ዘኍልቍ 16:1-7

ዘኍልቍ 16:1-7 NASV

የሌዊ ልጅ፣ የቀዓት ልጅ፣ የይስዓር ልጅ የሆነው ቆሬ፣ ከሮቤልም ነገድ የኤልያብ ልጆች ዳታንና አቤሮን እንዲሁም የፍሌት ልጅ ኦን በክፋት ተነሣሥተው፣ ሙሴን ተቃወሙት። ከእነዚህም ጋራ ታዋቂ የማኅበረ ሰቡ መሪዎች የሆኑና በጉባኤ አባልነት የተመረጡ ሁለት መቶ ዐምሳ እስራኤላውያን ዐብረው ነበሩ። እነዚህም ሙሴንና አሮንን ለመቃወም ግንባር ፈጥረው በመምጣት፣ “ምነው ከልክ አላለፋችሁም? የማኅበረ ሰቡ አባላት ሁሉ እያንዳንዳቸው የተቀደሱ ናቸው፤ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋራ ነው፤ ታዲያ በእግዚአብሔር ማኅበር ላይ የምትታበዩት ለምንድን ነው?” አሏቸው። ሙሴም ይህን ሲሰማ በግንባሩ መሬት ላይ ተደፋ፤ ቆሬንና ተከታዮቹን በሙሉ እንዲህ አላቸው፤ “የርሱ የሆነውና የተቀደሰው ማን መሆኑን እግዚአብሔር ጧት ያሳውቃል፤ ወደ ራሱም ያመጣዋል፤ የሚመርጠውን ሰው ወደ ራሱ እንዲቀርብ ያደርገዋል። ቆሬ፣ አንተና ተከታዮችህ ሁሉ እንዲህ አድርጉ፤ ጥናዎችን ውሰዱ፤ በማግስቱም በእግዚአብሔር ፊት እሳትና ዕጣን ጨምሩባቸው፤ እግዚአብሔር የሚመርጠውም ያ ሰው ቅዱስ ይሆናል፤ እናንተ የሌዊ ልጆች፤ ከልክ ያለፋችሁትስ እናንተ ናችሁ።”