ኢያሱ 24:1-18
ኢያሱ 24:1-18 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ኢያሱም የእስራኤልን ነገድ ሁሉ ወደ ሴሎ ሰበሰበ፤ የእስራኤልንም ሽማግሌዎች፥ አለቆቻቸውንም፥ ጸሓፊዎቻቸውንም፥ ፈራጆቻቸውንም ጠራቸው። በእግዚአብሔርም ፊት አቆማቸው። ኢያሱም ለሕዝቡ ሁሉ እንዲህ አለ፥ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘አባቶቻችሁ፥ የአብርሃምና የናኮር አባት ታራ፥ አስቀድመው በወንዝ ማዶ ተቀመጡ፤ ሌሎችንም አማልክት አመለኩ። አባታችሁንም አብርሃምን ከወንዝ ማዶ ወስጄ በከነዓን ምድር ሁሉ መራሁት፤ ዘሩንም አበዛሁ፤ ይስሐቅንም ሰጠሁት። ለይስሐቅም ያዕቆብንና ዔሳውን ሰጠሁት፤ ለዔሳውም የሴይርን ተራራ ርስት አድርጌ ሰጠሁት፤ የያዕቆብም ልጆች ወደ ግብፅ ወረዱ፤ በዚያም ታላቅ ሕዝብ ሆኑ፤ በዙም፤ በረቱም፤ ግብፃውያንም መከራ አጸኑባቸው። ሙሴንና አሮንንም ላክሁ፤ በእነርሱም ላይ ስላደረጉት ነገር ግብፃውያንን ቀሠፍኋቸው፤ ከዚያም በኋላ አባቶቻችሁን ከግብፅ አወጣኋቸው፤ ወደ ባሕሩም ገባችሁ፤ ግብፃውያንም አባቶቻችሁን በሰረገሎችና በፈረሶች እስከ ኤርትራ ባሕር ድረስ ተከተሉአቸው። ወደ እግዚአብሔርም በጮሃችሁ ጊዜ በእናንተና በግብፃውያን መካከል ደመናንና ጭጋግን አደረግሁ፤ ባሕሩንም መለስሁባቸው፤ አሰጠማቸውም፤ ዐይኖቻችሁም በግብፅ ያደረግሁትን አዩ፤ በምድረ በዳም ብዙ ጊዜ ተቀመጣችሁ። በዮርዳኖስ ማዶ ወደ ተቀመጡት ወደ አሞሬዎናውያን ምድርም ወሰድኋችሁ፤ ከእናንተም ጋር ተዋጉ፤ ሙሴም ተዋጋቸው፤ አሳልፌም በእጃችሁ ሰጠኋችሁ፤ ምድራቸውንም ወረሳችሁ፤ ከፊታችሁም አጠፋኋቸው። የሞዓብም ንጉሥ የሴፎር ልጅ ባላቅ ተነሥቶ ከእስራኤል ጋር ተዋጋ፤ እንዲረግማችሁም የቢዖርን ልጅ በለዓምን ልኮ አስጠራው። እኔ ግን ላጠፋችሁ አልወደድሁም፤ መባረክንም ባረክኋችሁ፤ ከእጁም አዳንኋችሁ፤ ዮርዳኖስንም ተሻገራችሁ፤ ወደ ኢያሪኮም መጣችሁ፤ የኢያሪኮም ሰዎች፥ አሞሬዎናዊው፥ ፌርዜዎናዊው፥ ከነዓናዊው፥ ኬጤዎናዊው፥ ጌርጌሴዎናዊው፥ ኤዌዎናዊው፥ ኢያቡሴዎናዊው ተዋጉአችሁ፥ አሳልፌም በእጃችሁ ሰጠኋቸው። በፊታችሁም ተርብ ሰደድሁ፤ በሰይፍህም፥ በቀስትህም ሳይሆን ዐሥራ ሁለቱን የአሞሬዎናውያንን ነገሥታት ከፊታችሁ አሳደድኋቸው። ያልደከማችሁበትንም ምድር፥ ያልሠራችኋቸውንም ከተሞች ሰጠኋችሁ፤ ተቀመጣችሁባቸውም፤ ካልተከላችኋቸውም ከወይንና ከወይራ በላችሁ።’ “አሁንም እግዚአብሔርን ፍሩት፤ በእውነትና በቅንነትም አምልኩት፤ አባቶቻችሁም በወንዝ ማዶ፥ በግብፅም ውስጥ ያመለኩአቸውን ሌሎች አማልክት ከእናንተ አርቁ፤ እግዚአብሔርንም አምልኩ። እግዚአብሔርን ታመልኩ ዘንድ ባትወድዱ ግን፥ አባቶቻችሁ በወንዝ ማዶ ሳሉ ያመለኩአቸውን አማልክት፥ ወይም በምድራቸው ያላችሁባቸውን የአሞሬዎናውያንን አማልክት ታመልኩ እንደ ሆነ፥ የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ። እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን፤ እርሱ ቅዱስ ነውና።” ሕዝቡም መልሰው እንዲህ አሉ፥ “እግዚአብሔርን ትተን ሌሎች አማልክትን ማምለክ ከእኛ ይራቅ፤ እኛንና አባቶቻችንን ከባርነት ቤት ከግብፅ ምድር ያወጣን፥ በዐይናችንም ፊት እነዚያን ታላላቅ ተአምራት ያደረገ፥ በሄድንባትም መንገድ ሁሉ፥ ባለፍንባቸውም አሕዛብ ሁሉ መካከል የጠበቀን፥ እርሱ አምላካችን እግዚአብሔር ነውና። እግዚአብሔር አሕዛብን ሁሉ፥ በምድሪቱም የተቀመጡትን አሞሬዎናውያንን ከፊታችን አሳደደ፤ ስለዚህ እርሱ አምላካችን ነውና እኛ እግዚአብሔርን እናመልካለን።”
ኢያሱ 24:1-18 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚያም ኢያሱ የእስራኤልን ነገዶች ሁሉ በሴኬም ሰበሰበ፤ የእስራኤልንም ሽማግሌዎች፣ መሪዎች፣ ፈራጆችና ሹማምት ጠራ፤ እነርሱም በእግዚአብሔር ፊት ቆሙ። ኢያሱም ሕዝቡን ሁሉ እንዲህ አላቸው፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የቀድሞ አባቶቻችሁ፣ የአብርሃምንና የናኮርን አባት ታራን ጨምሮ ከብዙ ዘመን በፊት ከወንዙ ማዶ ኖሩ፤ ሌሎችንም አማልክት አመለኩ። እኔ ግን አባታችሁን አብርሃምን ከወንዙ ማዶ ካለው ምድር አምጥቼ፣ በከነዓን ምድር ሁሉ መራሁት፤ ዘሮቹን አበዛሁለት፤ ይሥሐቅንም ሰጠሁት። ለይሥሐቅ ያዕቆብንና ዔሳውን ሰጠሁት፤ ለዔሳውም ኰረብታማውን የሴይርን ምድር ርስት አድርጌ ሰጠሁት፤ ያዕቆብና ልጆቹ ግን ወደ ግብጽ ወረዱ። “ ‘ከዚያም ሙሴንና አሮንን ላክሁ፤ ባመጣሁት መቅሠፍት ግብጻውያንን አስጨንቄ፣ እናንተን ከዚያ አወጣኋችሁ። አባቶቻችሁን ከግብጽ ባወጣኋቸው ጊዜ፣ ወደ ባሕሩ መጣችሁ፤ ግብጻውያንም በሠረገሎችና በፈረሰኞች እስከ ቀይ ባሕር ድረስ ተከታተሏቸው። እነርሱ ግን ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እርሱም በእናንተና በግብጻውያን መካከል ጨለማ እንዲሆን አደረገ። ባሕሩን በላያቸው አመጣ፤ አሰጠማቸውም። በግብጻውያን ላይ ያደረግሁትንም ራሳችሁ በዐይናችሁ አያችሁ፤ በምድረ በዳም ብዙ ጊዜ ኖራችሁ። “ ‘በምሥራቅ ዮርዳኖስ ወደሚኖሩት ወደ አሞራውያን ምድር አመጣኋችሁ፤ እነርሱ ወጓችሁ፤ እኔ ግን አሳልፌ በእጃችሁ ሰጠኋቸው፤ ከፊታችሁ አጠፋኋቸው፤ እናንተም ምድራቸውን ወረሳችሁ። የሞዓብ ንጉሥ የሴፎር ልጅ ባላቅ፣ እስራኤልን ለመውጋት ተነሣ፣ እናንተንም መጥቶ ይረግማችሁ ዘንድ ወደ ቢዖር ልጅ ወደ በለዓም መልእክተኛ ላከ፤ እኔ ግን በለዓምን ልሰማው አልፈለግሁም፤ ስለዚህ ደግሞ ደጋግሞ መረቃችሁ፤ እኔም፤ ከባላቅ እጅ ታደግኋችሁ። “ ‘ከዚያም ዮርዳኖስን ተሻገራችሁ፤ ወደ ኢያሪኮ መጣችሁ፤ አሞራውያን፣ ፌርዛውያን፣ ከነዓናውያን፣ ኬጢያውያን፣ ጌርጌሳውያን፣ ኤዊያውያንና ኢያቡሳውያን እንደ ወጓችሁ ሁሉ፣ የኢያሪኮም ገዦች ወጓችሁ፤ እኔ ግን አሳልፌ በእጃችሁ ሰጠኋቸው። በፊታችሁ ተርብ ላክሁ፤ ይህም እነርሱንና ሁለቱን የአሞራውያን ነገሥታት ጭምር ከፊታችሁ አሳደደ፤ ይህ ደግሞ በራሳችሁ ሰይፍና ቀስት ያደረጋችሁት አይደለም። ስለዚህ ያልደከማችሁበትን ምድርና ያልሠራችኋቸውን ከተሞች ሰጠኋችሁ። እነሆ፣ በከተሞቹ ትኖራላችሁ፤ ካልተከላችሁት የወይን ተክልና የወይራ ዛፍ ትበላላችሁ።’ “አሁንም እግዚአብሔርን ፍሩ፤ በፍጹም ታማኝነትም ተገዙለት። የቀድሞ አባቶቻችሁ ከወንዙ ማዶና በግብጽ ያመለኳቸውን አማልክት ከእናንተ አርቁ፤ እግዚአብሔርን ብቻ አምልኩ። እግዚአብሔርን ማምለክ የማያስፈልግ መስሎ ከታያችሁ ግን፣ የቀድሞ አባቶቻችሁ ከወንዙ ማዶ ካመለኳቸው አማልክት ወይም በምድራቸው የምትኖሩባቸው አሞራውያን ከሚያመልኳቸው አማልክት ታመልኩ እንደ ሆነ የምታመልኩትን ዛሬውኑ ምረጡ፤ እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን።” ከዚያም ሕዝቡ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ሌሎችን አማልእክት ለማምለክ ብለን እግዚአብሔርን መተው ከእኛ ይራቅ። እኛንና የቀደሙ አባቶቻችንን ከዚያ ከጦርነት ምድር ከግብጽ ያወጣን፣ በፊታችንም እነዚያን ታላላቅ ምልክቶች ያደረገ ማነው? ራሱ አምላካችን እግዚአብሔር አይደለምን? በጕዟችን ላይና ባለፍንባቸውም ሕዝቦች ሁሉ ዘንድ የጠበቀን እርሱ ነው። እንዲሁም እግዚአብሔር በምድሪቱ የሚኖሩትን አሞራውያንን ጨምሮ ሕዝቦችን ሁሉ ከፊታችን አሳደደ፤ ስለዚህ እኛም እግዚአብሔርን እናመልካለን፤ አምላካችን ነውና።”
ኢያሱ 24:1-18 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ኢያሱም የእስራኤልን ነገድ ሁሉ ወደ ሴኬም ሰበሰበ፥ የእስራኤልንም ሽማግሌዎች አለቆቻቸውንም ፈራጆቻቸውንም ሹማምቶቻቸውንም ጠራ። እነርሱም በእግዚአብሔር ፊት ቆሙ። ኢያሱም ለሕዝቡ ሁሉ እንዲህ አለ፦ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ አባቶቻችሁ፥ የአብርሃምና የናኮር አባት ታራ፥ አስቀድመው በወንዝ ማዶ ተቀመጡ፥ ሌሎችንም አማልክት አመለኩ። አባታችሁንም አብርሃምን ከወንዝ ማዶ ወስጄ በከነዓን ምድር ሁሉ መራሁት፥ ዘሩንም አበዛሁ፥ ይስሐቅንም ሰጠሁት። ለይስሐቅም ያዕቆብንና ዔሳውን ሰጠሁት፥ ለዔሳውም የሴይርን ተራራ ርስት አድርጌ ሰጠሁት፥ ያዕቆብም ልጆቹም ወደ ግብፅ ወረዱ። ሙሴንና አሮንንም ላክሁ፥ በመካከላቸውም እንዳደረግሁ ግብፅን ቀሠፍሁ፥ ከዚያም በኋላ አወጣኋቸው። አባቶቻችሁንም ከግብፅ አወጣኋቸው፥ ወደ ባሕሩም ደረሳችሁ፥ ግብፃውያንም አባቶቻችሁን በሰረገሎችና በፈረሰኞች እስከ ኤርትራ ባሕር ድረስ አባረሩአቸው። ወደ እግዚአብሔርም በጮኹ ጊዜ በእናንተና በግብፃውያን መካከል ጨለማ አደረገ፥ ባሕሩንም መለሰባቸው፥ አሰጠማቸውም፥ ዓይኖቻችሁም በግብፅ ያደረግሁትን አዩ፥ በምድረ በዳም ብዙ ጊዜ ተቀመጣችሁ። እኔም በዮርዳኖስ ማዶ ወደ ተቀመጡበት ወደ አሞራውያን ምድር አመጣኋችሁ፥ ከእናንተም ጋር ተዋጉ፥ አሳልፌም በእጃችሁ ሰጠኋችሁ፥ ምድራቸውንም ወረሳችሁ፥ ከፊታችሁም አጠፋኋቸው። የሞዓብም ንጉሥ የሴፎር ልጅ ባላቅ ተነሥቶ ከእስራኤል ጋር ተዋጋ፥ እንዲረግማችሁም የቢዖርን ልጅ በለዓምን ልኮ አስጠራው። እኔ ግን በለዓምን መስማት አልወደድሁም፥ እርሱም ፈጽሞ ባረካችሁ፥ እኔም ከእጁ አዳንኋችሁ። ዮርዳኖስንም ተሻገራችሁ፥ ወደ ኢያሪኮም መጣችሁ፥ የኢያሪኮም ሰዎች፥ አሞራዊው፥ ፌርዛዊው፥ ከነዓናዊው፥ ኬጢያዊው፥ ጌርጌሳዊው፥ ኤዊያዊው፥ ኢያቡሳዊው ተዋጉአችሁ፥ አሳልፌም በእጃችሁ ሰጠኋቸው። በፊታችሁም ተርብ ሰደድሁ፥ በሰይፍህም በቀሥትህም ሳይሆን ሁለቱን የአሞራውያንን ነገሥታት ከፊታችሁ አሳደዳቸው። ያልደከማችሁበትንም ምድር፥ ያልሠራችኋቸውንም ከተሞች ሰጠኋችሁ፥ ተቀመጣችሁባቸውም፥ ካልተከላችኋቸውም ከወይንና ከወይራ በላችሁ። አሁንም እግዚአብሔርን ፍሩ፥ በፍጹምም በእውነተኛም ልብ አምልኩት፥ አባቶቻችሁም በወንዝ ማዶ በግብፅም ውስጥ ያመለኩአቸውን አማልክት ከእናንተ አርቁ፥ እግዚአብሔርንም አምልኩ። እግዚአብሔርንም ማምለክ ክፉ መስሎ ቢታያችሁ፥ አባቶቻችሁ በወንዝ ማዶ ሳሉ ያመለኩአቸውን አማልክት ወይም በምድራቸው ያላችሁባቸውን የአሞራውያንን አማልክት ታመልኩ እንደ ሆነ፥ የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ። እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን። ሕዝቡም መልሰው እንዲህ አሉ፦ እግዚአብሔርን ትተን ሌሎችን አማልክትን ማምለክ ከእኛ ይራቅ፥ እኛንና አባቶቻችንን ከባርነት ቤት ከግብፅ ምድር ያወጣን፥ በዓይናችንም ፊት እነዚያን ታላላቅ ተአምራት ያደረገ፥ በሄድንባትም መንገድ ሁሉ ባለፍንባቸውም አሕዛብ ሁሉ መካከል የጠበቀን፥ እርሱ አምላካችን እግዚአብሔር ነውና። እግዚአብሔር አሕዛብን ሁሉ፥ በምድሪቱ የተቀመጡትን አሞራውያን ከፊታችን አሳደደ፥ ስለዚህ እርሱ አምላካችን ነውና እግዚአብሔርን እናመልካለን።
ኢያሱ 24:1-18 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኢያሱ የእስራኤልን ነገዶች በሙሉ በሴኬም በአንድነት ሰበሰበ፤ ሽማግሌዎችን፥ አለቆቻቸውን፥ ዳኞችንና የእስራኤልን የጦር አዛዦች ሁሉ ጠራ፤ እነርሱም በእግዚአብሔር ፊት ተሰበሰቡ፤ ኢያሱም ለሕዝቡ ሁሉ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፦ ‘ከብዙ ዘመናት በፊት የቀድሞ አባቶቻችሁ ከኤፍራጥስ ወንዝ ማዶ ባዕዳን አማልክትን በማምለክ ይኖሩ ነበር፤ ከነዚያም አባቶች አንዱ የአብርሃምና የናኮር አባት ታራ ነበር፤ ከዚህም በኋላ የቀድሞ አባታችሁን አብርሃምን ከኤፍራጥስ ወንዝ ማዶ ከሚገኘው ምድር ጠርቼ፥ በከነዓን ምድር ሁሉ መራሁት፤ ዘሩንም አበዛሁለት፤ ይስሐቅንም ሰጠሁት፤ ለይስሐቅም ያዕቆብንና ዔሳውን ሰጠሁ፤ ለዔሳውም የኤዶምን ኮረብታማ አገር ርስት አድርጌ ሰጠሁት፤ ነገር ግን ያዕቆብና ልጆቹ ወደ ግብጽ ወረዱ፤ ከዚያም በኋላ ሙሴንና አሮንን ላክሁ፤ ግብጽንም በመቅሠፍት መታሁ፤ በመጨረሻም እናንተን አወጣኋችሁ፤ የቀድሞ አባቶቻችሁን ከግብጽ ባወጣኋቸው ጊዜ ወደ ባሕር ደረሱ፤ ግብጻውያንም በሠረገሎችና በፈረሰኞች እስከ ቀይ ባሕር ድረስ ባሳደዱአቸው ጊዜ፥ እረዳቸው ዘንድ ወደ እኔ ጮኹ፤ እኔም በእነርሱና በግብጻውያን መካከል ጨለማ እንዲሆን አደረግሁ። ባሕሩም እንዲከነበልባቸው አድርጌ ግብጻውያንን አሰጠምሁ፤ በግብጻውያን ላይ ምን እንዳደረግሁ በዐይኖቻችሁ አይታችኋል፤ ከዚያም በኋላ እናንተ ለብዙ ጊዜ በበረሓ ኖራችሁ። ከዚህም በኋላ ከዮርዳኖስ በስተምሥራቅ ወደሚኖሩት ወደ አሞራውያን ምድር አመጣኋችሁ፤ እነርሱ ተዋጉአችሁ፤ እኔ ግን በእነርሱ ላይ ድልን አቀዳጀኋቸው፤ ከፊታችሁም አጠፋኋቸው፤ ምድራቸውንም ወረሳችሁ። ከዚህም በኋላ የሞአብ ንጉሥ የነበረው የጲፖር ልጅ ባላቅ ሊወጋችሁ በእናንተ ላይ ተነሣሣ፤ እናንተንም ይረግምለት ዘንድ በለዓም ተብሎ ወደሚጠራው ወደ ቢዖር ልጅ መልእክት ላከ፤ እኔ ግን በለዓምን አልሰማሁትም፤ ስለዚህም በመርገም ፈንታ ባረካችሁ፤ በዚህም ዐይነት ከባላቅ እጅ አዳንኳችሁ፤ እናንተም የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግራችሁ ወደ ኢያሪኮ መጣችሁ፤ የኢያሪኮም ሰዎች፥ እንዲሁም አሞራውያን፥ ፈሪዛውያን፥ ከነዓናውያን፥ ሒታውያን፥ ጌርጌሳውያን፥ ሒዋውያንና ኢያቡሳውያን እናንተን ለመውጋት ተነሡ፤ እኔ ግን በእነርሱ ላይ ድልን አቀዳጀኋችሁ። በሁለቱ አሞራውያን ነገሥታት ላይ እንዳደረግሁት አስቀድሜ ከፊታችሁ ያባረራቸውን ተርብ ሰደድኩባቸው፤ ይህ በእናንተ ሰይፍ ወይም በእናንተ ቀስት የሆነ አይደለም። እናንተ በማረስ ያልደከማችሁበትን የለማ ምድርና ያልሠራችኋቸውንም ከተሞች መኖሪያ አድርጌ ሰጠኋችሁ፤ እነሆ፥ አሁን ያልተከላችሁትን የወይን ተክልና ያልደከማችሁበትን የወይራ ዛፍ ፍሬ እየተመገባችሁ ትኖራላችሁ።’ ” ኢያሱ ንግግሩን በመቀጠል እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ እግዚአብሔርን አክብሩት፤ በፍጹም ቅንነትና በታማኝነት አገልግሉት፤ የቀድሞ አባቶቻችሁ ከኤፍራጥስ ወንዝ ማዶና በግብጽ ይሰግዱላቸው የነበሩትን ባዕዳን አማልክት አስወግዳችሁ እግዚአብሔርን ብቻ አምልኩ፤ እርሱን ማምለክ መልካም መስሎ ካልታያችሁ ግን የቀድሞ አባቶቻችሁ ከኤፍራጥስ ወንዝ ማዶ በነበሩበት ጊዜ ያመልኩአቸው የነበሩትን ወይም አሁን በምድራቸው የምትኖሩባቸውን የአሞራውያንን አማልክት ታመልኩ እንደሆን የምታመልኩትን ዛሬውኑ ምረጡ፤ እኔና ቤተሰቤ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን።” ሕዝቡም እንዲህ ሲሉ መለሱለት፤ “እግዚአብሔርን ትተን ሌሎች ባዕዳን አማልክትን ማምለክ ከእኛ ይራቅ! አምላካችን እግዚአብሔር አባቶቻችንንና እኛን ከግብጽ ባርነት አውጥቶናል፤ ያደረገውን ተአምራት ሁሉ አይተናል፤ ሕዝቦችን ሁሉ አልፈን በመጣንበት ጊዜ በሰላም ጠብቆናል፤ እግዚአብሔር ሕዝቦችን እንዲሁም በምድሪቱ የሚኖሩትን አሞራውያንን ሁሉ ከፊታችን አባሮልናል፤ ስለዚህም እርሱ አምላካችን ስለ ሆነ እግዚአብሔርን እናመልካለን።”
ኢያሱ 24:1-18 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ኢያሱም የእስራኤልን ነገድ ሁሉ ወደ ሴኬም ሰበሰበ፥ የእስራኤልንም ሽማግሌዎች አለቆቻቸውንም ፈራጆቻቸውንም ሹማምንቶቻቸውንም ጠራ። እነርሱም በጌታ ፊት ቆሙ። ኢያሱም ለሕዝቡ ሁሉ እንዲህ አለ፦ “የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘አባቶቻችሁ፥ የአብርሃምና የናኮር አባት ታራ፥ አስቀድመው በወንዝ ማዶ ተቀመጡ፤ ሌሎችንም አማልክት አመለኩ። አባታችሁንም አብርሃምን ከወንዝ ማዶ ወስጄ በከነዓን ምድር ሁሉ መራሁት፤ ዘሩንም አበዛሁ፥ ይስሐቅንም ሰጠሁት። ለይስሐቅም ያዕቆብንና ዔሳውን ሰጠሁት፤ ለዔሳውም የሴይርን ተራራ ርስት አድርጌ ሰጠሁት፤ ያዕቆብም ልጆቹም ወደ ግብጽ ወረዱ። ሙሴንና አሮንንም ላክሁ፥ በመካከላቸውም እንዳደረግሁ ግብጽን ቀሠፍሁ፤ ከዚያም በኋላ እናንተን አወጣሁ። አባቶቻችሁንም ከግብጽ አወጣኋቸው፥ ወደ ባሕሩም ደረሳችሁ፤ ግብፃውያንም አባቶቻችሁን በሰረገሎችና በፈረሰኞች እስከ ኤርትራ ባሕር ድረስ አባረሩአቸው። ወደ ጌታም በጮኹ ጊዜ በእናንተና በግብፃውያን መካከል ጨለማ አደረገ፥ ባሕሩንም መለሰባቸው፥ አሰጠማቸውም፤ ዐይኖቻችሁም በግብጽ ያደረግሁትን አዩ፤ በምድረ በዳም ብዙ ጊዜ ተቀመጣችሁ። እኔም በዮርዳኖስ ማዶ ወደ ተቀመጡበት ወደ አሞራውያን ምድር አመጣኋችሁ፤ ከእናንተም ጋር ተዋጉ፥ አሳልፌም በእጃችሁ ሰጠኋችሁ፥ ምድራቸውንም ወረሳችሁ፤ ከፊታችሁም አጠፋኋቸው። የሞዓብም ንጉሥ የሴፎር ልጅ ባላቅ ተነሥቶ ከእስራኤል ጋር ተዋጋ፤ እንዲረግማችሁም የቢዖርን ልጅ በለዓምን ልኮ አስጠራው። እኔ ግን በለዓምን መስማት አልፈለግሁም፤ እርሱም ፈጽሞ ባረካችሁ፥ እኔም ከእጁ አዳንኋችሁ። ዮርዳኖስንም ተሻገራችሁ፥ ወደ ኢያሪኮም መጣችሁ፤ የኢያሪኮም ሰዎች፥ አሞራዊው፥ ፌርዛዊው፥ ከነዓናዊው፥ ኬጢያዊው፥ ጌርጌሳዊው፥ ኤዊያዊው፥ ኢያቡሳዊው ተዋጉአችሁ፤ አሳልፌም በእጃችሁ ሰጠኋቸው። በሰይፍህም በቀሥትህም ሳይሆን በፊታችሁም ተርብ ሰድጄ ሁለቱን የአሞራውያንን ነገሥታት ከፊታችሁ አሳደዳቸው። ያልደከማችሁበትንም ምድር፥ ያልሠራችኋቸውንም ከተሞች ሰጠኋችሁ፥ ተቀመጣችሁባቸውም፤ ካልተከላችኋቸውም ከወይንና ከወይራ በላችሁ።’ “እንግዲህ አሁን ጌታን ፍሩ፥ በፍጹም ቅንነትና ታማኝነት አገልግሉት፤ አባቶቻችሁም በወንዝ ማዶ በግብጽም ውስጥ ያመለኩአቸውን አማልክት ከእናንተ አርቁ፥ ጌታንም አምልኩ። ጌታንም ማገልገል ክፉ መስሎ ቢታያችሁ፥ አባቶቻችሁ በወንዝ ማዶ ሳሉ ያገለገሉአቸውን አማልክት ወይም በምድራቸው የተቀመጣችሁባቸውን የአሞራውያንን አማልክት ታገለግሉ እንደሆነ፥ የምታገለግሉትን ዛሬ ምረጡ። እኔና ቤቴ ግን ጌታን እናገለግላለን።” ሕዝቡም መልሰው እንዲህ አሉ፦ “ጌታን ትተን ሌሎችን አማልክትን ማገልገል ከእኛ ይራቅ፤ እኛንና አባቶቻችንን ከባርነት ቤት ከግብጽ ምድር ያወጣን፥ በዓይናችንም ፊት እነዚያን ታላላቅ ተአምራት ያደረገ፥ በሄድንባትም መንገድ ሁሉ ባለፍንባቸውም አሕዛብ ሁሉ መካከል የጠበቀን፥ እርሱ ጌታ አምላካችን ነውና። ጌታ አሕዛብን ሁሉ፥ በምድሪቱ የተቀመጡትን አሞራውያን ከፊታችን አሳደደ፤ ስለዚህ እርሱ አምላካችን ነውና ጌታን እናገለግላለን።”