እነሆ፤ የእግዚአብሔር ቀን ይመጣል፤ ብዝበዛሽንም በውስጥሽ ይካፈላሉ። ኢየሩሳሌምን እንዲወጉ አሕዛብን ሁሉ እሰበስባለሁ፤ ከተማዪቱ ትያዛለች፤ ቤቶች ይበዘበዛሉ፤ ሴቶችም ይደፈራሉ፤ የከተማዪቱ እኩሌታ ይማረካል፤ የሚቀረው ሕዝብ ግን ከከተማዪቱ አይወሰድም። እግዚአብሔርም በጦርነት ጊዜ እንደሚዋጋ፣ እነዚያን አሕዛብ ሊወጋ ይወጣል። በዚያ ቀን እግሮቹ ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ይቆማሉ፤ የደብረ ዘይት ተራራም ታላቅ ሸለቆን በመሥራት የተራራውን እኩሌታ ወደ ሰሜን፣ እኩሌታውንም ወደ ደቡብ በማድረግ ምሥራቅና ምዕራብ ሆኖ ለሁለት ይከፈላል፤ እናንተም በእግዚአብሔር ተራራ ሸለቆ በኩል በይሁዳ ንጉሥ በዖዝያን ዘመን በምድር ትሸሻላችሁ፤ ሸለቆው እስከ አጸል ይደርሳልና። በምድር መናወጥ ምክንያት ሸሽታችሁ እንደ ነበረ ትሸሻላችሁ፤ ከዚያም አምላኬ እግዚአብሔር ይመጣል፤ ቅዱሳኑም ሁሉ ዐብረውት ይመጣሉ። በዚያ ቀን በረዶ፣ ውርጭና ብርሃን አይኖርም። ቀኑም የብርሃን ወይም የጨለማ ጊዜ የሌለበት ልዩ ቀን ይሆናል፤ ያም ቀን በእግዚአብሔር የታወቀ ቀን ይሆናል፤ ሲመሽም ብርሃን ይሆናል። በዚያ ቀን የሕይወት ውሃ ከኢየሩሳሌም ይፈልቃል፤ እኩሌታው ወደ ምሥራቁ ባሕር፣ እኩሌታውም ወደ ምዕራቡ ባሕር ይፈስሳል፤ ይህም በበጋና በክረምት ይሆናል። እግዚአብሔር በምድር ሁሉ ላይ ይነግሣል፤ በዚያ ቀን እግዚአብሔር አንድ፣ ስሙም አንድ ብቻ ይሆናል። ምድር ሁሉ ከጌባዕ አንሥቶ በኢየሩሳሌም ደቡብ እስካለችው ሪሞን ድረስ ተለውጣ ደልዳላ ሜዳ ትሆናለች፤ ኢየሩሳሌም ግን ከብንያም በር እስከ መጀመሪያው በር፣ ከማእዘን በርና ከሐናንኤል ግንብ እስከ ንጉሡ የወይን ጠጅ መጥመቂያ ድረስ በዚያው በቦታዋ ላይ ከፍ እንዳለች ትኖራለች። የሰው መኖሪያም ትሆናለች፤ ከቶም ዳግመኛ አትፈርስም፤ ኢየሩሳሌም ያለ ሥጋት በሰላም ትኖራለች። እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን የወጓትን አሕዛብ ሁሉ የሚመታበት መቅሠፍት ይህ ነው፤ ገና በእግራቸው ቆመው ሳሉ ሥጋቸው ይበሰብሳል፤ ዐይኖቻቸው በጕድጓዶቻቸው ውስጥ እንዳሉ ይበሰብሳሉ፤ ምላሶቻቸውም በአፎቻቸው ውስጥ እንዳሉ ይበሰብሳሉ። በዚያ ቀን ከእግዚአብሔር ዘንድ በሰዎች ላይ ታላቅ ሽብር ይወርዳል፤ እያንዳንዱ ሰው የባልንጀራውን እጅ ይይዛል፤ አንዱም ሌላውን ይወጋዋል። ይሁዳም ደግሞ ኢየሩሳሌምን ይወጋል። በዙሪያው ያሉ የአሕዛብ ሁሉ ሀብት፣ ብዙ ወርቅ፣ ብርና ልብስ ይሰበሰባል። ይህንኑ የሚመስል መቅሠፍት ፈረሶችንና በቅሎዎችን፣ ግመሎችንና አህዮችን እንዲሁም በየሰፈሩ ያሉትን እንስሳት ሁሉ ይመታል።
ዘካርያስ 14 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘካርያስ 14
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘካርያስ 14:1-15
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች