ዘሌዋውያን 8
8
አሮንና ልጆቹ ካህናት ሆነው መሾማቸው
8፥1-36 ተጓ ምብ – ዘፀ 29፥1-37
1 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2“አሮንንና ልጆቹን፣ ልብሰ ተክህኖውን፣ የመቅቢያ ዘይቱን፣ ለኀጢአት መሥዋዕት የሚሆነውን ወይፈን፣ ሁለቱን አውራ በጎችና ቂጣ ያለበትን መሶብ አምጣ፤ 3ማኅበሩን በሙሉ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ሰብስብ።” 4ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ማኅበሩም በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ተሰበሰበ።
5ሙሴም ማኅበሩን፣ “እግዚአብሔር እንዲደረግ ያዘዘው ይህ ነው” አላቸው። 6ሙሴም አሮንንና ልጆቹን ወደ ፊት አወጣቸው፤ በውሃም ዐጠባቸው። 7አሮንን እጀ ጠባብ አለበሰው፤ መቀነት አስታጠቀው፤ ቀሚስ አጠለቀለት፤ ኤፉድ ደረበለት፤ በልዩ ጥበብ በተጠለፈው መታጠቂያ ኤፉዱን አስታጠቀው፤ በላዩም አሰረው፤ 8የደረት ኪሱን በላዩ አደረገለት፤ በደረት ኪሱም ውስጥ ኡሪምንና ቱሚምን አኖረ። 9እግዚአብሔር ባዘዘውም መሠረት፣ ሙሴ መጠምጠሚያውን በአሮን ራስ ላይ አደረገ፤ በመጠምጠሚያው ላይ በፊት ለፊቱ በኩል የተቀደሰውን የወርቅ አክሊል አደረገለት።
10ሙሴም መቅቢያ ዘይቱን ወሰደ፤ ማደሪያ ድንኳኑንና በውስጡ የሚገኘውን ሁሉ ቀብቶ ቀደሰ። 11ከዘይቱም ጥቂት ወስዶ በመሠዊያው ላይ ሰባት ጊዜ ረጨ፤ ይቀድሳቸውም ዘንድ መሠዊያውን ከነመገልገያ ዕቃው ሁሉ እንዲሁም የመታጠቢያ ሳሕኑን ከነማስቀመጫው በዘይት ቀባ። 12ከመቅቢያ ዘይቱም በአሮን ራስ ላይ አፈሰሰ፤ የተቀደሰ እንዲሆንም ቀባው። 13እግዚአብሔርም ባዘዘው መሠረት ሙሴ፣ የአሮንን ልጆች ወደ ፊት አቅርቦ እጀ ጠባብ አለበሳቸው፤ መታጠቂያዎችን አስታጠቃቸው፤ ቆብም ደፋላቸው።
14ሙሴም የኀጢአት መሥዋዕት የሆነውን ወይፈን አመጣ፤ አሮንና ልጆቹም በወይፈኑ ራስ ላይ እጃቸውን ጫኑ። 15ሙሴም ወይፈኑን ዐረደ፤ ደሙንም ወስዶ መሠዊያውን ያነጻ ዘንድ በጣቱ የመሠዊያውን ቀንዶች ሁሉ ቀባ፤ የቀረውንም ደም ከመሠዊያው ሥር አፈሰሰው። ለመሠዊያውም እንዲህ አድርጎ ያስተሰርይለት ዘንድ ቀደሰው። 16ሙሴም የሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ሥብ ሁሉ፣ የጕበቱን ሽፋን፣ ኵላሊቶችንና ሥባቸውን ወስዶ በመሠዊያው ላይ አቃጠለ። 17ሙሴም እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ወይፈኑን፣ ቈዳውን፣ ሥጋውንና ፈርሱን ከሰፈር ውጭ አቃጠለ።
18ሙሴ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን አውራ በግ አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም እጃቸውን በበጉ ላይ ጫኑ። 19ሙሴም በጉን ዐርዶ ደሙን በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን ረጨ። 20በጉንም በየብልቱ ቈራረጠ፤ ሙሴም ጭንቅላቱን፣ ብልቶቹንና ሥቡን አቃጠለ። 21ሆድ ዕቃውንና እግሮቹን በውሃ አጠበ፤ ሙሴም እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት፣ በጉን በሙሉ ለእግዚአብሔር በእሳት የሚቀርብ፣ ሽታውም ደስ የሚያሰኝ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ በመሠዊያው ላይ አቃጠለው።
22ሙሴ ለቅድስና የሚሆነውን ሌላ አውራ በግ አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም እጆቻቸውን በበጉ ራስ ላይ ጫኑ። 23ሙሴ አውራ በጉን ዐረደ፤ ከደሙም ጥቂት ወስዶ የአሮንን ቀኝ ጆሮ ጫፍ፣ የቀኝ እጁን አውራ ጣትና የቀኝ እግሩን አውራ ጣት አስነካ፤ 24የአሮንንም ልጆች ወደ ፊት ጠራ፤ ሙሴም ከደሙ ጥቂት ወስዶ የቀኝ ጆሯቸውን ጫፍ፣ የቀኝ እጃቸውን አውራ ጣትና የቀኝ እግራቸውን አውራ ጣት አስነካ፤ የቀረውንም ደም በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን ረጨ። 25ሥቡን፣ ላቱን፣ ሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ሥብ ሁሉ፣ የጕበቱን ሽፋን፣ ሁለቱን ኵላሊቶችና ሥባቸውን እንዲሁም ቀኝ ወርቹን ወሰደ፤ 26በእግዚአብሔርም ፊት ካለው፣ ያለ እርሾ የተጋገረ ቂጣ ካለበት መሶብ ላይ አንድ ኅብስት፣ አንድ በዘይት የተጋገረ ቂጣ እንዲሁም ስስ ቂጣ ወስዶ በሥቦቹና በቀኝ ወርቹ ላይ አኖረ። 27እነዚህን ሁሉ ለአሮንና ለወንዶች ልጆቹ በእጃቸው ሰጣቸው፤ እነርሱም የሚወዘወዝ መሥዋዕት አድርገው በእግዚአብሔር ፊት ወዘወዙት። 28ሙሴም ከእጃቸው ተቀብሎ፣ ለእግዚአብሔር በእሳት የሚቀርብ፣ መዐዛውም ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት አድርጎ በመሠዊያው ላይ በሚቃጠለው መሥዋዕት ላይ አቃጠለው። 29ሙሴም እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት፣ ድርሻው የሆነውን ክህነት የመስጫውን አውራ በግ ፍርምባ ወስዶ የሚወዘወዝ መሥዋዕት በማድረግ በእግዚአብሔር ፊት ወዘወዘው።
30ቀጥሎም ሙሴ በመቅቢያው ዘይትና በመሠዊያው ላይ ካለው ደም ጥቂት ወስዶ፣ በአሮንና በልብሱ እንዲሁም በአሮን ልጆችና በልብሳቸው ላይ ረጨ፤ በዚህም ሁኔታ አሮንንና ልብሱን፣ ልጆቹንና ልብሳቸውን ቀደሰ።
31ሙሴም አሮንና ልጆቹን እንዲህ አላቸው፤ “ሥጋውን በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ቀቅሉት፤ በዚያም፣ ‘አሮንና ልጆቹ ይብሉት’ ተብዬ በታዘዝሁት#8፥31 ወይም ብዬ ባዘዝሁት መሠረት፣ በክህነት መስጫው መሥዋዕት መሶብ ውስጥ ካለው ቂጣ ጋራ ብሉት፤ 32የተረፈውንም ሥጋና ቂጣ በእሳት አቃጥሉ። 33የክህነት መቀበያችሁ ሥርዐት እስከሚፈጸምበት እስከ ሰባት ቀን ድረስ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ቈዩ፤ ሥርዐቱንም ለመፈጸም ሰባት ቀን ይወስዳልና። 34ዛሬ የተፈጸመው ይህ ሥርዐት ለእናንተ ማስተስረያ እግዚአብሔር ያዘዘው ነው። 35እንዳትሞቱ ሰባቱን ቀንና ሌሊት ከመገናኛው ድንኳን ደጃፍ አትለዩ፤ የእግዚአብሔርንም ሥርዐት ጠብቁ፤ የታዘዝሁት እንዲህ ነውና።” 36አሮንና ልጆቹም እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.