ዘኍልቍ 16:1-7
ዘኍልቍ 16:1-7 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የሌዊም ልጅ የቀዓት ልጅ የይስዓር ልጅ ቆሬ ከኤልያብ ልጆች ከዳታንና ከአቤሮን፥ ከሮቤልም ልጅ ከፋሌት ልጅ ከአውናን ጋር ተናገረ። በሙሴም ላይ ተነሡ፤ ከእስራኤልም ልጆች በምክር የተመረጡ፥ ዝናቸውም የተሰማ ሁለት መቶ አምሳ የማኅበሩ አለቆች ከእነርሱ ጋር ነበሩ። በሙሴና በአሮን ላይ ተነሡ፤ “ለእናንተ ይበቃችኋል፤ ማኅበሩ ሁሉ እያንዳንዳቸው ቅዱሳን ናቸውና፥ እግዚአብሔርም በመካከላቸው ነውና፤ በእግዚአብሔርስ ጉባኤ ላይ ለምን ትታበያላችሁ?” አሉአቸው። ሙሴም በሰማ ጊዜ በግንባሩ ወደቀ። ለቆሬም ለማኅበሩም ሁሉ እንዲህ አላቸው፥ “ነገ እግዚአብሔር የእርሱ የሚሆኑትን፥ ቅዱሳንም የሆኑትን ያያል፥ ያውቃልም፤ የመረጣቸውንም ሰዎች ወደ እርሱ ያቀርባቸዋል። እንዲሁ አድርጉ፤ ቆሬና ማኅበሩ ሁሉ፥ ጥናዎቹን ውሰዱ፤ ነገም በእግዚአብሔር ፊት እሳት አድርጉባቸው፤ ዕጣንም ጨምሩባቸው፤ እግዚአብሔርም የሚመርጠው ይህ ሰው ለሌዊ ልጆች ቅዱስ ይሁንላቸው።”
ዘኍልቍ 16:1-7 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የሌዊ ልጅ፣ የቀዓት ልጅ፣ የይስዓር ልጅ የሆነው ቆሬ፣ ከሮቤልም ነገድ የኤልያብ ልጆች ዳታንና አቤሮን እንዲሁም የፍሌት ልጅ ኦን በክፋት ተነሣሥተው፣ ሙሴን ተቃወሙት። ከእነዚህም ጋራ ታዋቂ የማኅበረ ሰቡ መሪዎች የሆኑና በጉባኤ አባልነት የተመረጡ ሁለት መቶ ዐምሳ እስራኤላውያን ዐብረው ነበሩ። እነዚህም ሙሴንና አሮንን ለመቃወም ግንባር ፈጥረው በመምጣት፣ “ምነው ከልክ አላለፋችሁም? የማኅበረ ሰቡ አባላት ሁሉ እያንዳንዳቸው የተቀደሱ ናቸው፤ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋራ ነው፤ ታዲያ በእግዚአብሔር ማኅበር ላይ የምትታበዩት ለምንድን ነው?” አሏቸው። ሙሴም ይህን ሲሰማ በግንባሩ መሬት ላይ ተደፋ፤ ቆሬንና ተከታዮቹን በሙሉ እንዲህ አላቸው፤ “የርሱ የሆነውና የተቀደሰው ማን መሆኑን እግዚአብሔር ጧት ያሳውቃል፤ ወደ ራሱም ያመጣዋል፤ የሚመርጠውን ሰው ወደ ራሱ እንዲቀርብ ያደርገዋል። ቆሬ፣ አንተና ተከታዮችህ ሁሉ እንዲህ አድርጉ፤ ጥናዎችን ውሰዱ፤ በማግስቱም በእግዚአብሔር ፊት እሳትና ዕጣን ጨምሩባቸው፤ እግዚአብሔር የሚመርጠውም ያ ሰው ቅዱስ ይሆናል፤ እናንተ የሌዊ ልጆች፤ ከልክ ያለፋችሁትስ እናንተ ናችሁ።”
ዘኍልቍ 16:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የሌዊም ልጅ የቀዓት ልጅ የይስዓር ልጅ ቆሬ ከሮቤልም ልጆች የኤልያብ ልጆች ዳታንና አቤሮን የፋሌትም ልጅ ኦን በሙሴ ላይ ተነሡ። ከእስራኤልም ልጆች ሁለት መቶ አምሳ ሰዎች ከእነርሱ ጋር ወሰዱ፤ ከጉባኤው የተመረጡ ዝናቸውም የተሰማ የማኅበሩ አለቆች ነበሩ። በሙሴና በአሮን ላይ ተሰብስበው፦ ማኅበሩ ሁሉ እያንዳንዳቸው ቅዱሳን ናቸውና፥ እግዚአብሔርም በመካከላቸው ነውና እናንተ እጅግ አብዝታችኋል፤ በእግዚአብሔርም ጉባኤ ላይ ለምን