ኢዮብ 5:1-27

ኢዮብ 5:1-27 NASV

“እስኪ ተጣራ፤ የሚመልስልህ አለን? ከቅዱሳንስ ወደ ማንኛው ዘወር ትላለህ? ቂሉን ሰው ብስጭት ይገድለዋል፤ ቂሉንም ቅናት ያጠፋዋል። ቂል ሰው ሥር ሰድዶ አየሁት፤ ግን ድንገት ቤቱ ተረገመ። ልጆቹ የኑሮ ዋስትና የራቃቸው፤ በፍርድ አደባባይ ጥቃት የደረሰባቸው፣ ታዳጊ የሌላቸው ናቸው። ከእሾኽ መካከል እንኳ አውጥቶ፣ ራብተኛ ሰብሉን ይበላበታል፤ ጥማተኛም ሀብቱን ይመኝበታል። ችግር ከምድር አይፈልቅም፤ መከራም ከመሬት አይበቅልም። ፍንጣሪው ከእሳቱ ላይ ሽቅብ እንደሚወረወር፣ ሰውም ለመከራ ይወለዳል። “እኔ ብሆን ኖሮ፣ ወደ እግዚአብሔር በቀረብሁ፣ ጕዳዬንም በፊቱ በገለጽሁለት ነበር። እርሱ፣ የማይመረመሩ ድንቅ ነገሮች፣ የማይቈጠሩም ታምራት ያደርጋል። ምድሪቱን በዝናብ ያረሰርሳል፤ ሜዳውንም ውሃ ያጠጣል። የተዋረዱትን በከፍታ ቦታ ያስቀምጣል፤ ያዘኑትንም ወደ አስተማማኝ ስፍራ ያወጣቸዋል። እጃቸው ያሰቡትን እንዳይፈጽም፣ የተንኰለኞችን ዕቅድ ያከሽፋል። ጥበበኞችን በራሳቸው ተንኰል ይይዛቸዋል፤ የጠማሞችንም ሤራ ያጠፋል። ቀኑ ጨለማ ይሆንባቸዋል፤ በቀትርም ጊዜ በሌሊት እንዳለ ሰው በዳበሳ ይሄዳሉ። ድኻውን ከአፋቸው ሰይፍ፣ ከኀይለኛውም እጅ ያድነዋል። ስለዚህ ድኻ ተስፋ አለው፤ ዐመፅም አፏን ትዘጋለች። “እነሆ፤ እግዚአብሔር የሚገሥጸው ሰው ብፁዕ ነው፤ ስለዚህ ሁሉን ቻይ አምላክ ተግሣጽ አትናቅ። እርሱ ያቈስላል፤ ይፈውሳል፤ እርሱ ይሰብራል፤ በእጁም ይጠግናል፤ እርሱ ከስድስት መቅሠፍት ይታደግሃል፤ በሰባተኛውም ጕዳት አያገኝህም። በራብ ጊዜ ከሞት፣ በጦርነትም ከሰይፍ ያድንሃል። ከምላስ ጅራፍ ትሰወራለህ፤ ጥፋት ሲመጣም አትፈራም። በጥፋትና በራብ ላይ ትሥቃለህ፤ የምድርንም አራዊት አትፈራም። ከሜዳ ድንጋዮች ጋራ ትዋዋላለህና፤ የዱር አራዊትም ከአንተ ጋራ ይስማማሉ። ድንኳንህ በሚያስተማምን ሁኔታ እንዳለ ታውቃለህ፤ በረትህን ትቃኛለህ፤ አንዳችም አይጐድልብህም። ዘሮችህ አያሌ እንደሚሆኑ፣ የምትወልዳቸውም እንደ ሣር እንደሚበዙ ታውቃለህ። የእህል ነዶ ጐምርቶ በወቅቱ እንደሚሰበሰብ፣ ዕድሜ ጠግበህ ወደ መቃብር ትሄዳለህ። “እነሆ፤ ይህን ሁሉ መርምረናል፤ እውነት ሆኖ አግኝተነዋል፤ ስለዚህ ልብ በል፤ ተቀበለውም።”