ዘካርያስ 2:1-13

ዘካርያስ 2:1-13 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ዓይኖቼንም አነሣሁ፣ እነሆም፥ በእጁ የመለኪያ ገመድ የያዘ አንድ ሰውን አየሁ። እኔም፦ አንተ ወዴት ትሄዳለህ? አልሁ። እርሱም፦ የኢየሩሳሌምን ወርድና ርዝመት ስንት መሆኑን ሰፍሬ አይ ዘንድ እሄዳለሁ አለኝ። እነሆም፥ ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ ወጣ፥ ሌላም መልአክ ሊገናኘው ወጣ፥ እንዲህም አለው፦ ሩጥ፥ ይህንም ጕልማሳ እንዲህ በለው፦ ኢየሩሳሌም በውስጥዋ ካሉት ሰዎችና እንስሶች ብዛት የተነሣ ቅጥር እንደሌላቸው መንደሮች ሆና ትኖራለች። እኔ በዙሪያዋ የእሳት ቅጥር እሆንላታለሁ፥ በውስጥዋም ክብርን እሆናለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። እናንተ ሆይ፥ ከሰሜን ምድር ሽሹ፥ ይላል እግዚአብሔር፣ እንደ አራቱ የሰማይ ነፋሳት በትኛችኋለሁና፥ ይላል እግዚአብሔር። አንቺ ከባቢሎን ሴት ልጅ ጋር የምትኖሪ ጽዮን ሆይ፥ ኰብልዪ። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ ከክብሩ በኋላ ወደ በዘበዙአችሁ አሕዛብ ልኮኛል፣ የሚነካችሁ የዓይኑን ብሌን የሚነካ ነውና። እነሆ፥ እጄን በላያቸው አወዛውዛለሁ፥ ተገዝተው ለነበሩት ብዝበዛ ይሆናሉ፣ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም እንደ ላከኝ ታውቃላችሁ። የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እነሆ፥ መጥቼ በመካከልሽ እኖራለሁና ዘምሪ ደስም ይበልሽ፥ ይላል እግዚአብሔር። በዚያም ቀን ብዙ አሕዛብ ወደ እግዚአብሔር ይጠጋሉ፥ ሕዝብም ይሆኑኛል፣ በመካከልሽም እኖራለሁ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ወደ አንቺ እንደ ላከኝ ታውቂአለሽ። እግዚአብሔርም ይሁዳን እድል ፈንታው አድርጎ በተቀደሰችው ምድር ይወርሰዋል፥ ኢየሩሳሌምንም ዳግመኛ ይመርጣል። እግዚአብሔር ከተቀደሰ ማደሪያው ነቅቶአልና ሥጋ ለባሽ ሁሉ ሆይ፥ በፊቱ ዝም በል።

ዘካርያስ 2:1-13 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ደግሞም ወደ ላይ ተመለከትሁ፤ እነሆ፤ በእጁ የመለኪያ ገመድ የያዘ ሰውም በፊቴ አየሁ፤ እኔም፣ “የት ልትሄድ ነው?” አልሁት። እርሱም፣ “የኢየሩሳሌም ርዝመትና ስፋት ምን ያህል እንደ ሆነ ለመለካት መሄዴ ነው፤” አለኝ። ከእኔ ጋራ ይነጋገር የነበረው መልአክም ሄደ፤ ሌላም መልአክ ሊገናኘው መጣ፤ እንዲህም አለው፣ “ሩጥና ለዚያ ጕልማሳ እንዲህ ብለህ ንገረው፤ ‘በውስጧ ካለው የሰውና የከብት ብዛት የተነሣ፣ ኢየሩሳሌም ቅጥር እንደሌላት ከተማ ትሆናለች፤ እኔ ራሴ በዙሪያዋ የእሳት ቅጥር እሆንላታለሁ’ ይላል እግዚአብሔር፣ ‘በውስጧም ክብሯ እሆናለሁ።’ “ኑ! ኑ! ውጡ፤ ከሰሜን ምድር አምልጡ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ለአራቱ የሰማይ ነፋሳት በትኛችኋለሁና” ይላል እግዚአብሔር። “አንቺ ጽዮን ነዪ፤ ከባቢሎን ሴት ልጅ ጋራ የምትኖሪ ሆይ፤ ኰብልዪ።” የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ “ካከበረኝና በዘረፏችሁ አሕዛብ ላይ ከላከኝ በኋላ፣ የሚነካችሁ የዐይኑን ብሌን ይነካል፤ እነሆ፤ እጄን በእነርሱ ላይ አነሣለሁ፤ ባሪያዎቻቸውም ይዘርፏቸዋል፤ ከዚያም የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እኔን እንደ ላከኝ ታውቃላችሁ። “የጽዮን ልጅ ሆይ፤ እልል በዪ፤ ደስም ይበልሽ፤ እኔ እመጣለሁና፤ በመካከልሽም እኖራለሁ” ይላል እግዚአብሔር። “በዚያ ቀን ብዙ አሕዛብ ወደ እግዚአብሔር ይጠጋሉ፤ የእኔም ሕዝብ ይሆናሉ። በመካከልሽ እኖራለሁ፤ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ወደ አንቺ እንደ ላከኝም ታውቃላችሁ። እግዚአብሔርም በተቀደሰችው ምድር ይሁዳን ርስቱ አድርጎ ይወርሳል፤ ኢየሩሳሌምንም እንደ ገና ይመርጣል። እግዚአብሔር ከተቀደሰ ማደሪያው ተነሥቷልና፣ ሥጋ ለባሽ ሁሉ ሆይ፤ በፊቱ ጸጥ በል።”

ዘካርያስ 2:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ዓይኖቼንም አነሣሁ፥ እነሆም፥ በእጁ የመለኪያ ገመድ የያዘ አንድ ሰውን አየሁ። እኔም፦ አንተ ወዴት ትሄዳለህ? አልሁ። እርሱም፦ የኢየሩሳሌምን ወርድና ርዝመት ስንት መሆኑን ሰፍሬ አይ ዘንድ እሄዳለሁ አለኝ። እነሆም፥ ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ ወጣ፥ ሌላም መልአክ ሊገናኘው ወጣ፥ እንዲህም አለው፦ ሩጥ፥ ይህንም ጕልማሳ እንዲህ በለው፦ ኢየሩሳሌም በውስጥዋ ካሉት ሰዎችና እንስሶች ብዛት የተነሣ ቅጥር እንደሌላቸው መንደሮች ሆና ትኖራለች። እኔ በዙሪያዋ የእሳት ቅጥር እሆንላታለሁ፥ በውስጥዋም ክብርን እሆናለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። እናንተ ሆይ፥ ከሰሜን ምድር ሽሹ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ እንደ አራቱ የሰማይ ነፋሳት በትኛችኋለሁና፥ ይላል እግዚአብሔር። አንቺ ከባቢሎን ሴት ልጅ ጋር የምትኖሪ ጽዮን ሆይ፥ ኰብልዪ። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ ከክብሩ በኋላ ወደ በዘበዙአችሁ አሕዛብ ልኮኛል፥ የሚነካችሁ የዓይኑን ብሌን የሚነካ ነውና። እነሆ፥ እጄን በላያቸው አወዛውዛለሁ፥ ተገዝተው ለነበሩት ብዝበዛ ይሆናሉ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም እንደ ላከኝ ታውቃላችሁ። የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እነሆ፥ መጥቼ በመካከልሽ እኖራለሁና ዘምሪ ደስም ይበልሽ፥ ይላል እግዚአብሔር። በዚያም ቀን ብዙ አሕዛብ ወደ እግዚአብሔር ይጠጋሉ፥ ሕዝብም ይሆኑኛል፥ በመካከልሽም እኖራለሁ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ወደ አንቺ እንደ ላከኝ ታውቂአለሽ። እግዚአብሔርም ይሁዳን እድል ፈንታው አድርጎ በተቀደሰችው ምድር ይወርሰዋል፥ ኢየሩሳሌምንም ዳግመኛ ይመርጣል። እግዚአብሔር ከተቀደሰ ማደሪያው ነቅቶአልና ሥጋ ለባሽ ሁሉ ሆይ፥ በፊቱ ዝም በል።

ዘካርያስ 2:1-13 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

በሌላም ራእይ በእጁ የመለኪያ ገመድ የያዘ አንድ ሰው አየሁ፤ እኔም “ወዴት እየሄድክ ነው?” ብዬ ጠየቅሁት፤ እርሱም “የኢየሩሳሌም ርዝመትና ስፋት ምን ያኽል እንደ ሆነ ለመለካት መሄዴ ነው” አለኝ። ከዚህ በኋላ ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ ወደፊት ሲራመድና ሌላ መልአክም ሊገናኘው ሲመጣ አየሁ። የመጀመሪያው መልአክ ሁለተኛውን እንዲህ አለው፦ “የመለኪያ ገመድ ወደያዘው ወጣት በሩጫ ሂድና ‘በኢየሩሳሌም ብዙ ሕዝብና ብዙ እንስሶች ስለሚገኙ ትልቅ ግንብ መሥራት ያዳግታል’ ብለህ ንገረው። እግዚአብሔር ራሱ በዙሪያዋ እንደ እሳት ቅጽር ሆኖ ከተማይቱን እንደሚጠብቅና በክብሩም በዚያ እንደሚኖር ተስፋ ሰጥቶአል።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በየአራቱም ማእዘን በትኜአችሁ ነበር፤ አሁን ግን ከሰሜን ምድር ተነሥታችሁ ሽሹ። በባቢሎን የምትኖሩ እናንተ ስደተኞች ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።” እናንተን የሚነካ የእርሱን ዓይን ብሌን እንደሚነካ ሆኖ ይቈጠራል። የክብር ጌታ በበዘበዙአችሁ ሕዝቦች ላይ በላከኝ ጊዜ የተናገራቸው ቃላት እነዚህ ናቸው። “አሁን እኔ በእነርሱ ላይ እጄን አነሣለሁ፤ እነርሱም ባሪያዎች አድርገው ለገዙአቸው ምርኮኞች ይሆናሉ፤ ከዚያ በኋላ እናንተም የሠራዊት አምላክ እኔን እንደ ላከኝ ታውቃላችሁ። “እኔ መጥቼ በመካከላችሁ ስለምኖር የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሆይ! ዘምሩ! ደስም ይበላችሁ!” ይላል እግዚአብሔር። በዚያን ጊዜ ብዙ የአሕዛብ ነገዶች ከእግዚአብሔር ጋር ተባብረው ወገኖቹ ይሆናሉ። እርሱም በመካከላችሁ ይኖራል፤ እኔንም ወደ እናንተ የላከኝ እርሱ መሆኑን ትገነዘባላችሁ። በተቀደሰችው ምድር ይሁዳን የራሱ ርስት ያደርጋታል፤ ኢየሩሳሌምንም እንደገና ይመርጣታል። እግዚአብሔር ከተቀደሰ መኖሪያው ለመምጣት ስለ ተነሣ ሁላችሁም በፊቱ ዝም በሉ።

ዘካርያስ 2:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ዐይኖቼንም አንሥቼ እነሆም አራት ቀንዶች አየሁ። ከዚያም ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረውን መልአክ፦ “እነዚህ ምንድን ናቸው?” አልሁት። እርሱም፦ “እነዚህ ይሁዳን፥ እስራኤልንና ኢየሩሳሌምን የበተኑ ቀንዶች ናቸው” ብሎ መለሰልኝ። ጌታም አራት ጠራቢዎች አሳየኝ። እኔም፦ “እነዚህ የመጡት ምን ሊሠሩ ነው?” አልኩት። እርሱም፦ “አንድ ሰው ራሱን ቀና ማድረግ እስኪሳነው ድረስ እነዚህ ቀንዶች ይሁዳን የበተኑ ናቸው፤ እነዚህ ግን ሊያስፈራሯቸው፥ የይሁዳንም አገር ለመበተን ቀንዳቸውን ያነሡትን የአሕዛብን ቀንዶች ሊቆርጡ መጥተዋል” ብሎ ተናገረ። ዐይኖቼንም አነሣሁ፥ እነሆም፥ በእጁ የመለኪያ ገመድ የያዘ አንድ ሰውን አየሁ። እኔም፦ “አንተ ወዴት ነው የምትሄደው?” አልኩት። እርሱም፦ “ኢየሩሳሌምን ልለካትና ወርድና ርዝመቷ ስንት መሆኑን ለማየት ነው የምሄደው” አለኝ። እነሆም፥ ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ ሌላ መልአክ ሊገናኘው እንደመጣ እርሱም ወጣ፥ እንዲህም አለው፦ “ሩጥ፥ ይህንም ጎልማሳ እንዲህ በለው፦ ኢየሩሳሌም በውስጥዋ ካሉት ሰዎችና እንስሶች ብዛት የተነሣ ቅጥር እንደሌላቸው መንደሮች ትሆናለች። እኔ በዙሪያዋ የእሳት ቅጥር እሆንላታለሁ፥ በመካከሏም ክብር እሆናለሁ፥ ይላል ጌታ።” ተነሡ! ተነሡ! ከሰሜን ምድር ሽሹ፥ ይላል ጌታ፤ እንደ አራቱ የሰማይ ነፋሳት በትኛችኋለሁና፥ ይላል ጌታ። አንቺ ከባቢሎን ሴት ልጅ ጋር የምትኖሪ ጽዮን ሆይ፥ ተነሽ፥ ኰብልይ። የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላልና፦ ከክብሩ በኋላ ወደ ዘረፏችሁ አሕዛብ ልኮኛል፥ የሚነካችሁ በቀጥታ እኔን የዓይኔን ብሌን ይነካል። እነሆ፥ እጄን በላያቸው ላይ አነሣለሁ፥ በምርኮ ተገዝተውላቸው ለነበሩት ራሳቸው በምርኮ ይዘረፋሉ፤ የሠራዊት ጌታም እንደ ላከኝ ታውቃላችሁ።