ትታበያላችሁ? አሉ። ሙሴም በሰማ ጊዜ በግምባሩ ወደቀ፤ ለቆሬም ለወገኑም ሁሉ፦ ነገ እግዚአብሔር ለእርሱ የሚሆነውን፥ ቅዱስም የሚሆነውን ያስታውቃል፤ የመረጠውንም ሰው ወደ እርሱ ያቀርበዋል። እንዲሁ አድርጉ፤ ቆሬና ወገንህ ሁሉ፥ ጥናዎቹን ውሰዱ፤ ነገም በእግዚአብሔር ፊት እሳት አድርጉባቸው፥ ዕጣንም ጨምሩባቸው፤ እንዲህም ይሆናል፤ እግዚአብሔር የሚመርጠው እርሱ ቅዱስ ይሆናል፤ እናንተ የሌዊ ልጆች ሆይ፥ እጅግ አብዝታችኋል ብሎ ተናገራቸው።
ዘኍልቍ 16:1-7 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከሌዊ ነገድ የሆነው የቀዓት ጐሣ የይስዓር ልጅ ቆሬ፥ ከሮቤል ነገድ የሆኑት የኤልያብ ልጆች ዳታንና አቤሮን፥ የፋሌትም ልጅ ኦን ዐመፁ፤ ከእነርሱም ጋር በእስራኤላውያን ዘንድ ዝናቸው የታወቀና ለሕዝብ መሪነት የተመረጡ ሁለት መቶ ኀምሳ ሰዎችን ወስደው በሙሴ ላይ ተነሡ፤ እነርሱም በሙሴና በአሮን ፊት ተሰብስበው እንዲህ አሉአቸው፦ “እናንተ ከልክ አልፋችኋል! የዚህ ጉባኤ አባላት የሆኑ ሁሉ ለእግዚአብሔር የተለዩ ናቸው፤ እግዚአብሔርም ከእኛ ሁሉ ጋር ነው፤ ታዲያ በእግዚአብሔር ጉባኤ ላይ ራሳችሁን ከፍ ከፍ የምታደርጉት ስለምንድን ነው?” ሙሴም ይህን በሰማ ጊዜ በግንባሩ ወድቆ ጸለየ፤ ቆሬንና ተከታዮቹን እንዲህ አላቸው፦ “ነገ ጠዋት እግዚአብሔር ለእርሱ የተለየ ማን እንደ ሆነ ለይቶ ያሳየናል፤ ይኸውም የእርሱ የሆነውንና የመረጠውን በመሠዊያው ላይ ያገለግለው ዘንድ ወደ እርሱ እንዲቀርብ ይፈቅድለታል። ነገ ጠዋት አንተና ተባባሪዎችህ ሁሉ ጥናዎችን ይዛችሁ ኑ! በእነርሱም ላይ የከሰል ፍምና ዕጣን አድርጋችሁ ወደ መሠዊያው አቅርቡአቸው፤ ከዚያም በኋላ እግዚአብሔር ማንኛችንን መርጦ ለራሱ እንደ ለየ እናያለን፤ ከልክ ያለፋችሁትስ እናንተ ሌዋውያኑ ናችሁ።”
ዘኍልቍ 16:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የሌዊም ልጅ የቀዓት ልጅ የይስዓር ልጅ ቆሬ የኤልያብ ልጆች ዳታንንና አቤሮንን ከሮቤልም ልጆች የፋሌት ልጅ ኦንን ወሰዳቸው። ከእስራኤልም ልጆች ሁለት መቶ ኀምሳ ሰዎች የሆኑ ከጉባኤው የተመረጡ፥ በዝናቸውም የገነኑ የማኅበሩ አለቆች ጋር በመሆን እነርሱ በሙሴ ላይ ተነሡ። በሙሴና በአሮን ላይ ተሰብስበው እንዲህ አሉአቸው፦ “ማኅበሩ ሁሉ እያንዳንዳቸው ቅዱሳን ናቸውና፥ ጌታም በመካከላቸው ነውና እናንተ እጅግ አብዝታችሁታል፤ በጌታም ጉባኤ ላይ ለምን ትታበያላችሁ?” ሙሴም በሰማ ጊዜ በግምባሩ ወድቆ ሰገደ፤ ለቆሬም እርሱንም ለተከሉት ሁሉ እንዲህ ቡሎ ተናገረ፦ “ነገ ጠዋት ጌታ ለእርሱ የሆነውን ሰው፥ ቅዱስም ማን እንሆነ፥ ወደ እርሱም ለመቅረብ የተፈቀደለትን ሰው ያሳውቃል፤ የመረጠውንም ሰው ወደ እርሱ እንዲቀርብ ይፈቅድለታል። እንዲሁ አድርጉ፤ ቆሬና እርሱንም የተከተሉት ሁሉ፥ ጥናዎችን ይውሰዱ፤ በማግስቱም በጌታ ፊት እሳት አድርጉባቸው፥ ዕጣንም ጨምሩባቸው፤ እንዲህም ይሆናል፤ ጌታ የሚመርጠው እርሱ ቅዱስ ይሆናል፤ እናንተ የሌዊ ልጆች ሆይ! እጅግ አብዝታችሁታል።”