ዘሌዋውያን 8:18-29

ዘሌዋውያን 8:18-29 NASV

ሙሴ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን አውራ በግ አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም እጃቸውን በበጉ ላይ ጫኑ። ሙሴም በጉን ዐርዶ ደሙን በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን ረጨ። በጉንም በየብልቱ ቈራረጠ፤ ሙሴም ጭንቅላቱን፣ ብልቶቹንና ሥቡን አቃጠለ። ሆድ ዕቃውንና እግሮቹን በውሃ አጠበ፤ ሙሴም እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት፣ በጉን በሙሉ ለእግዚአብሔር በእሳት የሚቀርብ፣ ሽታውም ደስ የሚያሰኝ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ በመሠዊያው ላይ አቃጠለው። ሙሴ ለቅድስና የሚሆነውን ሌላ አውራ በግ አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም እጆቻቸውን በበጉ ራስ ላይ ጫኑ። ሙሴ አውራ በጉን ዐረደ፤ ከደሙም ጥቂት ወስዶ የአሮንን ቀኝ ጆሮ ጫፍ፣ የቀኝ እጁን አውራ ጣትና የቀኝ እግሩን አውራ ጣት አስነካ፤ የአሮንንም ልጆች ወደ ፊት ጠራ፤ ሙሴም ከደሙ ጥቂት ወስዶ የቀኝ ጆሯቸውን ጫፍ፣ የቀኝ እጃቸውን አውራ ጣትና የቀኝ እግራቸውን አውራ ጣት አስነካ፤ የቀረውንም ደም በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን ረጨ። ሥቡን፣ ላቱን፣ ሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ሥብ ሁሉ፣ የጕበቱን ሽፋን፣ ሁለቱን ኵላሊቶችና ሥባቸውን እንዲሁም ቀኝ ወርቹን ወሰደ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ካለው፣ ያለ እርሾ የተጋገረ ቂጣ ካለበት መሶብ ላይ አንድ ኅብስት፣ አንድ በዘይት የተጋገረ ቂጣ እንዲሁም ስስ ቂጣ ወስዶ በሥቦቹና በቀኝ ወርቹ ላይ አኖረ። እነዚህን ሁሉ ለአሮንና ለወንዶች ልጆቹ በእጃቸው ሰጣቸው፤ እነርሱም የሚወዘወዝ መሥዋዕት አድርገው በእግዚአብሔር ፊት ወዘወዙት። ሙሴም ከእጃቸው ተቀብሎ፣ ለእግዚአብሔር በእሳት የሚቀርብ፣ መዐዛውም ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት አድርጎ በመሠዊያው ላይ በሚቃጠለው መሥዋዕት ላይ አቃጠለው። ሙሴም እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት፣ ድርሻው የሆነውን ክህነት የመስጫውን አውራ በግ ፍርምባ ወስዶ የሚወዘወዝ መሥዋዕት በማድረግ በእግዚአብሔር ፊት ወዘወዘው።