ዘኍልቍ 6:1-8

ዘኍልቍ 6:1-8 NASV

እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “እስራኤላውያንን ተናገራቸው፤ እንዲህም በላቸው፣ ‘ወንድም ሆነ ሴት ናዝራዊ ይሆን ዘንድ ራሱን ለእግዚአብሔር ለመለየት ስእለት ቢሳል፣ ከወይን ጠጅና ከሌላም ከሚያሰክር መጠጥ ይታቀብ፤ የወይንም ሆነ የሚያሰክር የሌላ መጠጥ ሖምጣጤ አይጠጣ፤ እንዲሁም የወይን ጭማቂ አይጠጣ፤ የወይን ፍሬም ሆነ ዘቢብ አይብላ። በናዝራዊነቱ ወቅት ከወይን ተክል የሚገኘውን ማንኛውም ነገር፣ የወይኑን ዘር፣ ግልፋፊውንም እንኳ ቢሆን አይብላ። “ ‘ስእለት ተስሎ ራሱን በለየበት ጊዜ ሁሉ ምላጭ ራሱን አይንካው፤ ለእግዚአብሔር የተለየበት ጊዜ እስኪያበቃ ድረስ የተቀደሰ ይሁን፤ የራስ ጠጕሩንም ያሳድግ። ራሱን ለእግዚአብሔር በለየበት ጊዜ ሁሉ ወደ ሬሳ አይቅረብ። ራሱን ለእግዚአብሔር የለየበት ምልክት በራሱ ላይ ስላለ አባቱም ይሁን እናቱ፣ ወንድሙም ይሁን እኅቱ ቢሞቱ ለእነርሱ ሲል እንኳ ራሱን አያርክስ። ራሱን በለየበት ጊዜ ሁሉ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ነው።