ማቴዎስ 22:15-22

ማቴዎስ 22:15-22 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከዚህ በኋላ ፈሪሳውያን ወጥተው በመሄድ በአፍ ዕላፊ እንዴት እንደሚያጠምዱት ተማከሩ። ደቀ መዛሙርታቸውን ከሄሮድስ ወገኖች ጋራ ወደ እርሱ ልከው እንዲህ አሉት፤ “መምህር ሆይ፤ አንተ እውነተኛና የእግዚአብሔርንም መንገድ በእውነት የምታስተምር እንደ ሆንህ፣ ለማንም ሳታደላ ሁሉን እኩል እንደምትመለከት እናውቃለን፤ ስለዚህ ንገረን፤ ምን ይመስልሃል? ለመሆኑ ለቄሳር ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም?” ኢየሱስ ግን ተንኰላቸውን በመረዳት እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ ግብዞች ለምን በነገር ልታጠምዱኝ ትሻላችሁ? ለግብር የሚከፈለውን ገንዘብ እስኪ አሳዩኝ።” እነርሱም አንድ ዲናር አመጡለት። እርሱም፣ “በዚህ ገንዘብ ላይ የሚታየው መልክ የማን ነው? ጽሕፈቱስ የማን ነው?” አላቸው። እነርሱም፣ “የቄሳር ነው” አሉት። እርሱም መልሶ፣ “እንግዲያውስ የቄሳርን ለቄሳር፣ የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር ስጡ” አላቸው። ይህን ሲሰሙ ተደነቁ፤ ትተዉትም ሄዱ።

ማቴዎስ 22:15-22 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ከዚህ በኋላ ፈሪሳውያን ሄዱና እንዴት አድርገው ኢየሱስን በንግግሩ እንደሚያጠምዱት ተማከሩ፤ የእነርሱንም ደቀ መዛሙርት ከሄሮድስ ሰዎች ጋር ወደ ኢየሱስ ልከው፥ “መምህር ሆይ! አንተ እውነተኛ መሆንህንና የእግዚአብሔርን መንገድ በእውነት እንደምታስተምር እናውቃለን፤ ሰውንም በመፍራት የምታደርገው ነገር የለም፤ ለሰውም አታዳላም” ካሉት በኋላ፥ እንዲህ ብለው ጠየቁት። “በል እስቲ ንገረን ምን ይመስልሃል? ለሮማው ንጉሠ ነገሥት ግብር መክፈል ሕጋዊ ነውን ወይስ አይደለም?” ኢየሱስ ግን ክፋታቸውን ዐውቆ፥ “እናንተ ግብዞች! ስለምን ትፈትኑኛላችሁ? ለግብር የሚከፈለውን ገንዘብ እስቲ አሳዩኝ!” አላቸው። ስለዚህ እነርሱ አንድ ዲናር አምጥተው አሳዩት። እርሱም፥ “በዚህ ገንዘብ ላይ የተቀረጸው መልክና የተጻፈው ስም የማን ነው?” ሲል ጠየቃቸው፤ እነርሱም፥ “የሮማው ንጉሠ ነገሥት ነው!” አሉት፤ እርሱም፥ “እንግዲያውስ የንጉሡን ለንጉሡ የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር ስጡ፤” አላቸው። እነርሱም ከሰሙት በኋላ በአነጋገሩ ተደንቀው ትተውት ሄዱ።