ዮሐንስ 17:6-19

ዮሐንስ 17:6-19 NASV

“ለእነዚህ ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገልጬላቸዋለሁ። የአንተ ነበሩ ለእኔ ሰጠኸኝ፤ እነርሱም ቃልህን ጠብቀዋል። የሰጠኸኝ ሁሉ ከአንተ እንደ ሆነ አሁን ዐውቀዋል፤ ምክንያቱም የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸው ተቀብለዋል፤ እኔም ከአንተ እንደ ወጣሁ በርግጥ ዐውቀዋል፤ አንተ እንደ ላክኸኝም አምነዋል፤ እነርሱ የአንተ ስለ ሆኑ እጸልይላቸዋለሁ፤ ለሰጠኸኝና የአንተ ለሆኑት እንጂ ለዓለም አልጸልይም። የእኔ የሆነው ሁሉ የአንተ ነው፤ የአንተ የሆነውም ሁሉ የእኔ ነው፤ በእነርሱም ከብሬአለሁ። ከእንግዲህ እኔ በዓለም አልቈይም፤ እነርሱ ግን በዓለም ውስጥ ናቸው፤ እኔም ወደ አንተ መምጣቴ ነው። ቅዱስ አባት ሆይ፤ እኛ አንድ እንደ ሆንን፣ እነርሱም አንድ እንዲሆኑ በሰጠኸኝ በስምህ ጠብቃቸው። እኔ ከእነርሱ ጋራ ሳለሁ፣ በሰጠኸኝ ስም ከለልኋቸው፤ ጠበቅኋቸውም፤ የመጽሐፍ ቃል እንዲፈጸም ከአንዱ ከጥፋት ልጅ በቀር ከእነርሱ ማንም አልጠፋም። “አሁን ወደ አንተ መምጣቴ ነው፤ ነገር ግን ደስታዬ በእነርሱ ዘንድ የተሟላ እንዲሆን፣ አሁን በዓለም እያለሁ ይህን እናገራለሁ። ቃልህን ሰጥቻቸዋለሁ፤ እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ፣ እነርሱም ከዓለም ባለመሆናቸው ዓለም ጠልቷቸዋል። የምለምንህም ከክፉው እንድትጠብቃቸው እንጂ፣ ከዓለም እንድታወጣቸው አይደለም። እኔ ከዓለም እንዳልሆንሁ ሁሉ፣ እነርሱም ከዓለም አይደሉም። ቃልህ እውነት ነው፤ በእውነትህ ቀድሳቸው። አንተ ወደ ዓለም እንደ ላክኸኝ እኔም ወደ ዓለም ልኬአቸዋለሁ። እነርሱ በእውነት የተቀደሱ እንዲሆኑ፣ ራሴን ስለ እነርሱ ቀድሻለሁ።”