ዘካርያስ 14:1-15
ዘካርያስ 14:1-15 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እነሆ፥ የእግዚአብሔር ቀን ይመጣል፥ ብዝበዛሽንም በውስጥሽ ይካፈላሉ። አሕዛብንም ሁሉ በኢየሩሳሌም ላይ ለሰልፍ እሰበስባለሁ፣ ከተማይቱም ትያዛለች፥ ቤቶችም ይበዘበዛሉ፥ ሴቶችም ይነወራሉ፣ የከተማይቱም እኵሌታ ለምርኮ ይወጣል፥ የቀረው ሕዝብ ግን ከከተማ አይጠፋም። እግዚአብሔርም ይወጣል፥ በሰልፍም ቀን እንደ ተዋጋ ከእነዚያ አሕዛብ ጋር ይዋጋል። በዚያም ቀን እግሮቹ በኢየሩሳሌም ትይዩ በምሥራቅ በኩል ባለው በደብረ ዘይት ላይ ይቆማሉ፣ ደብረ ዘይትም በመካከል ወደ ምሥራቅና ወደ ምዕራብ ይሰነጠቃል፥ እጅግም ታላቅ ሸለቆ ይሆናል፣ የተራራውም እኵሌታ ወደ ሰሜን፥ እኵሌታውም ወደ ደቡብ ይርቃል። የተራሮችም ሸለቆ እስከ አጸል ይደርሳልና በተራሮች ሸለቆ ትሸሻላችሁ፣ በይሁዳም ንጉሥ በዖዝያን ዘመን ከሆነው ከምድር መናወጥ ፊት እንደ ሸሻችሁ ትሸሻላችሁ፣ አምላኬ እግዚአብሔርም ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ይመጣል። በዚያም ቀን በረዶና ውርጭ እንጂ ብርሃን አይሆንም። አንድ ቀንም ይሆናል፥ እርሱም በእግዚአብሔር ዘንድ የታወቀ ይሆናል፣ ቀንም አይሆንም፥ ሌሊትም አይሆንም፣ ሲመሽም ብርሃን ይሆናል። በዚያም ቀን የሕይወት ውኃ ከኢየሩሳሌም ይወጣል፣ እኵሌታው ወደ ምሥራቁ ባሕር፥ እኵሌታውም ወደ ምዕራቡ ባሕር ይሄዳል፣ ይህ በበጋና በክረምት ይሆናል። እግዚአብሔርም በምድር ሁሉ ላይ ይነግሣል፣ በዚያ ቀን እግዚአብሔር አንድ፥ ስሙም አንድ ይሆናል። ምድር ሁሉ ከጌባ ጀምሮ በኢየሩሳሌምም ደቡብ በኩል እስካለችው እስከ ሬሞን ድረስ ተለውጣ እንደ ዓረባ ትሆናለች፣ እርስዋም ከፍ ከፍ ትላለች፥ ከብንያምም በር ጀምሮ እስከ ፊተኛው በር ስፍራ እስከ ማዕዘኑ በር ድረስ፥ ከሐናንኤልም ግንብ ጀምሮ እስከ ንጉሡ መጥመቂያ ድረስ በስፍራዋ ትኖራለች። ሰዎችም ይኖሩባታል፥ ከዚያም ወዲያ እርግማን አይሆንም፣ ኢየሩሳሌምም ተዘልላ ትኖራለች። እግዚአብሔርም ከኢየሩሳሌም ጋር የተዋጉትን አሕዛብ ሁሉ የሚቀሥፍበት ቸነፈር ይህ ነው፣ በእግራቸው ሲቆሙ ሥጋቸው ይበሰብሳል፥ ዓይኖቻቸውም በዓይነስባቸው ውስጥ ይበሰብሳሉ፥ ምላሳቸውም በአፋቸው ውስጥ ይበሰብሳል። በዚያም ቀን ከእግዚአብሔር ዘንድ ታላቅ ሽብር በእነርሱ ላይ ይሆናል፣ እያንዳንዱም የባልንጀራውን እጅ ይይዛል፥ እጁም በባልንጀራው እጅ ላይ ይነሣል። ይሁዳም ደግሞ በኢየሩሳሌም ውስጥ ሆኖ ይዋጋል፣ በዙሪያም ያሉት የአሕዛብ ሁሉ ሀብት እጅግ ብዙ ወርቅና ብር ልብስም ይሰበሰባል። በፈረስና በበቅሎ፥ በግመልና በአህያ፥ በዚያም ሰፈር ባለ እንስሳ ሁሉ ላይ የሆነ ቸነፈር እንደዚያ ያለ ቸነፈር ይሆናል።
ዘካርያስ 14:1-15 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እነሆ፤ የእግዚአብሔር ቀን ይመጣል፤ ብዝበዛሽንም በውስጥሽ ይካፈላሉ። ኢየሩሳሌምን እንዲወጉ አሕዛብን ሁሉ እሰበስባለሁ፤ ከተማዪቱ ትያዛለች፤ ቤቶች ይበዘበዛሉ፤ ሴቶችም ይደፈራሉ፤ የከተማዪቱ እኩሌታ ይማረካል፤ የሚቀረው ሕዝብ ግን ከከተማዪቱ አይወሰድም። እግዚአብሔርም በጦርነት ጊዜ እንደሚዋጋ፣ እነዚያን አሕዛብ ሊወጋ ይወጣል። በዚያ ቀን እግሮቹ ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ይቆማሉ፤ የደብረ ዘይት ተራራም ታላቅ ሸለቆን በመሥራት የተራራውን እኩሌታ ወደ ሰሜን፣ እኩሌታውንም ወደ ደቡብ በማድረግ ምሥራቅና ምዕራብ ሆኖ ለሁለት ይከፈላል፤ እናንተም በእግዚአብሔር ተራራ ሸለቆ በኩል በይሁዳ ንጉሥ በዖዝያን ዘመን በምድር ትሸሻላችሁ፤ ሸለቆው እስከ አጸል ይደርሳልና። በምድር መናወጥ ምክንያት ሸሽታችሁ እንደ ነበረ ትሸሻላችሁ፤ ከዚያም አምላኬ እግዚአብሔር ይመጣል፤ ቅዱሳኑም ሁሉ ዐብረውት ይመጣሉ። በዚያ ቀን በረዶ፣ ውርጭና ብርሃን አይኖርም። ቀኑም የብርሃን ወይም የጨለማ ጊዜ የሌለበት ልዩ ቀን ይሆናል፤ ያም ቀን በእግዚአብሔር የታወቀ ቀን ይሆናል፤ ሲመሽም ብርሃን ይሆናል። በዚያ ቀን የሕይወት ውሃ ከኢየሩሳሌም ይፈልቃል፤ እኩሌታው ወደ ምሥራቁ ባሕር፣ እኩሌታውም ወደ ምዕራቡ ባሕር ይፈስሳል፤ ይህም በበጋና በክረምት ይሆናል። እግዚአብሔር በምድር ሁሉ ላይ ይነግሣል፤ በዚያ ቀን እግዚአብሔር አንድ፣ ስሙም አንድ ብቻ ይሆናል። ምድር ሁሉ ከጌባዕ አንሥቶ በኢየሩሳሌም ደቡብ እስካለችው ሪሞን ድረስ ተለውጣ ደልዳላ ሜዳ ትሆናለች፤ ኢየሩሳሌም ግን ከብንያም በር እስከ መጀመሪያው በር፣ ከማእዘን በርና ከሐናንኤል ግንብ እስከ ንጉሡ የወይን ጠጅ መጥመቂያ ድረስ በዚያው በቦታዋ ላይ ከፍ እንዳለች ትኖራለች። የሰው መኖሪያም ትሆናለች፤ ከቶም ዳግመኛ አትፈርስም፤ ኢየሩሳሌም ያለ ሥጋት በሰላም ትኖራለች። እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን የወጓትን አሕዛብ ሁሉ የሚመታበት መቅሠፍት ይህ ነው፤ ገና በእግራቸው ቆመው ሳሉ ሥጋቸው ይበሰብሳል፤ ዐይኖቻቸው በጕድጓዶቻቸው ውስጥ እንዳሉ ይበሰብሳሉ፤ ምላሶቻቸውም በአፎቻቸው ውስጥ እንዳሉ ይበሰብሳሉ። በዚያ ቀን ከእግዚአብሔር ዘንድ በሰዎች ላይ ታላቅ ሽብር ይወርዳል፤ እያንዳንዱ ሰው የባልንጀራውን እጅ ይይዛል፤ አንዱም ሌላውን ይወጋዋል። ይሁዳም ደግሞ ኢየሩሳሌምን ይወጋል። በዙሪያው ያሉ የአሕዛብ ሁሉ ሀብት፣ ብዙ ወርቅ፣ ብርና ልብስ ይሰበሰባል። ይህንኑ የሚመስል መቅሠፍት ፈረሶችንና በቅሎዎችን፣ ግመሎችንና አህዮችን እንዲሁም በየሰፈሩ ያሉትን እንስሳት ሁሉ ይመታል።
ዘካርያስ 14:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እነሆ፥ የእግዚአብሔር ቀን ይመጣል፥ ብዝበዛሽንም በውስጥሽ ይካፈላሉ። አሕዛብንም ሁሉ በኢየሩሳሌም ላይ ለሰልፍ እሰበስባለሁ፥ ከተማይቱም ትያዛለች፥ ቤቶችም ይበዘበዛሉ፥ ሴቶችም ይነወራሉ፥ የከተማይቱም እኵሌታ ለምርኮ ይወጣል፥ የቀረው ሕዝብ ግን ከከተማ አይጠፋም። እግዚአብሔርም ይወጣል፥ በሰልፍም ቀን እንደ ተዋጋ ከእነዚያ አሕዛብ ጋር ይዋጋል። በዚያም ቀን እግሮቹ በኢየሩሳሌም ትይዩ በምሥራቅ በኩል ባለው በደብረ ዘይት ላይ ይቆማሉ፥ ደብረ ዘይትም በመካከል ወደ ምሥራቅና ወደ ምዕራብ ይሰነጠቃል፥ እጅግም ታላቅ ሸለቆ ይሆናል፥ የተራራውም እኵሌታ ወደ ሰሜን፥ እኵሌታውም ወደ ደቡብ ይርቃል። የተራሮችም ሸለቆ እስከ አጸል ይደርሳልና በተራሮች ሸለቆ ትሸሻላችሁ፥ በይሁዳም ንጉሥ በዖዝያን ዘመን ከሆነው ከምድር መናወጥ ፊት እንደ ሸሻችሁ ትሸሻላችሁ፥ አምላኬ እግዚአብሔርም ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ይመጣል። በዚያም ቀን በረዶና ውርጭ እንጂ ብርሃን አይሆንም። አንድ ቀንም ይሆናል፥ እርሱም በእግዚአብሔር ዘንድ የታወቀ ይሆናል፥ ቀንም አይሆንም፥ ሌሊትም አይሆንም፥ ሲመሽም ብርሃን ይሆናል። በዚያም ቀን የሕይወት ውኃ ከኢየሩሳሌም ይወጣል፥ እኵሌታው ወደ ምሥራቁ ባሕር፥ እኵሌታውም ወደ ምዕራቡ ባሕር ይሄዳል፥ ይህ በበጋና በክረምት ይሆናል። እግዚአብሔርም በምድር ሁሉ ላይ ይነግሣል፥ በዚያ ቀን እግዚአብሔር አንድ፥ ስሙም አንድ ይሆናል። ምድር ሁሉ ከጌባ ጀምሮ በኢየሩሳሌምም ደቡብ በኩል እስካለችው እስከ ሬሞን ድረስ ተለውጣ እንደ ዓረባ ትሆናለች፥ እርስዋም ከፍ ከፍ ትላለች፥ ከብንያምም በር ጀምሮ እስከ ፊተኛው በር ስፍራ እስከ ማዕዘኑ በር ድረስ፥ ከሐናንኤልም ግንብ ጀምሮ እስከ ንጉሡ መጥመቂያ ድረስ በስፍራዋ ትኖራለች። ሰዎችም ይኖሩባታል፥ ከዚያም ወዲያ እርግማን አይሆንም፥ ኢየሩሳሌምም ተዘልላ ትኖራለች። እግዚአብሔርም ከኢየሩሳሌም ጋር የተዋጉትን አሕዛብ ሁሉ የሚቀሥፍበት ቸነፈር ይህ ነው፥ በእግራቸው ሲቆሙ ሥጋቸው ይበሰብሳል፥ ዓይኖቻቸውም በዓይነስባቸው ውስጥ ይበሰብሳሉ፥ ምላሳቸውም በአፋቸው ውስጥ ይበሰብሳል። በዚያም ቀን ከእግዚአብሔር ዘንድ ታላቅ ሽብር በእነርሱ ላይ ይሆናል፥ እያንዳንዱም የባልንጀራውን እጅ ይይዛል፥ እጁም በባልንጀራው እጅ ላይ ይነሣል። ይሁዳም ደግሞ በኢየሩሳሌም ውስጥ ሆኖ ይዋጋል፥ በዙሪያም ያሉት የአሕዛብ ሁሉ ሀብት እጅግ ብዙ ወርቅና ብር ልብስም ይሰበሰባል። በፈረስና በበቅሎ፥ በግመልና በአህያ፥ በዚያም ሰፈር ባለ እንስሳ ሁሉ ላይ የሆነ ቸነፈር እንደዚያ ያለ ቸነፈር ይሆናል።
ዘካርያስ 14:1-15 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የእግዚአብሔር ፍርድ ቀን ደርሶአል፤ በዚያን ጊዜ ዐይናችሁ እያየ በዝባዦች ከእናንተ የወሰዱትን ይካፈሉታል። ኢየሩሳሌምን እንዲወጉ እግዚአብሔር ሕዝቦችን ሰብስቦ ይመጣል፤ ከተማይቱ ትያዛለች፤ ቤቶች ይበዘበዛሉ፤ ሴቶች ይደፈራሉ፤ ከሕዝቡም እኩሌታው ተማርኮ ይሄዳል፤ የቀሩት ግን ከከተማይቱ አይወጡም። ከዚያን በኋላ እግዚአብሔር በጦርነት ጊዜ እንደሚዋጋ ሕዝቦችን ለመውጋት ይነሣል። በዚያን ቀን እግዚአብሔር ከኢየሩሳሌም በስተ ምሥራቅ ባለው በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ይቆማል፤ የደብረ ዘይት ተራራም ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ በሰፊ ሸለቆ በሁለት ይከፈላል፤ ስለዚህም የተራራው እኩሌታ ወደ ሰሜን እኩሌታውም ወደ ደቡብ ፈቀቅ ይላል። እናንተም ተራራውን በሁለት ከፍሎ እስከ አጻል በደረሰው በዚህ ሸለቆ ውስጥ አልፋችሁ ታመልጣላችሁ፤ በይሁዳ ንጉሥ በዖዝያ ዘመን ምድር በተናወጠች ጊዜ የቀድሞ አባቶቻችሁ በሸሹት ዐይነት ትሸሻላችሁ፤ እግዚአብሔር አምላኬም ቅዱሳኑን አስከትሎ ይመጣል። በዚያን ዘመን ውርጭና ዐመዳይ ጨለማም ከቶ አይኖርም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ የታወቀ አንድ ተከታታይ ቀን ይመጣል፤ በምሽት ጊዜ ብርሃን ስለሚሆን ቀንም ሌሊትም የለም። በዚያን ቀን ከኢየሩሳሌም የሕይወት ውሃ ይፈልቃል፤ ከእርሱም እኩሌታው በምሥራቅ በኩል ወደ ሙት ባሕር፥ እኩሌታው በምዕራብ በኩል ወደ ሜዲቴራኒያን ባሕር ይፈስሳል፤ በበጋም ሆነ በክረምት ዓመቱን ሙሉ ሲፈስ ይኖራል። በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር በዓለም ሁሉ ይነግሣል፤ ሰዎችም አምላክ እርሱ ብቻ መሆኑን ያምናሉ፤ የእርሱንም ስም ብቻ ይጠራሉ። በሰሜን ከጌባዕ አንሥቶ ኢየሩሳሌምን በደቡብ በኩል አልፎ እስከ ሪሞን ድረስ ያለው አውራጃ ደልዳላ ይሆናል፤ ኢየሩሳሌም በዙሪያዋ ካለው ምድር በላይ ከፍ ትላለች፤ ከተማይቱም ከብንያም በር አንሥቶ በቀድሞው በር አቅጣጫ እስከ ማእዘን በር እንዲሁም ከሐናንኤል ግንብ አንሥቶ እስከ ቤተ መንግሥቱ ወይን መጭመቂያው ድረስ ከፍ በማለት ጸንታ ትኖራለች። ኢየሩሳሌም የሕዝብ መኖሪያ ትሆናለች፤ ከእንግዲህ ወዲህ ጥፋት አይደርስባትም፤ ሕዝብዋም ያለ ስጋት በሰላም ይኖራል። ኢየሩሳሌምን ለመውጋት በሚነሣሡ ሕዝቦች ላይ እግዚአብሔር ቀሣፊ በሽታ ያመጣባቸዋል፤ በሕይወት እያሉ ሥጋቸው ይበሰብሳል፤ ዐይናቸው በዐይነስባቸው ውስጥ፥ ምላሳቸውም በአፋቸው ውስጥ ይበሰብሳል። በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር ሁከትና ፍርሀት ስለሚለቅባቸው እያንዳንዱ ሰው በአጠገቡ ያለውን ሌላ ሰው ይዞ አደጋ ይጥልበታል። የይሁዳ ሰዎች ኢየሩሳሌምን ለመከላከል ይዋጋሉ፤ በዙሪያዋም ያሉትን መንግሥታት ሀብት ሁሉ ማርከው ይወስዳሉ፤ ከሚወስዱትም ምርኮ ወርቅ፥ ብርና የልብስ ዐይነት እጅግ ብዙ ይሆናል። ያንን የሚመስል ቀሣፊ በሽታ በጠላት ሰፈር ባሉ እንስሶች በፈረሶች፥ በበቅሎዎች፥ በግመሎችና በአህዮች ሁሉ ላይ ይመጣል።
ዘካርያስ 14:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እነሆ፥ ከእናንት የተወሰድ ምርኮ በመካከላችሁ ለክፍፍል የሚበቃበት የጌታ ቀን ይመጣል። አሕዛብንም ሁሉ በኢየሩሳሌም ላይ እንዲነሱ እሰበስባቸዋለሁ፤ ከተማይቱም ትያዛለች፥ ቤቶችም ይበዘበዛሉ፥ ሴቶችም ይደፈራሉ፤ የከተማይቱም እኩሌታ ለምርኮ ይጋዛል፥ የቀረው ሕዝብ ግን ከከተማዋ አይፈናቃልም። ጌታም ይወጣል፥ በጦርነትም ቀን እንደሚዋጋ ከእነዚያ አሕዛቦች ጋር ይዋጋል። በዚያም ቀን የእግዚአብሔር እግሮች በኢየሩሳሌም ትይዩ በምሥራቅ በኩል ባለው በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ይቆማሉ፤ የደብረ ዘይት ተራራም በመካከሉ ወደ ምሥራቅና ወደ ምዕራብ ይሰነጠቃል፥ እጅግም ጥልቅ ሸለቆ ይሆናል፤ የተራራውም እኩሌታ ወደ ሰሜን፥ እኩሌታውም ወደ ደቡብ ይሸሻል። የተራሮችም ሸለቆ እስከ አጸል ስለሚደርስ፥ በተራሮች መካከል ባለው ሸለቆ ትሸሻላችሁ። በይሁዳም ንጉሥ በዖዝያን ዘመን በምድር መንቀጥቀጥ ምክንያት ከሆነው ሽሽት በበለጠ ትሸሻላችሁ። ከዚያም አምላኬ ጌታ ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ይመጣል። በዚያም ቀን በረዶና ውርጭ አይኖርም። የማያቋርጥ አንድ የብርሃን ቀን ይሆናል፥ እርሱም በጌታ ዘንድ የታወቀ ይሆናል፤ ቀንም አይሆንም፥ ሌሊትም አይሆንም፤ ሲመሽም ብርሃን ይሆናል። በዚያም ቀን የሕይወት ውኃ ከኢየሩሳሌም ይወጣል፥ እኩሌታው ወደ ምሥራቁ ባሕር፥ እኩሌታውም ወደ ምዕራቡ ባሕር ይወርዳል፤ ይህ በበጋና በክረምት የማያቋርጥ ይሆናል። ጌታም በምድር ሁሉ ላይ ይነግሣል፤ በዚያ ቀን ጌታ አንድ፥ ስሙም አንድ ይሆናል። ምድር ሁሉ ከጌባ ጀምሮ በኢየሩሳሌምም ደቡብ በኩል እስካለችው እስከ ሬሞን ድረስ ተለውጣ፥ እንደ ዓረባ ትሆናለች፤ እርሷም ከፍ ከፍ ትላለች፥ ከብንያምም በር ጀምሮ እስከ ፊተኛው የበሯ ስፍራ እስከ ማዕዘኑ በር ድረስ፥ ከሐናንኤልም ግንብ ጀምሮ እስከ ንጉሡ መጥመቂያ ድረስ በስፍራዋ ትኖራለች። ከተማዋም ሰዎች ይኖሩባታል፥ ከዚያም ወዲያ እርግማን አይኖርም። ኢየሩሳሌምም በሰላም ትኖራለች። ጌታም ከኢየሩሳሌም ጋር የተዋጉትን አሕዛብ ሁሉ የሚቀሥፍበት ቸነፈር ይህ ነው፤ በእግራቸው ሲቆሙ ሥጋቸው ይበሰብሳል፥ ዐይኖቻቸውም በዓይነስባቸው ውስጥ ይበሰብሳል፥ ምላሳቸውም በአፋቸው ውስጥ ይበሰብሳል። በዚያም ቀን ከእግዚአብሔር የመጣ ታላቅ ሽብር በእነርሱ ላይ ያድራል፤ እርስ በእርሳቸውም ይያያዛሉ፥ አንዱም በሌላው ላይ ይነሣል። ይሁዳም እንኳን ኢየሩሳሌም ውስጥ ሆኖ ለውጊያ ይነሣባታል። በዙሪያም ያሉትን የአሕዛብ ሁሉ ሀብት፥ እጅግ ብዙ ወርቅና ብር፥ ልብስም ይሰበሰባል። በፈረሶች፥ በበቅሎዎች፥ በግመሎች፥ በአህዮች፥ እንዲሁም በዚያም ሰፈር ባሉ እንስሶች ሁሉ ላይ በሰዎች ላይ እንደ ሆነው ዓይነት ቸነፈር በእነርሱም ላይ ይሆናል።