ማርቆስ 7:1-13

ማርቆስ 7:1-13 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ፈሪሳውያንና ከጻፎች ወገን ከኢየሩሳሌም የመጡትም ወደ እርሱ ተሰበሰቡ። ከደቀ መዛሙርቱም አንዳንድ በርኵስ ማለት ባልታጠበ እጅ እንጀራ ሲበሉ አዩ። ፈሪሳውያንና አይሁድም ሁሉ የሽማግሎችን ወግ ሲጠብቁ እጃቸውን ደኅና አድርገው ሳይታጠቡ አይበሉምና፤ ከገበያም ተመልሰው ካልታጠቡ አይበሉም፤ ጽዋንም ማድጋንም የናስ ዕቃንም አልጋንም እንደ ማጠብ ሌላ ነገር ሊጠብቁት የተቀበሉት ብዙ አለ። ፈሪሳውያንና ጻፎችም “ደቀ መዛሙርትህ እንደ ሽማግሌዎች ወግ ስለ ምን አይሄዱም? ነገር ግን እጃቸውን ሳይታጠቡ እንጀራ ይበላሉ፤” ብለው ጠየቁት። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው “ኢሳይያስ ስለ እናንተ ስለ ግብዞች ‘ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው፤ የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል፤’ ተብሎ እንደ ተጻፈ በእውነት ትንቢት ተናገረ። የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትታችሁ ጽዋን ማድጋንም እንደ ማጠብ የሰውን ወግ ትጠብቃላችሁ፤ ይህንም የመሰለ ብዙ ሌላ ነገር ታደርጋላችሁ።” እንዲህም አላቸው “ወጋችሁን ትጠብቁ ዘንድ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እጅግ ንቃችኋል። ሙሴ ‘አባትህንና እናትህን አክብር፤’ ደግሞም ‘አባቱን ወይም እናቱን የሰደበ ፈጽሞ ይሙት፤’ ብሎአልና። እናንተ ግን ትላላችሁ ‘ሰው አባቱን ወይም እናቱን ከእኔ የምትጠቀምበት ነገር ሁሉ ቍርባን ማለት መባ ነው፤’ ቢል፥ ለአባቱና ለእናቱ ምንም እንኳ ሊያደርግ ወደ ፊት አትፈቅዱለትም፤ ባስተላለፋችሁትም ወግ የእግዚአብሔርን ቃል ትሽራላችሁ፤ እንደዚሁም ይህን የሚመስል ብዙ ነገር ታደርጋላችሁ።”

ማርቆስ 7:1-13 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከዚህ በኋላ ፈሪሳውያንና ከኢየሩሳሌም የመጡ አንዳንድ ጸሐፍት በዙሪያው ተሰበሰቡ፤ ከደቀ መዛሙርቱም አንዳንዶቹ ባልነጻ ማለት ባልታጠበ እጅ እንጀራ ሲበሉ አዩ፤ ፈሪሳውያንና አይሁድ ሁሉ የአባቶችን ወግ ለመጠበቅ ሲሉ፣ በሥርዐቱ መሠረት እጃቸውን በጥንቃቄ ሳይታጠቡ አይበሉም ነበርና። ከገበያ ሲመለሱም ታጥበው ራሳቸውን ካላነጹ በቀር አይበሉም ነበር። እንዲሁም ዋንጫን፣ ማሰሮን፣ ሳሕንና ዐልጋን እንደ ማጠብ ያሉትን ሌሎችን ወጎች ይጠብቁ ነበር። ፈሪሳውያንና ጸሐፍትም፣ “ደቀ መዛሙርትህ እንደ አባቶች ወግ በመኖር ፈንታ ባልታጠበ እጃቸው ለምን እንጀራ ይበላሉ?” ብለው ጠየቁት። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ኢሳይያስ ስለ እናንተ፣ ስለ ግብዞች በትክክል ተንብዮአል፤ እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፤ “ ‘ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው፤ በከንቱ ያመልኩኛል፤ ትምህርታቸውም ሰው ሠራሽ ሥርዐት ነው።’ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትታችሁ የሰዎችን ወግና ሥርዐት ታጠብቃላችሁ።” ደግሞም፣ እንዲህ አላቸው፤ “የራሳችሁን ወግ ለመጠበቅ ስትሉ፣ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ የምትተዉበት ዘዴ አላችሁ። ሙሴ፣ ‘አባትህንና እናትህን አክብር፤ አባቱን ወይም እናቱን የሚሳደብ ይሙት’ ብሎ ነበርና፤ እናንተ ግን አንድ ሰው አባቱን ወይም እናቱን፣ ከእኔ ማግኘት የሚገባችሁን ርዳታ ሁሉ ቍርባን፣ ይኸውም መባ እንዲሆን ሰጥቻለሁ ቢላቸው፣ እናንተም ይህ ሰው ለአባቱም ሆነ ለእናቱ ከዚህ በኋላ ምንም ነገር እንዲያደርግ አትፈቅዱለትም። ስለዚህ ለትውልድ በምታስተላልፉት ወግ የእግዚአብሔርን ቃል ትሽራላችሁ፤ ይህን የመሰለም ብዙ ነገር ታደርጋላችሁ።”

ማርቆስ 7:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ፈሪሳውያንና ከጻፎች ወገን ከኢየሩሳሌም የመጡትም ወደ እርሱ ተሰበሰቡ። ከደቀ መዛሙርቱም አንዳንድ በርኵስ ማለት ባልታጠበ እጅ እንጀራ ሲበሉ አዩ። ፈሪሳውያንና አይሁድም ሁሉ የሽማግሎችን ወግ ሲጠብቁ እጃቸውን ደኅና አድርገው ሳይታጠቡ አይበሉምና፥ ከገበያም ተመልሰው ካልታጠቡ አይበሉም፥ ጽዋንም ማድጋንም የናስ ዕቃንም አልጋንም እንደ ማጠብ ሌላ ነገር ሊጠብቁት የተቀበሉት ብዙ አለ። ፈሪሳውያንም ጻፎችም፦ ደቀ መዛሙርትህ እንደ ሽማግሌዎች ወግ ስለ ምን አይሄዱም? ነገር ግን እጃቸውን ሳይታጠቡ እንጀራ ይበላሉ ብለው ጠየቁት። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው፦ ኢሳይያስ ስለ እናንተ ስለ ግብዞች፦ ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው፤ የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል ተብሎ እንደ ተጻፈ በእውነት ትንቢት ተናገረ። የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትታችሁ ጽዋን ማድጋንም እንደ ማጠብ የሰውን ወግ ትጠብቃላችሁ፥ ይህንም የመሰለ ብዙ ሌላ ነገር ታደርጋላችሁ። እንዲህም አላቸው፦ ወጋችሁን ትጠብቁ ዘንድ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እጅግ ንቃችኋል። ሙሴ፦ አባትህንና እናትህን አክብር፤ ደግሞ፦ አባቱን ወይም እናቱን የሰደበ ፈጽሞ ይሙት ብሎአልና። እናንተ ግን ትላላችሁ፦ ሰው አባቱን ወይም እናቱን፦ ከእኔ የምትጠቀምበት ነገር ሁሉ ቍርባን ማለት መባ ነው ቢል፥ ለአባቱና ለእናቱ ምንም እንኳ ሊያደርግ ወደ ፊት አትፈቅዱለትም፤ ባስተላለፋችሁትም ወግ የእግዚአብሔርን ቃል ትሽራላችሁ፤ እንደዚሁም ይህን የሚመስል ብዙ ነገር ታደርጋላችሁ።

ማርቆስ 7:1-13 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ፈሪሳውያንና ከኢየሩሳሌም የመጡ አንዳንድ የሕግ መምህራን ወደ ኢየሱስ መጥተው በዙሪያው ተሰበሰቡ። ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አንዳንዶቹ በሥርዓት ባልነጻ ማለት ባልታጠበ እጅ እንጀራ ሲበሉ አዩአቸው። ፈሪሳውያንና የቀሩትም አይሁድ የሽማግሌዎችን ወግ በመጠበቅ እጃቸውን በሥርዓቱ ካልታጠቡ አይበሉም ነበር። እንዲሁም ከገበያ ሲመለሱ ካልታጠቡ አይበሉም ነበር፤ ዋንጫን፥ ማሰሮን፥ የናስ ዕቃዎችንና አልጋን፥ እንደማጠብ ያለ፥ ሌላም ብዙ ወግ ይጠብቁ ነበር። ስለዚህ ፈሪሳውያንና የሕግ መምህራን፥ “ደቀ መዛሙርትህ የሽማግሌዎችን ወግ በመጣስ፥ ስለምን እጃቸውን ሳይታጠቡ እንጀራ ይበላሉ?” ሲሉ ኢየሱስን ጠየቁት። እርሱ ግን እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እናንተ ግብዞች! ኢሳይያስ ስለ እናንተ፥ ‘ይህ ሕዝብ በአፉ ብቻ ያከብረኛል እንጂ ልቡ ከእኔ የራቀ ነው! ሰው ሠራሽ ሥርዓትን እንደ እግዚአብሔር ሕግ አድርገው እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል!’ ብሎ የተናገረው ትንቢት ትክክል ነው፤ “ስለዚህ እናንተ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትታችሁ የሰውን ወግ ትጠብቃላችሁ።” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ “ወጋችሁን ለመጠበቅ ስትሉ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትተዋላችሁ፤ ሙሴ፦ ‘አባትህንና እናትህን አክብር፤ ደግሞም በአባቱ ወይም በእናቱ ላይ ክፉ የሚናገር ሰው በሞት ይቀጣ፤’ ይላል። እናንተ ግን እንዲህ ትላላችሁ፤ ‘አንድ ሰው ለአባቱ ወይም ለእናቱ በመርዳት ፈንታ ለአባቱና ለእናቱ ማድረግ የሚገባውን ነገር ሁሉ ለእግዚአብሔር ያቀረብኩት መባ ነው፤’ ቢላችሁ፥ አባትና እናቱን ከመርዳት ነጻ ታደርጉታላችሁ፤ በዚህም ሁኔታ የራሳችሁን ወግ ለመጠበቅ ስትሉ የእግዚአብሔርን ቃል ትሽራላችሁ፤ እንዲሁም ይህን የመሳሰለ ብዙ ነገር ታደርጋላችሁ።”

ማርቆስ 7:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ከዚህ በኋላ ፈሪሳውያንና ከኢየሩሳሌም የመጡ አንዳንድ ጸሐፍት በዙሪያው ተሰበሰቡ፤ ከደቀ መዛሙርቱም አንዳንዶቹ ባልነጻ ማለትም ባልታጠበ እጅ እንጀራ ሲበሉ አዩ፤ ፈሪሳውያንና አይሁድ ሁሉ የአባቶችን ወግ ለመጠበቅ ሲሉ፥ በሥርዓቱ መሠረት እጃቸውን በጥንቃቄ ሳይታጠቡ አይበሉም ነበርና። ከገበያ ሲመለሱም ታጥበው ራሳቸውን ካላነጹ በስተቀር አይበሉም ነበር። እንዲሁም ዋንጫን፥ ማሰሮን፥ ሳሕንና ዐልጋን እንደማጠብ ያሉትን ሌሎችን ወጎች ይጠብቁ ነበር። ፈሪሳውያንና ጸሐፍትም፥ “ደቀ መዛሙርትህ እንደ አባቶች ወግ በመኖር ፈንታ ባልታጠበ እጃቸው ለምን እንጀራ ይበላሉ?” ብለው ጠየቁት። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰ፤ ኢሳይያስ ስለ እናንተ፥ ስለ ግብዞች ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው፤ በከንቱ ያመልከኛል፤ ትምህርታቸውም ሰው ሠራሽ ሥርዓት ብቻ ነው። ተብሎ እንደ ተጻፈ በእውነት ትንቢት ተናገረ። የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትታችሁ የሰዎችን ወግና ሥርዓት ትጠብቃላችሁ። ደግሞም፥ እንዲህ አላቸው፤ “የራሳችሁን ወግ ለመጠበቅ ስትሉ፥ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ የምትተውበት ዘዴ። ሙሴ፥ አባትህንና እናትህን አክብር፤ አባቱን ወይም እናቱን የሚሳደብ ፈጽሞ ይሙት ብሎ ነበርና፤ እናንተ ግን አንድ ሰው አባቱን ወይም እናቱን፥ ከእኔ ማግኘት የሚገባችሁን ርዳታ ሁሉ ቁርባን ይኸውም መባ አድርጌለሁ ቢላቸው፥ እናንተም ይህ ሰው ለአባቱም ሆነ ለእናቱ ከዚህ በኋላ ምንም ነገር እንዲያደርግ አትፈቅዱለትም። ስለዚህ ለትውልድ በምታስተላልፉት ወግ የእግዚአብሔርን ቃል ትሽራላችሁ፤ ይህን የመሰለም ብዙ ነገር ታደርጋላችሁ።”