ዮሐንስ 17:6-19
ዮሐንስ 17:6-19 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“ከዓለም ለይተህ ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገለጥሁ፤ ያንተ ነበሩ፤ እነርሱንም ለእኔ ሰጥተኸኛል፤ ቃልህንም ጠበቁ። የሰጠኸኝም ሁሉ ከአንተ እንደ ሆነ ዛሬ ዐወቁ። የሰጠኽኝን ቃል ሰጥቻቸዋለሁና፤ እነርሱም ተቀብለው ከአንተ እንደ ወጣሁ በእውነት ዐወቁ፤ አንተም እንደ ላክኸኝ አመኑ። እኔ ስለ እነርሱ እለምናለሁ፤ የምለምንህ ስለ ዓለም አይደለም፤ ስለ ሰጠኸኝ ነው እንጂ፤ ያንተ ናቸውና። የእኔም የሆነ ሁሉ የአንተ ነው፤ የአንተም የሆነ የእኔ ነው፤ እኔም በእነርሱ ከብሬአለሁ። እንግዲህ በዓለም አልኖርም፤ እነርሱ ግን በዓለም ይኖራሉ፤ እኔም ወደ አንተ እመጣለሁ፤ ቅዱስ አባት ሆይ፥ እነዚህን የሰጠኸኝን እንደ እኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ በስምህ ጠብቃቸው፤ እኔ በዓለም ከእነርሱ ጋር ሳለሁ ግን የሰጠኸኝን በስምህ እጠብቃቸው ነበር፤ ጠበቅኋቸውም፤ የመጽሐፉም ቃል ይፈጸም ዘንድ ከጥፋት ልጅ በቀር ከእነርሱ አንድ ስንኳን አልጠፋም። አሁን ግን ወደ አንተ እመጣለሁ፤ በእነርሱም ደስታዬ ፍጹም ይሆን ዘንድ ይህን በዓለም እናገራለሁ። እኔ ቃልህን ሰጠኋቸው፤ ዓለም ግን ጠላቸው፤ እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ እነርሱ ከዓለም አይደሉምና። ከክፉ ነገር እንድትጠብቃቸው ነው እንጂ ከዓለም እንድትለያቸው አልለምንም። እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉምና። በእውነትህ ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነውና። አንተ እኔን ወደ ዓለም እንደ ላክኸኝ እኔም እነርሱን ወደ ዓለም ላክኋቸው። እነርሱም በእውነት ቅዱሳን ይሆኑ ዘንድ ስለ እነርሱ እኔ ራሴን እቀድሳለሁ።
ዮሐንስ 17:6-19 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“ለእነዚህ ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገልጬላቸዋለሁ። የአንተ ነበሩ ለእኔ ሰጠኸኝ፤ እነርሱም ቃልህን ጠብቀዋል። የሰጠኸኝ ሁሉ ከአንተ እንደ ሆነ አሁን ዐውቀዋል፤ ምክንያቱም የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸው ተቀብለዋል፤ እኔም ከአንተ እንደ ወጣሁ በርግጥ ዐውቀዋል፤ አንተ እንደ ላክኸኝም አምነዋል፤ እነርሱ የአንተ ስለ ሆኑ እጸልይላቸዋለሁ፤ ለሰጠኸኝና የአንተ ለሆኑት እንጂ ለዓለም አልጸልይም። የእኔ የሆነው ሁሉ የአንተ ነው፤ የአንተ የሆነውም ሁሉ የእኔ ነው፤ በእነርሱም ከብሬአለሁ። ከእንግዲህ እኔ በዓለም አልቈይም፤ እነርሱ ግን በዓለም ውስጥ ናቸው፤ እኔም ወደ አንተ መምጣቴ ነው። ቅዱስ አባት ሆይ፤ እኛ አንድ እንደ ሆንን፣ እነርሱም አንድ እንዲሆኑ በሰጠኸኝ በስምህ ጠብቃቸው። እኔ ከእነርሱ ጋራ ሳለሁ፣ በሰጠኸኝ ስም ከለልኋቸው፤ ጠበቅኋቸውም፤ የመጽሐፍ ቃል እንዲፈጸም ከአንዱ ከጥፋት ልጅ በቀር ከእነርሱ ማንም አልጠፋም። “አሁን ወደ አንተ መምጣቴ ነው፤ ነገር ግን ደስታዬ በእነርሱ ዘንድ የተሟላ እንዲሆን፣ አሁን በዓለም እያለሁ ይህን እናገራለሁ። ቃልህን ሰጥቻቸዋለሁ፤ እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ፣ እነርሱም ከዓለም ባለመሆናቸው ዓለም ጠልቷቸዋል። የምለምንህም ከክፉው እንድትጠብቃቸው እንጂ፣ ከዓለም እንድታወጣቸው አይደለም። እኔ ከዓለም እንዳልሆንሁ ሁሉ፣ እነርሱም ከዓለም አይደሉም። ቃልህ እውነት ነው፤ በእውነትህ ቀድሳቸው። አንተ ወደ ዓለም እንደ ላክኸኝ እኔም ወደ ዓለም ልኬአቸዋለሁ። እነርሱ በእውነት የተቀደሱ እንዲሆኑ፣ ራሴን ስለ እነርሱ ቀድሻለሁ።”
ዮሐንስ 17:6-19 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገለጥሁላቸው። የአንተ ነበሩ ለእኔም ሰጠሃቸው፤ ቃልህንም ጠብቀዋል። የሰጠኸኝ ሁሉ ከአንተ እንደ ሆነ አሁን ያውቃሉ፤ የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸዋለሁና፤ እነርሱም ተቀበሉት፥ ከአንተም ዘንድ እንደ ወጣሁ በእውነት አወቁ፥ አንተም እንደ ላክኸኝ አመኑ። እኔ ስለ እነዚህ እለምናለሁ፤ ስለ ዓለም አልለምንም ስለ ሰጠኸኝ እንጂ፤ የአንተ ናቸውና፤ የእኔም የሆነ ሁሉ የአንተ ነው የአንተውም የእኔ ነው፤ እኔም ስለ እነርሱ ከብሬአለሁ። ከዚህም በኋላ በዓለም አይደለሁም፥ እነርሱም በዓለም ናቸው፥ እኔም ወደ አንተ እመጣለሁ። ቅዱስ አባት ሆይ፥ እነዚህን የሰጠኸኝን እንደ እኛ አንድ እንዲሆኑ በስምህ ጠብቃቸው። ከእነርሱ ጋር በዓለም ሳለሁ የሰጠኸኝን በስምህ እኔ እጠብቃቸው ነበር፤ ጠበቅኋቸውም መጽሐፉም እንዲፈጸም ከጥፋት ልጅ በቀር ከእነርሱ ማንም አልተፋም። አሁንም ወደ አንተ እመጣለሁ፤ በእነርሱም ዘንድ ደስታዬ የተፈጸመ እንዲሆንላቸው ይህን በዓለም እናገራለሁ። እኔ ቃልህን ሰጥቻቸዋለሁ፤ እኔም ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉምና ዓለም ጠላቸው። ከክፉ እንድትጠብቃቸው እንጂ ከዓለም እንድታወጣቸው አልለምንም። እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉም። በእውነትህ ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነው። ወደ ዓለም እንደ ላክኸኝ እንዲሁ እኔ ወደ ዓለም ላክኋቸው፤ እነርሱም ደግሞ በእውነት የተቀደሱ እንዲሆኑ እኔ ራሴን ስለ እነርሱ እቀድሳለሁ።
ዮሐንስ 17:6-19 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
“ከዓለም ውስጥ መርጠህ ለሰጠኸኝ ሰዎች የአንተን ማንነት ገለጥኩላቸው፤ እነርሱ የአንተ ነበሩ፤ አንተ እነርሱን ለእኔ ሰጠኸኝ፤ እነርሱም ቃልህን ጠብቀዋል፤ የሰጠኸኝ ሁሉ ከአንተ እንደ ሆነ እነርሱ አሁን ዐውቀዋል። የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸዋለሁ፤ እነርሱም ተቀብለውታል፤ ከአንተ ዘንድ መጥቼ መምጣቴንም በእውነት ዐውቀዋል፤ አንተ እንደ ላክኸኝም አምነዋል። “እኔ የምጸልየው ለእነርሱ ነው፤ እነዚህ የሰጠኸኝ የአንተ ስለ ሆኑ ለእነርሱ እጸልያለሁ፤ ለዓለም አልጸልይም። የእኔ የሆነው ሁሉ የአንተ ነው የአንተም የሆነው የእኔ ነው፤ እኔም በእነርሱ እከብራለሁ። እኔ ከእንግዲህ ወዲህ በዓለም ላይ አልኖርም፤ እነርሱ ግን በዓለም ናቸው። እኔ ወደ አንተ መምጣቴ ነው፤ ቅዱስ አባት ሆይ፥ እነዚህ የሰጠኸኝ እንደእኛ አንድ እንዲሆኑ ለእኔ በሰጠኸኝ ስምህ ጠብቃቸው። ይላሉ” እኔ አብሬአቸው በነበርኩ ጊዜ በሰጠኸኝ ስምህ ጠብቄአቸዋለሁ፤ እኔ ጠበቅኋቸው፤ ስለዚህ የቅዱስ መጽሐፍ ቃል እንዲፈጸም ከዚያ ከጥፋት ልጅ በቀር ከቶ ከእነርሱ ማንም አልጠፋም። አሁን እኔ ወደ አንተ መምጣቴ ነው፤ በዓለም ላይ ሳለሁ ይህን የምናገረው ደስታዬ በእነርሱ ዘንድ ፍጹም እንዲሆን ነው። እኔ ቃልህን ሰጥቻቸዋለሁ፤ እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ እነርሱም ከዓለም አይደሉም፤ ስለዚህ ዓለም ጠላቸው። ከክፉው እንድትጠብቃቸው እንጂ ከዓለም ውጪ እንድትወስዳቸው አለምንም። እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ እነርሱም ከዓለም አይደሉም። በእውነትህ ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነው። አንተ እኔን ወደ ዓለም እንደ ላክኸኝ እኔም እነርሱን ወደ ዓለም ላክኋቸው። እነርሱ በእውነት ቅዱሳን እንዲሆኑ እኔ ራሴን ስለ እነርሱ ቅዱስ አደርጋለሁ።
ዮሐንስ 17:6-19 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
“ከዓለም ወስጥ ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገለጥሁላቸው። የአንተ ነበሩ፤ ለእኔም ሰጠሃቸው፤ ቃልህንም ጠብቀዋል። የሰጠኸኝ ሁሉ ከአንተ እንደሆነ አሁን ያውቃሉ፤ የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸዋለሁና፤ እነርሱም ተቀበሉት፤ ከአንተም ዘንድ እንደ ወጣሁ በእውነት አወቁ፤ አንተም እንደ ላክኸኝ አመኑ። እኔ ስለ እነርሱ እለምናለሁ፤ ስለ ሰጠኸኝ ስለ እነርሱ እንጂ ስለ ዓለም አልለምንም፤ እነርሱ የአንተ ናቸውና፤ የእኔም የሆነ ሁሉ የአንተ ነው፤ የአንተ የሆነውም የእኔ ነው፤ እኔም በእነርሱ ከብሬአለሁ። ከዚህም በኋላ በዓለም አይደለሁም፤ እነርሱ ግን በዓለም ናቸው፤ እኔም ወደ አንተ እመጣለሁ። ቅዱስ አባት ሆይ! እነዚህን የሰጠኸኝ እንደ እኛ አንድ እንዲሆኑ በስምህ ጠብቃቸው። ከእነርሱ ጋር በዓለም ሳለሁ የሰጠኸኝን እኔ በስምህ እጠብቃቸው ነበር፤ ጠበቅኋቸውም፤ የመጽሐፉም ቃል እንዲፈጸም ከጥፋት ልጅ በቀር ከእነርሱ ማንም አልጠፋም። አሁንም ወደ አንተ እመጣለሁ፤ በእነርሱም ዘንድ ደስታዬ የተፈጸመ እንዲሆንላቸው ይህን በዓለም እናገራለሁ። እኔ ቃልህን ሰጥቻቸዋለሁ፤ እኔም ከዓለም እንዳልሆንሁ ሁሉ እነርሱም ከዓለም አይደሉምና ዓለም ጠላቸው። ከክፉ እንድትጠብቃቸው እንጂ ከዓለም እንድታወጣቸው አልለምንም። እኔ ከዓለም እንዳልሆንሁ ሁሉ እነርሱም ከዓለም አይደሉም። በእውነትህ ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነው። ወደ ዓለም እንደ ላክኸኝ ሁሉ እኔም ወደ ዓለም ላክኋቸው፤ እነርሱም ደግሞ በእውነትህ የተቀደሱ እንዲሆኑ እኔ ራሴን ስለ እነርሱ እቀድሳለሁ።”