ኢዮብ 5

5
1“እስኪ ተጣራ፤ የሚመልስልህ አለን?
ከቅዱሳንስ ወደ ማንኛው ዘወር ትላለህ?
2ቂሉን ሰው ብስጭት ይገድለዋል፤
ቂሉንም ቅናት ያጠፋዋል።
3ቂል ሰው ሥር ሰድዶ አየሁት፤
ግን ድንገት ቤቱ ተረገመ።
4ልጆቹ የኑሮ ዋስትና የራቃቸው፤
በፍርድ አደባባይ ጥቃት የደረሰባቸው፣ ታዳጊ የሌላቸው ናቸው።
5ከእሾኽ መካከል እንኳ አውጥቶ፣
ራብተኛ ሰብሉን ይበላበታል፤
ጥማተኛም ሀብቱን ይመኝበታል።
6ችግር ከምድር አይፈልቅም፤
መከራም ከመሬት አይበቅልም።
7ፍንጣሪው ከእሳቱ ላይ ሽቅብ እንደሚወረወር፣
ሰውም ለመከራ ይወለዳል።
8“እኔ ብሆን ኖሮ፣ ወደ እግዚአብሔር በቀረብሁ፣
ጕዳዬንም በፊቱ በገለጽሁለት ነበር።
9እርሱ፣ የማይመረመሩ ድንቅ ነገሮች፣
የማይቈጠሩም ታምራት ያደርጋል።
10ምድሪቱን በዝናብ ያረሰርሳል፤
ሜዳውንም ውሃ ያጠጣል።
11የተዋረዱትን በከፍታ ቦታ ያስቀምጣል፤
ያዘኑትንም ወደ አስተማማኝ ስፍራ ያወጣቸዋል።
12እጃቸው ያሰቡትን እንዳይፈጽም፣
የተንኰለኞችን ዕቅድ ያከሽፋል።
13ጥበበኞችን በራሳቸው ተንኰል ይይዛቸዋል፤
የጠማሞችንም ሤራ ያጠፋል።
14ቀኑ ጨለማ ይሆንባቸዋል፤
በቀትርም ጊዜ በሌሊት እንዳለ ሰው በዳበሳ ይሄዳሉ።
15ድኻውን ከአፋቸው ሰይፍ፣
ከኀይለኛውም እጅ ያድነዋል።
16ስለዚህ ድኻ ተስፋ አለው፤
ዐመፅም አፏን ትዘጋለች።
17“እነሆ፤ እግዚአብሔር የሚገሥጸው ሰው ብፁዕ ነው፤
ስለዚህ ሁሉን ቻይ#5፥17 በዕብራይስጥ ሻዳይ ማለት ሲሆን፣ በዚህ ቍጥርና በኢዮብ መጽሐፍ ውስጥም እንዲሁ ነው። አምላክ ተግሣጽ አትናቅ።
18እርሱ ያቈስላል፤ ይፈውሳል፤
እርሱ ይሰብራል፤ በእጁም ይጠግናል፤
19እርሱ ከስድስት መቅሠፍት ይታደግሃል፤
በሰባተኛውም ጕዳት አያገኝህም።
20በራብ ጊዜ ከሞት፣
በጦርነትም ከሰይፍ ያድንሃል።
21ከምላስ ጅራፍ ትሰወራለህ፤
ጥፋት ሲመጣም አትፈራም።
22በጥፋትና በራብ ላይ ትሥቃለህ፤
የምድርንም አራዊት አትፈራም።
23ከሜዳ ድንጋዮች ጋራ ትዋዋላለህና፤
የዱር አራዊትም ከአንተ ጋራ ይስማማሉ።
24ድንኳንህ በሚያስተማምን ሁኔታ እንዳለ ታውቃለህ፤
በረትህን ትቃኛለህ፤ አንዳችም አይጐድልብህም።
25ዘሮችህ አያሌ እንደሚሆኑ፣
የምትወልዳቸውም እንደ ሣር እንደሚበዙ ታውቃለህ።
26የእህል ነዶ ጐምርቶ በወቅቱ እንደሚሰበሰብ፣
ዕድሜ ጠግበህ ወደ መቃብር ትሄዳለህ።
27“እነሆ፤ ይህን ሁሉ መርምረናል፤ እውነት ሆኖ አግኝተነዋል፤
ስለዚህ ልብ በል፤ ተቀበለውም።”

Currently Selected:

ኢዮብ 5: NASV

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