ከዚህ በኋላ ፈሪሳውያንና ከኢየሩሳሌም የመጡ አንዳንድ ጸሐፍት በዙሪያው ተሰበሰቡ፤ ከደቀ መዛሙርቱም አንዳንዶቹ ባልነጻ ማለት ባልታጠበ እጅ እንጀራ ሲበሉ አዩ፤ ፈሪሳውያንና አይሁድ ሁሉ የአባቶችን ወግ ለመጠበቅ ሲሉ፣ በሥርዐቱ መሠረት እጃቸውን በጥንቃቄ ሳይታጠቡ አይበሉም ነበርና። ከገበያ ሲመለሱም ታጥበው ራሳቸውን ካላነጹ በቀር አይበሉም ነበር። እንዲሁም ዋንጫን፣ ማሰሮን፣ ሳሕንና ዐልጋን እንደ ማጠብ ያሉትን ሌሎችን ወጎች ይጠብቁ ነበር። ፈሪሳውያንና ጸሐፍትም፣ “ደቀ መዛሙርትህ እንደ አባቶች ወግ በመኖር ፈንታ ባልታጠበ እጃቸው ለምን እንጀራ ይበላሉ?” ብለው ጠየቁት። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ኢሳይያስ ስለ እናንተ፣ ስለ ግብዞች በትክክል ተንብዮአል፤ እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፤ “ ‘ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው፤ በከንቱ ያመልኩኛል፤ ትምህርታቸውም ሰው ሠራሽ ሥርዐት ነው።’ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትታችሁ የሰዎችን ወግና ሥርዐት ታጠብቃላችሁ።” ደግሞም፣ እንዲህ አላቸው፤ “የራሳችሁን ወግ ለመጠበቅ ስትሉ፣ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ የምትተዉበት ዘዴ አላችሁ። ሙሴ፣ ‘አባትህንና እናትህን አክብር፤ አባቱን ወይም እናቱን የሚሳደብ ይሙት’ ብሎ ነበርና፤ እናንተ ግን አንድ ሰው አባቱን ወይም እናቱን፣ ከእኔ ማግኘት የሚገባችሁን ርዳታ ሁሉ ቍርባን፣ ይኸውም መባ እንዲሆን ሰጥቻለሁ ቢላቸው፣ እናንተም ይህ ሰው ለአባቱም ሆነ ለእናቱ ከዚህ በኋላ ምንም ነገር እንዲያደርግ አትፈቅዱለትም። ስለዚህ ለትውልድ በምታስተላልፉት ወግ የእግዚአብሔርን ቃል ትሽራላችሁ፤ ይህን የመሰለም ብዙ ነገር ታደርጋላችሁ።”
ማርቆስ 7 ያንብቡ
ያዳምጡ ማርቆስ 7
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ማርቆስ 7:1-13
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች