ማቴዎስ 22:15-22

ማቴዎስ 22:15-22 NASV

ከዚህ በኋላ ፈሪሳውያን ወጥተው በመሄድ በአፍ ዕላፊ እንዴት እንደሚያጠምዱት ተማከሩ። ደቀ መዛሙርታቸውን ከሄሮድስ ወገኖች ጋራ ወደ እርሱ ልከው እንዲህ አሉት፤ “መምህር ሆይ፤ አንተ እውነተኛና የእግዚአብሔርንም መንገድ በእውነት የምታስተምር እንደ ሆንህ፣ ለማንም ሳታደላ ሁሉን እኩል እንደምትመለከት እናውቃለን፤ ስለዚህ ንገረን፤ ምን ይመስልሃል? ለመሆኑ ለቄሳር ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም?” ኢየሱስ ግን ተንኰላቸውን በመረዳት እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ ግብዞች ለምን በነገር ልታጠምዱኝ ትሻላችሁ? ለግብር የሚከፈለውን ገንዘብ እስኪ አሳዩኝ።” እነርሱም አንድ ዲናር አመጡለት። እርሱም፣ “በዚህ ገንዘብ ላይ የሚታየው መልክ የማን ነው? ጽሕፈቱስ የማን ነው?” አላቸው። እነርሱም፣ “የቄሳር ነው” አሉት። እርሱም መልሶ፣ “እንግዲያውስ የቄሳርን ለቄሳር፣ የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር ስጡ” አላቸው። ይህን ሲሰሙ ተደነቁ፤ ትተዉትም ሄዱ።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች