ኢያሱ 10:1-15

ኢያሱ 10:1-15 NASV

የኢየሩሳሌም ንጉሥ አዶኒጼዴቅ፣ ኢያሱ ጋይን ይዞ እንደ ደመሰሳት፣ እንደዚሁም በኢያሪኮና በንጉሧ ላይ ያደረገውን ሁሉ፣ በጋይና በንጉሧ ላይ ማድረጉን፣ የገባዖን ሰዎችም ከእስራኤል ጋራ የሰላም ውል አድርገው በአጠገባቸው መኖራቸውን ሰማ። በዚህም እርሱና ሕዝቡ ደነገጡ፤ ምክንያቱም ገባዖን እንደ ነገሥታቱ ከተማ ሁሉ ታላቅ ከተማ፣ በስፋቷም ከጋይ የምትበልጥ፣ ሰዎቿም ብርቱ ተዋጊዎች ነበሩ። ስለዚህ የኢየሩሳሌም ንጉሥ አዶኒጼዴቅ፣ ሆሃም ወደተባለው የኬብሮን ንጉሥ ጲርአም ወደተባለው የያርሙት ንጉሥ፣ ያፊዓ ወደተባለው የለኪሶ ንጉሥና ዳቤር ወደተባለው የዔግሎን ንጉሥ በመላክ፣ “ወደዚህ ወጥታችሁ አግዙኝ፤ ከኢያሱና ከእስራኤላውያን ጋራ ሰላምን መሥርታለችና ገባዖንን እንምታ” አላቸው። ከዚያም ዐምስቱ የአሞራውያን ነገሥታት ማለት የኢየሩሳሌም ንጉሥ፣ የኬብሮን ንጉሥ፣ የያርሙት ንጉሥ፣ የለኪሶ ንጉሥና የዔግሎን ንጉሥ ያላቸውን አስተባብረው፣ ሰራዊታቸውንም ሁሉ ይዘው በመውጣት ገባዖንን ወጓት። የገባዖንም ሰዎች በጌልገላ ወደ ሰፈረው ወደ ኢያሱ፣ “በተራራማው አገር የሚኖሩ የአሞራውያን ነገሥታት ኀይላቸውን አስተባብረው ተሰልፈውብናል፤ እኛን ባሮችህን አትተወን፤ ርዳን፤ ፈጥነህ በመድረስም አድነን” ሲሉ ላኩበት። ስለዚህ ኢያሱ ምርጥ የሆኑትን ተዋጊዎች ሁሉ ጨምሮ ሰራዊቱን በሙሉ ይዞ ከጌልገላ ወጣ። እግዚአብሔርም ኢያሱን፣ “አትፍራቸው፤ ሁሉንም አሳልፌ በእጅህ ሰጥቻቸዋለሁ፤ አንዳቸውም እንኳ ሊቋቋሙህ አይችሉም” አለው። ኢያሱ ከጌልገላ ሌሊቱን ሁሉ ሲገሠግሥ ዐድሮ ድንገት ወረራቸው። እግዚአብሔርም የአሞራውያንን ነገሥታት በእስራኤል ፊት አሸበራቸው፤ በገባዖን እጅግ መታቸው፤ ወደ ቤትሖሮን በሚያስወጣውም መንገድ ሽቅብ ተከተላቸው፤ እስከ ዓዜቅና እስከ መቄዳም ድረስ አሳድዶ መታቸው። ከቤትሖሮን ወደ ዓዜቃ ቍልቍል በሚወስደው መንገድ ላይ፣ ከእስራኤላውያን ፊት በሚሸሹበት ጊዜ፣ እግዚአብሔር ከሰማይ ትልልቅ የበረዶ ድንጋይ አወረደባቸው፤ በእስራኤላውያን ሰይፍ ካለቁት ይልቅ በወረደው የበረዶ ድንጋይ ያለቁት በልጠው ተገኙ። እግዚአብሔር አሞራውያንን ለእስራኤል አሳልፎ በሰጠባት ዕለት፣ ኢያሱ እግዚአብሔርን በእስራኤል ፊት እንዲህ አለው፤ “ፀሓይ ሆይ፤ በገባዖን ላይ ቁሚ፤ ጨረቃም ሆይ፤ በኤሎን ሸለቆ ላይ ቀጥ በዪ።” ስለዚህ ሕዝቡ ጠላቶቹን እስኪበቀል ድረስ፣ ፀሓይ ባለችበት ቆመች፤ ጨረቃም አልተንቀሳቀሰችም። ይህም በያሻር መጽሐፍ ተጽፎ ይገኛል። ፀሓይ በሰማዩ መካከል ቆመች፤ ለመጥለቅም ሙሉ ቀን ፈጀባት። እግዚአብሔር የሰውን ቃል የሰማበት እንደዚያ ያለ ዕለት ከዚያ በፊትም ሆነ ከዚያ በኋላ አልነበረም፤ እግዚአብሔር ለእስራኤል ተዋግቶ ነበርና። ከዚያም ኢያሱ ከመላው እስራኤል ጋራ ጌልገላ ወዳለው ሰፈር ተመለሰ።