ኢያሱ 24:1-18

ኢያሱ 24:1-18 NASV

ከዚያም ኢያሱ የእስራኤልን ነገዶች ሁሉ በሴኬም ሰበሰበ፤ የእስራኤልንም ሽማግሌዎች፣ መሪዎች፣ ፈራጆችና ሹማምት ጠራ፤ እነርሱም በእግዚአብሔር ፊት ቆሙ። ኢያሱም ሕዝቡን ሁሉ እንዲህ አላቸው፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የቀድሞ አባቶቻችሁ፣ የአብርሃምንና የናኮርን አባት ታራን ጨምሮ ከብዙ ዘመን በፊት ከወንዙ ማዶ ኖሩ፤ ሌሎችንም አማልክት አመለኩ። እኔ ግን አባታችሁን አብርሃምን ከወንዙ ማዶ ካለው ምድር አምጥቼ፣ በከነዓን ምድር ሁሉ መራሁት፤ ዘሮቹን አበዛሁለት፤ ይሥሐቅንም ሰጠሁት። ለይሥሐቅ ያዕቆብንና ዔሳውን ሰጠሁት፤ ለዔሳውም ኰረብታማውን የሴይርን ምድር ርስት አድርጌ ሰጠሁት፤ ያዕቆብና ልጆቹ ግን ወደ ግብጽ ወረዱ። “ ‘ከዚያም ሙሴንና አሮንን ላክሁ፤ ባመጣሁት መቅሠፍት ግብጻውያንን አስጨንቄ፣ እናንተን ከዚያ አወጣኋችሁ። አባቶቻችሁን ከግብጽ ባወጣኋቸው ጊዜ፣ ወደ ባሕሩ መጣችሁ፤ ግብጻውያንም በሠረገሎችና በፈረሰኞች እስከ ቀይ ባሕር ድረስ ተከታተሏቸው። እነርሱ ግን ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እርሱም በእናንተና በግብጻውያን መካከል ጨለማ እንዲሆን አደረገ። ባሕሩን በላያቸው አመጣ፤ አሰጠማቸውም። በግብጻውያን ላይ ያደረግሁትንም ራሳችሁ በዐይናችሁ አያችሁ፤ በምድረ በዳም ብዙ ጊዜ ኖራችሁ። “ ‘በምሥራቅ ዮርዳኖስ ወደሚኖሩት ወደ አሞራውያን ምድር አመጣኋችሁ፤ እነርሱ ወጓችሁ፤ እኔ ግን አሳልፌ በእጃችሁ ሰጠኋቸው፤ ከፊታችሁ አጠፋኋቸው፤ እናንተም ምድራቸውን ወረሳችሁ። የሞዓብ ንጉሥ የሴፎር ልጅ ባላቅ፣ እስራኤልን ለመውጋት ተነሣ፣ እናንተንም መጥቶ ይረግማችሁ ዘንድ ወደ ቢዖር ልጅ ወደ በለዓም መልእክተኛ ላከ፤ እኔ ግን በለዓምን ልሰማው አልፈለግሁም፤ ስለዚህ ደግሞ ደጋግሞ መረቃችሁ፤ እኔም፤ ከባላቅ እጅ ታደግኋችሁ። “ ‘ከዚያም ዮርዳኖስን ተሻገራችሁ፤ ወደ ኢያሪኮ መጣችሁ፤ አሞራውያን፣ ፌርዛውያን፣ ከነዓናውያን፣ ኬጢያውያን፣ ጌርጌሳውያን፣ ኤዊያውያንና ኢያቡሳውያን እንደ ወጓችሁ ሁሉ፣ የኢያሪኮም ገዦች ወጓችሁ፤ እኔ ግን አሳልፌ በእጃችሁ ሰጠኋቸው። በፊታችሁ ተርብ ላክሁ፤ ይህም እነርሱንና ሁለቱን የአሞራውያን ነገሥታት ጭምር ከፊታችሁ አሳደደ፤ ይህ ደግሞ በራሳችሁ ሰይፍና ቀስት ያደረጋችሁት አይደለም። ስለዚህ ያልደከማችሁበትን ምድርና ያልሠራችኋቸውን ከተሞች ሰጠኋችሁ። እነሆ፣ በከተሞቹ ትኖራላችሁ፤ ካልተከላችሁት የወይን ተክልና የወይራ ዛፍ ትበላላችሁ።’ “አሁንም እግዚአብሔርን ፍሩ፤ በፍጹም ታማኝነትም ተገዙለት። የቀድሞ አባቶቻችሁ ከወንዙ ማዶና በግብጽ ያመለኳቸውን አማልክት ከእናንተ አርቁ፤ እግዚአብሔርን ብቻ አምልኩ። እግዚአብሔርን ማምለክ የማያስፈልግ መስሎ ከታያችሁ ግን፣ የቀድሞ አባቶቻችሁ ከወንዙ ማዶ ካመለኳቸው አማልክት ወይም በምድራቸው የምትኖሩባቸው አሞራውያን ከሚያመልኳቸው አማልክት ታመልኩ እንደ ሆነ የምታመልኩትን ዛሬውኑ ምረጡ፤ እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን።” ከዚያም ሕዝቡ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ሌሎችን አማልእክት ለማምለክ ብለን እግዚአብሔርን መተው ከእኛ ይራቅ። እኛንና የቀደሙ አባቶቻችንን ከዚያ ከጦርነት ምድር ከግብጽ ያወጣን፣ በፊታችንም እነዚያን ታላላቅ ምልክቶች ያደረገ ማነው? ራሱ አምላካችን እግዚአብሔር አይደለምን? በጕዟችን ላይና ባለፍንባቸውም ሕዝቦች ሁሉ ዘንድ የጠበቀን እርሱ ነው። እንዲሁም እግዚአብሔር በምድሪቱ የሚኖሩትን አሞራውያንን ጨምሮ ሕዝቦችን ሁሉ ከፊታችን አሳደደ፤ ስለዚህ እኛም እግዚአብሔርን እናመልካለን፤ አምላካችን ነውና።”