንላታለሁ’ ይላል እግዚአብሔር፣ ‘በውስጧም ክብሯ እሆናለሁ።’ “ኑ! ኑ! ውጡ፤ ከሰሜን ምድር አምልጡ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ለአራቱ የሰማይ ነፋሳት በትኛችኋለሁና” ይላል እግዚአብሔር። “አንቺ ጽዮን ነዪ፤ ከባቢሎን ሴት ልጅ ጋራ የምትኖሪ ሆይ፤ ኰብልዪ።” የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ “ካከበረኝና በዘረፏችሁ አሕዛብ ላይ ከላከኝ በኋላ፣ የሚነካችሁ የዐይኑን ብሌን ይነካል፤ እነሆ፤ እጄን በእነርሱ ላይ አነሣለሁ፤ ባሪያዎቻቸውም ይዘርፏቸዋል፤ ከዚያም የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እኔን እንደ ላከኝ ታውቃላችሁ። “የጽዮን ልጅ ሆይ፤ እልል በዪ፤ ደስም ይበልሽ፤ እኔ እመጣለሁና፤ በመካከልሽም እኖራለሁ” ይላል እግዚአብሔር። “በዚያ ቀን ብዙ አሕዛብ ወደ እግዚአብሔር ይጠጋሉ፤ የእኔም ሕዝብ ይሆናሉ። በመካከልሽ እኖራለሁ፤ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ወደ አንቺ እንደ ላከኝም ታውቃላችሁ። እግዚአብሔርም በተቀደሰችው ምድር ይሁዳን ርስቱ አድርጎ ይወርሳል፤ ኢየሩሳሌምንም እንደ ገና ይመርጣል። እግዚአብሔር ከተቀደሰ ማደሪያው ተነሥቷልና፣ ሥጋ ለባሽ ሁሉ ሆይ፤ በፊቱ ጸጥ በል።”
ዘካርያስ 2 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘካርያስ 2
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘካርያስ 2:1-13
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች