ዘሌዋውያን 8:10-17

ዘሌዋውያን 8:10-17 NASV

ሙሴም መቅቢያ ዘይቱን ወሰደ፤ ማደሪያ ድንኳኑንና በውስጡ የሚገኘውን ሁሉ ቀብቶ ቀደሰ። ከዘይቱም ጥቂት ወስዶ በመሠዊያው ላይ ሰባት ጊዜ ረጨ፤ ይቀድሳቸውም ዘንድ መሠዊያውን ከነመገልገያ ዕቃው ሁሉ እንዲሁም የመታጠቢያ ሳሕኑን ከነማስቀመጫው በዘይት ቀባ። ከመቅቢያ ዘይቱም በአሮን ራስ ላይ አፈሰሰ፤ የተቀደሰ እንዲሆንም ቀባው። እግዚአብሔርም ባዘዘው መሠረት ሙሴ፣ የአሮንን ልጆች ወደ ፊት አቅርቦ እጀ ጠባብ አለበሳቸው፤ መታጠቂያዎችን አስታጠቃቸው፤ ቆብም ደፋላቸው። ሙሴም የኀጢአት መሥዋዕት የሆነውን ወይፈን አመጣ፤ አሮንና ልጆቹም በወይፈኑ ራስ ላይ እጃቸውን ጫኑ። ሙሴም ወይፈኑን ዐረደ፤ ደሙንም ወስዶ መሠዊያውን ያነጻ ዘንድ በጣቱ የመሠዊያውን ቀንዶች ሁሉ ቀባ፤ የቀረውንም ደም ከመሠዊያው ሥር አፈሰሰው። ለመሠዊያውም እንዲህ አድርጎ ያስተሰርይለት ዘንድ ቀደሰው። ሙሴም የሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ሥብ ሁሉ፣ የጕበቱን ሽፋን፣ ኵላሊቶችንና ሥባቸውን ወስዶ በመሠዊያው ላይ አቃጠለ። ሙሴም እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ወይፈኑን፣ ቈዳውን፣ ሥጋውንና ፈርሱን ከሰፈር ውጭ አቃጠለ።